“ማሸነፍ የነበረብንን ጨዋታ በዳኛዋ ተነጥቀናል፤ ፍፁም ቅጣት ምቱ አያሰጥም” ሄኖክ አዱኛ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በታላቅ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የፋሲል ከነማና የቅ/ጊዮርጊስ ጨዋታ 2ለ2 ተጠናቋል፤ከጨዋታው በላይ ትኩረት የሳበው 83ኛው ደቂቃ ላይ ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ ለፋሲል ከነማ የሰጠችው የፍፁም ቅጣት ምት ተገቢነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችንና ተጨዋቾችን አበሳጭቷል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱን ያሰጠው ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ተበድለናል፤ ፍፁም ቅጣት ምቱም አያሰጥም ሲል ተናግሯል፡፡

ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ወቅታዊ አቋም የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል?
ሄኖክ፡- አዎ ለውጥማ አለን…ነገር ግን ያ ብቃታችን ገና እየጨመረ የሚሄድ ነው፤ወቅታዊ አቋማችን አሪፍ ነው…በተለይ ባለፉት ጨዋታዎች የተሻለ አቋም እያሳየን ነው፤ወልዋሎን ከሜዳ ውጭ ማሸነፋችን በራስ መተማመናችንን ጨምሯል።ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ በከበደበት ሁኔታ ይሄ ለውጥ መገኘቱ ደስ ይላል፤ፋሲል ከነማንም ለማሸነፍ ብንገባም በዳኛዋ በደል ደርሶብናል፡፡
ሀትሪክ፡-ከፋሲል ከነማ ጋር ስትጫወቱ የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት ተገቢነው ትላለህ…?በእርግጥስ ሱራፌልን አልነካኸ ውም?
ሄኖክ፡- በፍፁም ልክ አይደለም…ህዝቡ ይፈርዳል፤የዳኛዋ ውሳኔ ጎድቶናል 2 ነጥብም አሳጥቶናል። ዳኞች ላይ በእርጥግም ብዙ ጫና እንዳለ ይገባኛል፤ አርቢትሯ አቻችላ ለመውጣት የገባች ነው የሚመስለው፤ ከባድ ጨዋታ አልነበረም…ነገር ግን ተበድለናል…ይሄ መስተካከል አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ ተጨዋቾች ግን የፍፁም ቅጣት ምቱ ተገቢ ነው…ማሸነፍም ይገባናል እያሉ ነው? አንተስ?
ሄኖክ፡- በፍፁም ቅጣት ምቱ…አትጠራጠር ተገቢ አልነበረም…ኮርና ነው ብዬ ልመለስ ስል ነው ፍፁም ቅጣት ምት የሰጠችው በጨዋታ ሂደትም ከነርሱ የተሻልን የነበርነውና የሞከርነው እኮ እኛ ነን፡፡ ባለሜዳ የምንመስለው እኛ ነበርን…ባናሸንፍም በዚያ ጫና ውስጥ እንዲህ መጫወታችን ደስ ይላል፡፡
ሀትሪክ፡- የሊጉን ዋንጫ የማንሣት እድል አለን ማለት ትላለህ?
ሄኖክ፡- በእርግጠኝነት…!…የእስ ካሁኑን የዋንጫ ጥማታችንን በደንብ እናሳካለን…ይሄ አይቀርም።
ሀትሪክ፡-ቀጣዩ ጨዋታችሁ ከአዳማ ጋር ነው፤ የአዳማው ዳዋ ሁቴሳ ጊዮርጊስን እንከብደዋለን እያለ ነው ትቀበለዋለህ?
ሄኖክ፡-በእርግጠኝነት አሸንፈን የ1ኛ ዙር መሪ ሆነን እንጨርሳለን…አዳማ ፍፁም ሊከብደን አይችልም ዳኝነት ግን መስተካከል አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- በዳኛ ጉዳይ የምትለን ከሆነ ዳኛ ጭምር የሚያሸንፍ ቡድን የለም እያልክ ነው?
ሄኖክ፡- በጣም ነውኮ ዳኞች ጊዮርጊስን የሚበድሉት…ዳኛ ብቻ ደግሞ አይደለም አንዳንድ ጋዜጦችም የሚሰሩት ልክ አይደለም መስተካከል አለበት፡፡
ሀትሪክ፡-ጨዋታው አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ ያለው ስሜትህ ምንድነው?
ሄኖክ፡- አውርቻለሁ…ይቅርታ ካጠፋው…ቲቪ ላይ እንደገና አየዋለው ብላኛለች…ጥፋት ደግሞ በእርግጠኝነት ይገኝበታል…
ሀትሪክ፡-ለደጋፊዎቻችሁ…የምትለው ነገር አለ…?
ሄኖክ፡-ጎንደር ድረስ ተጉዛችሁ …ይህን ያህል ኪሎ ሜትር አቋርጣችሁ ለመጣችሁ…ለደገፋችሁን ደጋፊዎቻችን ይህን በደል አይተው መመለሳቸው አሳዝኖኛል…በቀጣይ ጨታዎች እንደምንክሳቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport