ዛሬ በተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሪው ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ድል ሲቀናቸው ክልል ላይ በነበረ ብቸኛ ጨዋታ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከመከላከያ ያለግብ ተለያይተዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ
9:00 ሲል የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ደግሞ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚደረግ ጨዋታ በመሆኑ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ እጅግ በጉጉት ተጠብቆ ነበር። እንደተጠበቀውም እጅግ በርካታ ደጋፊ በስታዲየሙ በመገኘት ያማረ እና የደመቀ ህብረ ዝማሬ በማሰማት መጀመር ችሏል።
በጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚሰለጥነው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአንፃሩ በጣም ወደኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ከተገኘ ግብ ለማስቆጠር ካልተቻለም ተከላክሎ 1ነጥብ ይዞ ለመውጣት ያቀዱበትን የጨዋታ ዘይቤ ይዞ መጓዝ ችሏል። ሆኖም ይህ የጨዋታ ዘይቤ ሊያዛልቀው አልቻለም። የጨዋታው መጠናቀቂያ እየተጠበቀ በነበረበት ሰዓት 91ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና ፈራሚ ባፕቲስቴ ፋዬ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ ቡናን ጣፋጭ 3ነጥብ ስታጎናፅፍ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ደግሞ አሳዛኝ ተሸናፊ አድርጎታል። ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 26አድርሶ 6ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአንፃሩ በ14ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ደደቢት ከ አዳማ ከተማ
ከኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ 11:30 ሲል የጀመረው ሌላኛው ጨዋታ በሊጉ መሪ ደደቢት እና ከጊዜ ወደጊዜ ወጥ አቋሙን በማሳየት ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ሲሆን በውጤቱም ባለሜዳው ደደቢት በኤፍሬም አሻሞ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
ደደቢት ሁለት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች ተሸንፎ እንደመምጣቱ መጠን ይህንን ጨዋታ ለማሸነፍ ተጫዋቾቹ ላይ መነቃቃት ይታይ ነበር። በአዳማ ከተማ በኩል በ16ኛው ሳምንት ወልድያ ከተማ ላይ ያስመዘገበውን የ3-1 ጣፋጭ ድል የሊጉ መሪ ላይ በመድገም ወደ ዋንጫው የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳመር ያደረጉት እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ነው። በዚህም መሰረት በሁለተኛው አጋማሽ 57ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ ኤፍሬም አሻሞ ያስቆጠራት ግብ ደደቢትን ከ3ኛ ተከታታይ ሽንፈት ታድጋዋለች።
ሆኖም ይህ ጨዋታ የቀጠለው እስከ 82ኛው ደቂቃ ድረስ ብቻ ነበር። 82ኛው ደቂቃ ላይ የስታዲየሙ መብራት(ፓውዛ) በመጥፋቱ ጨዋታው ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ሊቋረጥ ችሏል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም ተመልሶ በርቶ ጨዋታቸውን ያከናወኑ ሲሆን ምንም የውጤት ለውጥ ሳይኖር ጨዋታው በደደቢት 1-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል። ውጤቱንም ተከትሎ ደደቢት 32ነጥቦችን በመሰብሰብ መሪነቱን ማጠናከር ሲችል አዳማ ከተማ በበኩሉ ከመሪው ደደቢት በ7 ነጥቦች ርቆ በ25 ነጥቦች ወደ 5ኛ ደረጃ ሊንሸራተት ችሏል።

አስተያየት ይስጡ