“ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ራሴን የምገልፅበት ክለብ ስለሆነልኝ ነው”አቤል ማሞ /ኢት.ቡና/

“ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ራሴን የምገልፅበት ክለብ ስለሆነልኝ ነው”

“ትክክለኛ የበረኛ አሰልጣኝ ያገኘሁት በክለብ ሣይሆን በብሔራዊ ቡድን ነው”
አቤል ማሞ /ኢት.ቡና/


የእግር ኳስ ሀሁን የጀመረው በቢሸፍቱ ከነማ ነው /የመጫወት እድል ባያገኝም/ ፊንጫ ስኳር፣ ሻሸመኔ ከተማ ሙገር ሲሚንቶና መከላከያ ከተጫወተ በኋላ ለካሳዬ አራጌ ኢትዮጵያ ቡና ማገር ለመሆን ለቀጣዮቹ 2 አመታት ፈርሟል፡፡ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ መከኒሳ ተብሎ በተጠራው ስፍራ የሆነው እንግዳችን ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ነው፡፡ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለግብ ጠባቂነት ፍላጎቱ፣ አሁን ስላለበት ደረጃ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግብ ጠባቂ ያለው ትርጉም መዛባቱ፣ ችሎታዬን ለማሳየት ለቡና ፈርሜያሁ ስለማለቱ፣ ስለሚያደንቀው ተከላካይ፣ ለአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር ስለነበረው ግንኙነት፣ ጠያቂ ተጨዋቾች በአሰልጣኞች ስላለመወደዳቸው፣ ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎች በአሰልጣኞች ስለሚያጡት እምነት፣ ስለ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር የቦርድ አባልነቱና ሌሎች ጉዳዮች ምላሹን የሰጠው የአዲሱ አመት የመጀመሪያ እንግዳችንን አቤል ማሞ በርካታ ጉዳዮችን ዳሷልና ተከታተሉት፡፡


ሀትሪክ፡- እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሰህ?

አቤል፡- እንኳን አብሮ አደረሰን ለመላው የስፖርት ቤተሰቡ በመጀመሪያ ለአዲሱ ለ2013 ዓ.ም እንኳን አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ የሠላም አመት ይሁንላችሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የ2013 የመጀመሪያው የሀትሪክ እንግዳ ሆንክ…?

አቤል፡- /ሳቅ/ ደስ ይላል መስከረም ሁለትን በኢንተርቪው ላስታውስ ነው /ሳቅ/ ከበዓል ቀጥሎ ባለው ቀን ማለት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በዓሉ ጾም ቀን /አርብ/ ነው ጋዜጣው የወጣው በቅዳሜ በፍስክ ቀን ነው?

አቤል፡- /ሳቅ/ በላ የፍስክ ነገሮችን እናውራ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- የግብ ጠባቂነት መነሻህ የት ነው?
አቤል፡- ተወልጄ ያደኩት መካኒሳ አካባቢ ነው፤ከልጅነቴ ጀምሮ ባደኩበት ሰፈር በረኝነትን ጀመርኩ እኔ ባላውቀውም ሰዎች ስገባና ስወጣ ሲያዩ ያበረታቱኝ ነበር ፍላጎቱም ስለነበረኝ በዚያው ገፋሁበት፤በርግጥ መሀል ላይ ገባ ወጣ እል ነበር ኳስ ተጨዋች መሆን እፈልግ ነበረና… አንዳንዴ አልገባም ብዬ በእግር ለመጫወት እጥር ነበርና ግብ ጠባቂነቱ ይሻልሃል የሚሉኝም ነበሩ፡፡ ፖዘቲቭ የሚያስቡ ከኔ ከፍ ያሉ ልጆች ያበረታቱኝ ነበርና መነሻዬ ከዚህ ይጀምራል፡፡

ሀትሪክ፡- ግብ ጠባቂነት ተሰጥኦህ ነው ትመጥናለህ ብሎ ያሳመነህ ማነው?

አቤል፡- አብርሃም አራርሶ በዚህ በኩል ቅድሚያውን ይወስዳል፡፡ ፤ጊዮርጊስ ይጫወት ነበር፡፡ ሰፈር አካባቢ መካኒሳ ጉሊት ሰፈር የሚካሄድና ሲሳይ በሚባል ልጅ ይዘጋጅ የነበረ ውድድር ነው፡፡ ሲሳይ በህይወት የለም /ነፍስ ይማር ብያለሁ/ በዚህ ውድድር ላይ የኛ ቡድን ግብ ጠባቂ እኔ ነበርኩና አብርሃም አይቶኝ ስለኔ የሚታየውን ጥሩ ነገር ይነግረኝ ነበር፤በርታ ከበረታህ ጥሩ ደረጃ ላይ ትደርሳለህ ብሎ ያበረታታኝ ነበር እድሉን አግኝቼ ለማመስገን ማስታወስ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ…እንዳለኝ ጠንክሬ በመስራቴ ለዚህ ደረጃ ደርሻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አሁን ያለህበት ደረጃ ደርሰህ ተገናኝታችሁ ታውቃላችሁ?
አቤል፡- አዎ በተለይ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በቲቪ ሲታይ ያይና ቻት ስናደርግ ይሄ ጥሩ ነው ይህን አስተካከል በማለት ይመክረኛል ነገር ግን ወደ ክለብ ደረጃ ስደርስ በኔ ላይ አሻራ የጣሉ ብዙ ናቸው፡፡ ከአብርሃም ውጪ ዞንታ የሴቶች ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ትልቁን ቦታ ይይዛሉ፡፡

ሀትሪክ፡- ለ6 ክለቦች ተጫውተሃል፤ በተለይ በሻሻመኔ ከተማ የነበረው ቆይታህ ረዘም ያለ ነው ቆይታህ ምን ይመስላል… ሙገር ስትገባ የጋሽ አዳነ እጅ ነበረበትና ዘርዘር አድርገህ አውጋን?

አቤል፡- ሻሸመኔ 4 አመት ተጫውቻለሁ… እንደገባሁ ነው ቋሚ የነበርኩት ነገር ግን ጉዳት ደርሶብኝ ቡድኑን ተለየው አገግሜ ስመለስም ቦታዬን አስከብሬ ተጫውቻለሁ ያኔ አሰልጣኙ ደጄኔ ጫካ ይባላል፡፡ ከ4 አመት በኋላ ባህር ዳር ላይ በተደረገ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የማደጊያ ውድድር ላይ የሙገር ዋና መልማይ የነበሩትና በርካታ ተጨዋቾች ላይ አሻራቸውን ያሳረፉት ጋሽ አዳነ አይተው መረጡኝ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግን እፈልጋለሁ የቡደኑ አሰልጣኝ የውጪ ዜጋውን የወልቂጤ ግብ ጠባቂ ሲፈልግ ጋሽ አዳነ አቤል ነው ብለው ተከራከሩ…. በዚህ ልዩነት ውስጥ ሙገር ገብቼ ጋሽ አዳነን አላስፈርኳቸውም እንደሄድኩ ነው ቋሚ የሆንኩት በሙገር ተሰላፊነቴ ገና 4 ጨዋታ እንደተጫወትኩ ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመረጥኩ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶም ጥሪ አድርጎልኛል አልረሳውም፡፡

ሀትሪክ፡- ከ6ቱ ክለቦች ቆይታ የትኛው ጊዜህ ነው ምርጡ?

አቤል፡- ወደ ኋላ ልመልስህ ነው /ሳቅ/ መሰረት የያዝኩበት ጊዜ ለኔ ምርጡ ነው መነሻዬ እሱ ነው ያ ጊዜ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር ሁለት ጊዜ አንደኛ ወጥተን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግ ወደሚደረጉ ውድድሮች የሄድንበትን ጊዜ አልረሣም፡፡ አሁን ላለው አቤል እነዚህ ጊዜያት ናቸው ትልቁን አስተዋፅኦ የተወጡት… እርሱን ባላልፍ ድንገት አሁን ላንገናኝ እንችል ነበር፡፡ ከዚያ ባለፈ በመከላከያ ተሰላፊነቴ በአመት ሁለት ጊዜ ዋንጫ የወሰድንበት ጊዜ ልዩ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ለግብ ጠባቂ ያለው ቦታ መልካም ነው ተብሎ አይታሰብምና እንዲስተካከል የምትፈልገው የቱ ጋ ነው… ?

አቤል፡- ይህንንማ አይተናል አሁን አሁን የራሣቸው ፍልስፍና ያላቸው፣ ግብ ጠባቂውን አካተው መጫወት የሚችሉ በአንድ እጅ ጣት የማይሞሉ አሰልጣኞች አሉ እግዚአብሔር ይመስገን.. እነዚህ አሰልጣኞች ግብ ጠባቂ ተጨዋች እስኪመሰል ድረስ አገነኑን እንጂ በፊት የነበረውማ በረኛ ግብ ጠባቂ ብቻ ነበር፡፡ ትልቁ ሚና ግብ ጠባቂው ጋር ሆኖ ይሰጠው የነበረው ቦታ ግን በጣም አናሳ ነበር፡፡ በየክለቡ የበረኛ አሰልጣኝ ራሱ ዋናው አሰልጣኝ ሲሆንም አይተናል ይሄ የትኩረት አለመስጠትን ያሳያል ሁለተኛ ሚናው ምን እንደሆነ አለማወቅ ጭምር ነው፡፡ በረኛ ማለት የቡድኑን 50 በመቶ የሚይዘው ማለት ነው ተብሎ በሰለጠኑት ሀገራት ይጠራልና ይሄን ደረጃ የማየት አቅም ሊኖረን ይገባል፡፡ ለበረኛ ሙሉ ክብር ሲሰጥ ደስ ይላል ውጤቱ የጋራ ነው፡፡ በረኛ ሆነው ያለፉ አቅም ያላቸውን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ማየት ደስ ይላል እኛ ሀገር ግን ይሄ የለም፡፡ ትኩረት መስጠት ዋጋ ያስገኛልና ቢስተካከል ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- አንድ ኃላፊ ታኬታ ለቡድኑ ሲገዛ ለሶስት በረኞች አንድ ጫማ ገዝቶ መጣ ሶስት በረኞቹ እያሉ እንዴት አንድ ትገዛለህ ሲባል ሲገቡ ይቀያየሩት ደግሞ ለመቆም የምን 3 ታኬታ ነው ያለበት አጋጣሚ አለ አሉኝ እውነት ነው?

አቤል፡- /ሳቅ/ ይሄ በጓንትም ገጥሞኛል… አንድ ጓንት ተገዝቶ ይቀያየሩ የሚገባው አርጎ ይግባ ተብሎም ያውቃል፡፡ ሙሉ ትጥቅ ማድረግ ተጨዋቹንም በረኛውን የማነሳሳት አቅም አለው ያኔ ገቢያችን በራሳችን የምንገዛበት አልነበረም አሁን ግን ተሻሽሎ ቡድኑ ሰጠም አልሰጠም የራሳችንን የምንገዛበት ጊዜ ላይ ደርሶናል፡፡ ከፋይናንስ እጥረት ብቻ ባይሆን ከእውቀት ችግር የመነጨ ይመስለኛል፡፡ አሁን ላይ ግን የሚኖር አይመስለኝም፡፡

ሀትሪክ፡- እንደ ማን.ሲቲው ግብ ጠባቂ ኤደርሰን በእግር መጫወት ይፈልጋል አሉኝ… እውነት ነው?

አቤል፡- ራሴን ለመግለፅ ያህል የሚመጡ አሰልጣኞች በሙሉ እንደዚህ አይነት ስሜት እንዳለኝ ይነገሩኛል፡፡ እግርህ ጥሩ ነው ይሉኛል በተለይ ያለፍኩባቸው ክለቦች ይህን ነገር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በብሔራዊ ቡድን ወደ 5 የሚጠጉ አሰልጣኞች መጥተዋል የየራሳቸው ፍልስፍና ቢኖራቸውም ተመሳሳይ ነገር ካላቸው አምስቱም የመጀመሪያ ቋሚ በረኛ አድርገው አጫውተውኛል፡፡ በየትኛውም ፍልስፍና ውስጥ መጫወት እንደምችል አውቃለው ለዚህም ነው የሚመርጡኝ… እግሬ ብቻ ሳይሆን የትኛውንም የጨዋታ ሚና ቢሰጡኝ እንደምወጣው አውቀው መርጠውኛል፡፡ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ሲያስፈርመኝ እግሬ አሪፍ መሆኑን ስለተረዳ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለቡና የፈረምከው የተከፈለህ ብር ብዙ ስለሆነ ወይስ የካሳዬ ተፅዕኖ?

አቤል፡- ቡናን ስወደው ኖሬያለሁ… የመጫወት ህልሜም የቆየ ነው ነገር ግን ክለቡ በውጪ በረኛ ላይ ባለው እምነት የተነሣ ሳልገባ ፍላጎቴን ገድቤ ኖሬያለሁ የመጫወት እድል ባገኝና በገባሁ ብዬ ተመኝቼ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ያንን ስላላየሁ አርፌ ተቀምጫለሁ ካሳዬ ግን ሲገባ ደስ አለኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ራሴን የምገልፅበት ክለብ ስለሆነልኝ ነው ለዚያ ደግሞ ትልቁን ሚና የተወጣው ካሳዬ አራጌ ነው የርሱም የአሠልጣኞች ቡድንም በዚህ ላይ እምነቱ አላቸው የሚፈለገውን ለመግለፅ ብቁ ነኝ ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- ከቡና ደጋፊ ያገኘኸው ምላሽ ምን ይመስላል?

አቤል፡- ሙገርም ሆነ መከላከያ እየተጫወትኩ ለኔ የነበራቸው ስሜት ጥሩ ነበር ቡና እንድገባ የሚጠይቁኝ የሚያበረታቱኝ ብዙ ናቸው ብዙ ጊዜ ስታዲየም ጨዋታ ለማየት የምገባው የቡናን ነው ደጋፊው ለእኔ ያኔም ጥሩ ስሜት ነበራቸው፡፡ ከፈረምኩ በኋላ በተለያዩ ፔጆች ላይ በተለይ ሊያነሳሳኝ በሚችል መንገድ እያበረታቱኝ ነው እኔ እንደዚህ ነኝ ወይ ብዬ እስክጠይቅ ድረስ በደንብ ተቀብለውኛል ደስታቸውንም ገልፀውልኛል፡፡ መጀመሪያም አከብራቸው ነበር አሁን ግን ጭራሽ ብሶብኛል.. /ሳቅ/ ያለኝን በሙሉ እንድሰጥ አነሳስተውኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በአንተ ፊት ሲቆም በራስ መተማመንህ እንዲጨምር የሚያደርግህ ተከላካይ ማነው?

አቤል፡- አቅም ቢኖርህም ኮሚዩኒኬሽን ወሣኝ ነው አቅም ያላቸው ተከላካዮችን አይቻለው፡፡ ግንኙነቱ መናበቡ አሪፍ ሲሆን አቅማችን ጎልቶ ይወጣል፡፡ ተከላካይ ክፍሉ ጥሩ መናበብ ካለው ውጤት ይዘን እንወጣለን በዚያ መሀል በግሉ ልዩ የሚሆን ተጨዋች ሊኖር ይችላል፡፡ ለኔ ከአቅም በላይ ወሳኙ ኮሚዩኒኬሽኑ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሻሸመኔ ከተማ በቀለ እልሁና አፈወርቅ ዮሀንስ ጋር ተጫውቻለሁ፡፡ የሚሰጡኝ ድጋፍ የሚፈጥሩልኝ በራስ መተማመን ልዩ ነው ልምድ አላቸው ምርጥ አጋዥ ናቸው ከነርሱ ይህን አይቻለሁ አሁን ያሉት ተከላካዮችም ይህን መቅሰም አለባቸው በራስ መተማመን እንዲኖርህ ትጥራለህ ባይኖርህ እና ባይሳካልህ ደግሞ ደጋግመህ ትሞክራለህ፡፡ አሁን ደግሞ አስቻለሁ ታመነ ጥሩ አቅም አለው በብሔራዊ ቡድን ላይ አብሬው ተጫውቻለሁ አንተነህ ተስፋዬም አለ በመከላከያ ምንተስኖት ከበደ ጥሩ ነው ደስ የሚል በራስ መተማመን አላቸው እኔንም የራስ መተማመን እንዲኖረኝ አድርገውኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ምርጡ አሰልጣኝ ላንተ ማነው?

አቤል፡- መሰረት ወደጣልኩበት ልመልስህ ነው ለአሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ትልቅ ቦታ አለኝ ያለኝን አቅም ነግሮኝ ነው ያሳደገኝ… መወቀስም ሲኖርብኝ በደንብ ወቅሶኛል ይሄ አይጠቅምም ይሄ አሪፍ ብሎ ትልቅ አሻራ ጥሎብኛል ሁሌም ነው የማመሰግነው፡፡ ሲቀጥል ነፍሱን ይማረውና የሻሸመኔው አሰልጣኝ ደጀኔ ጫቃንም አመሰግናለሁ፡፡ ሲኒየር በረኞች በነበሩበት አምኖ አሰልፎኛል ያለህን ነው የምፈልገው እንጅ እድሜ ሕግ አይደለም ብሎ አጫውቶኛል በዚህ በዚህ በብዛት ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞች በራስ መተማመንን ሰጥተውኛል ለይቼ የማያቸው በብሔራዊ ቡድን ዮሀንስ ሳህሌን አመሰግናለው እንደመጀመሪያነቴ ሳያየኝ አምኖ አሰልፎኛል፡፡ ከኔ የተሻሉ ሲኒየሮች እያሉ እኔን አምኖ አቅሜን እንጂ ስሜን ሳያይ አሰልፎኛል እነኚህ በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በመከላከያ ተሰላፊነትህ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ አይታመንበህም.. ተደጋጋሚ ጊዜ ተቀያሪ በረኛ ነህ ተቀበልከው ውሳኔውን?

አቤል፡- የምፍልገውን ጥያቄ ነው ያነሳኸውና አመሰግናለሁ፡፡ መቶ ፐርሰንት ልምምድ ስትሰራ የመተጣጠፍ ሁኔታው ወይም ሜዳዎቹ ጥሩ ባለመሆናቸው ጉዳት ያጋጥማል ረጅም ጊዜ ያስቀመጠኝ የብሽሽት ጉዳት አጋጥሞኛል፡፡ እርሱ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ የማልረሳው ብሔራዊ ቡድናችን ከጋና ጋር ተጫውቶ 2ለ0 ተሸነፍን፡፡ ከቀናት በኋላ ደግሞ መከላከያ ኢንተርናሽናል ጨዋታ አለው፡፡ በደርሶ መልስ ጨዋታ ተቀያሪ ነው የሆነኩት በሀገር ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ቋሚ ሆኜ በክለብ ግን ተቀያሪ ነበርኩ፡፡ አልተመቸኝም የአሰልጣኝ ስዩም ውሣኔ.. ነገር ግን የቡድኑን መንፈስ ላለመረበሽ ብጥርም መናደዴን ልደብቅ አልቻልኩምና ተናገርኩ… ምንድነው ከኔ የምትፈልጉት ብዬ ሁሌ ጮህኩ፤ አብረውኝ የነበሩትን በረኞችን አከብራለሁ አቅም አላቸው፡፡ ሊያስቀምጡኝ ሁሉ ይችላሉ… ያም ሆኖ በደርሶ መልስ ተሸንፈን ወጣን፡፡ ጨዋታው ሲያልቅ ምንድነው ችግሩ ብዬ አሰልጣኝ ስዩምን ስጠይቀው “እንድታርፍ ነው” አለኝ /ሳቅ/ መጠየቅ ግን ነበረብኝ… ደከመኝ ቡድኑን እጎዳለሁ ስል ነበር ማረፍ የነበረብኝ… ለዋሊያዎቹ ተጫውቼ ስመጣ አልተጎዳሁም የኔ ስራ መጫወት ቢሆንም እንደዚህ አይነት ነገር ሲኖር በግልፅ መነጋገር አለብን፡፡

ሀትሪክ፡- አቤል፣ ዳዊት… ጠያቂ ናቸው ይሏችኋል አሰልጣኞች ደግሞ መጠየቅ አይፈልጉም… ይሄ ባህሪህ አልጎዳህም?

አቤል፡- ኮስታራና ጠያቂ መሆኔ የጎዳኝ ይመስለኛል /ሳቅ/ ቡድኑ ውስጥ ከአሰልጣኙ ቀድሜ ገብቼ ይሆናል ወይም አሰልጣኙ ቡድኑ ውስጥ ቀድሞኝ ገብቶ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለእኔ እግር ኳስ ንግግር ነው፡፡ ስትነጋገር ነው ውጤት የሚመጣው የተበላሸው የሚስተካከለው ይሄ መለመድ አለበት… ቡና አስፈርሞኝ የሚከፍለኝ ኃላፊነት ሰጥቶኝ ነው ከቻልኩ ቻልኩ ነው ካልቻልኩ ለመቻል ደግሜ እሰራለሁ… የምጫወተው ሆነ የምቀመጠው በአቅሜ መሆን አለበት፡፡ አጨዋወት ሲቀያየር ቋሚ ወይም ተቀያሪ ልትሆን ትችላለህ… ድንገት ግን ስትጠይቅ ምናልባት ግጭት የሚፈጥሩ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ልክ ነው ልክ አይደለም ስትል ይኮረፋል.. ብዙ ችግርም ሊፈጠር ይችላል… ጠያቂ ተጨዋቾች የሚጎ ዱት ከፊት ለፊት ሳይሆን ከጀርባቸው ነው ፊት ለፊት ስትጠይቅ ነገሮች የሚጦዙት ከጀርባህ ነው ይሄ ከባድ ጉዳይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- መከላከያን ስታስብ ቅሬታ ወይስ ደስታ ይሰማሃል…? ቡድኑ ላይስ የምትለው አለ?

አቤል፡-ቡድኑ መጥፎ ነው እያልኩ አይደለም… የሚረዱት ፊት ለፊት ለቡድኑ የሚጠቅመውን እንድንናገር የሚፈልጉ አሉ፡፡ ስታወራ የሚረዱህ እንደነ ምንያምርና ሙሉ አይነት ሰዎችም አሉ ዝም አትበሉ ይሉን ነበር ማንንም ለማስወቀስ ሌላውን ለመጥቀም ሣይሆን በእግር ኳስ ቋንቋ ነው የምናወራውና አንዳንዴ ስትናገር ጥጋበኛ ጉረኛ ማን አለብኝነት ነው ይሉሃል ብቻ እግር ኳስ ውስጥ ውይይት ይጠይቃል፡፡

ሀትሪክ፡- እኛ ሀገር ተጨዋቾች ከአሰ ልጣኞች ጋር በግልፅ ሲናገሩ ብዙም አይታይም… ይሄስ መጥፎ ባህል አይደለም?

አቤል፡- እግር ኳስ ውይይት ይፈልጋል፡፡ እንዳንዴ በሃሳብ የሚመራህን ሰው ትቀድምና ልትጋጭ ትችላለህ… ለኛ ሀገር ከባድ ነው… በኛ ሀገር ተማሪዎች አስተማሪዎችን በጥያቄ ሲያፋጥጡ እንዳንድ ት/ቤቶች እድል ሊከለክሉ ይችላሉ… ስትጠይቅ አቅም ልትፈትሽ ሁሉ ትችላለህ ተብሎ ነው ይህ ሃሣብ መኖር የለበትም በእግር ኳሱም ተመሳሳይ መሆኑ ያሳዝናል አሰልጣኝና ተጫዋች ስለ እግር ኳሱ ካላወሩ ምን ሊያወሩ ይችላሉ? በርግጥ ስራዬ መጫወት ቢሆንም የሚታዩ ችግሮችን መናገር አለብኝ ይሄ መለመድ አለበት አንድን ተጨዋች የምታናግረው ስለቀረብከው ብቻ አይደለም፡፡ ያልቀረብከውም አለማናገር ተገቢ አይደለም የአሰልጣኙ በር ክፍት መሆን አለበት መፍትሔ የሚሆነው አሰልጣኞች ተጨዋች እስኪመጣ የማይጠብቁ ወደ ተጨዋቾቹ ገብተው ሃሣባቸውን እንዲገልፁ የሚያደርጉ መሆን አለባቸው አሰልጣኙ ተጨዋቹ እስኪመጣ ሲጠብቅ የማይስተካከል ችግር ቢከሰትስ? ቤተሰባዊ ግንኙነት መኖር አለበት፡፡ በሰለጠነው አለም በልምምድ ሰዓት ተጨዋቹ አሰልጣኙ ላይ ሎጬ ሲያስቆጥር ይታያል ይሄ ትልቅ ህብረት ይፈጥራልና እዚህ አገር መለመድ አለበት፡፡ በክለብ ደረጃ የገጠመኝን እያወራሁ ነው ውይይት የለም ውይይት ኖሮ ሁሉም ሃሳቡን የሚገልፅበት መድረክ ቢኖር ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች በአሰልጣኞች አይታመንባቸውም.. ይህን ታዝበሃል?

አቤል፡- ምንም ጥያቄ የለውም ለውጪ በረኞች ያለው ክብር ለኛ ቢሰጠን ምናለበት ብዬ ተመኝቻለሁ፡፡ 2009 ላይ ጊዮርጊስ ዋንጫ ወስዶ እኛ ታች ደረጃ ላይ እያለን ሮበርት ኦዶንካራ እያለ የአመቱ ኮከብ በረኛ ተብዬ የተመረጥኩት እኔ ነኝ ይሄ የሚያሳየው ምንድነው? 5 ተከታታይ አመታት ያሸነፈውን መቅደም ምን ትርጉም ይሰጣል? ግልፅ ነው.. አለን.. እድል ካገኘን ማደግ እንችላለን የሚል ትርጉም አለው፡፡ ልዩነቱ በግልፅ ታይቷል፡፡ የኔ አቅም ጥሩ ስለነበር ማመን ባትፈልግም የግድ ትቀበለዋለህ፡፡ በግል የነበረኝ ጥረት፣ የተሰጠኝ እድል ፣ ከቡድኑ ጋር የነበረኝ ጥምረት ውጤት ነው… አቅም ስላለኝ ነው ይሄ በኔ ብቻ አይቆምም ሌሎች ምርጥ በረኞችም አሉን፡፡ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ትክክለኛ የበረኛ አሰልጣኝ ያገኘሁት በክለብ ሣይሆን በብሔራዊ ቡድን ነው /ሳቅ/ አሊረዲ በወቅቱ አሰልጣኜ ነበር፡፡ ዮሐንስ ሳህሌ መርጦኝ አሊ ረዲ ተረከበኝ የበረኛ አሰልጣኝ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ካገኘሁ የነበረኝን ጉዞ ከማድነቅ ውጪ አማራጭ የለኝም፡፡ የኔ የህይወት ታሪክ ይሄ ነው… የገባብን ግብ ሣይሆን ሊሻሻል ስለሚቻለው ጉዳይ ትኩረት ማድረግ አለብን በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለቦች በረኞች ተወቃሽ ናቸው ነገር ግን በጥረታችን እንጂ ተሰርቶብን እንዳልመጣን ሊታወቅ ይገባል በአካዳሚው ያደገና በጥረቱ የመጣን በረኛ ማወዳደር ትልቅ ፋውል ነው፡፡ ተመልከት የውጭ ዜጎች ይቅሩ እየተባለ እንኳን አሁንም ዜጋዎችን እያስፈረሙ ነው ይሄኮ ንቀት ነው ትኩረት አለመስጠት ነው በሀገሬ ሁለተኛ ዜጋ የሆንኩበት ጉዳይ መቆም አለበት፡፡ ይሄ ክለቦቻችን ላይ ያለ ወረርሽኝ ቢወገድ ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በዝውውር ደረጃ ትልቁ ጫና የክለቦች ወይስ ፌዴሬሽኑ?

አቤል፡- ትልቁ ሚና የሚወጡት ክለቦች ናቸው፡፡ የውጪ በረኛ አምጥተን ምን ተጠቀምን የሚለው መመርመር አለበት የውጪ ሀገር በረኛ ይዘው ዋንጫ የወሰዱ ቢኖሩም የወረዱት ብዙዎች ናቸው፡፡ ለፈለጉት አላማ የውጪ ዜጋ ቀጥረው ውጤት ያጡ ብዙ ክለቦች ናቸው በአፍሪካ መድረክ ይሳተፉና ወዲያው በአንደኛው ዙር ግን ይወድቃሉ.. ለምን ታዲያ ለሀገር ውስጥ በረኞች ቅድሚያ አይሰጡም? በሀገሬ መከበርና ቅድሚያ ማግኘት አለብኝ የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ እጥረት አለ እየተባለ ለመፍትሔው ብዙ አልተጓዝንም፡፡ እንደአመራር ፌዴሬሽኑ የራሱን ሥራ መስራት አስፈላጊ ያለውን ውሣኔ ደግሞ መወሰን አለበት፡፡ የምር ፕሮፌሽኑ ይከበር ከተባለ ክለቦች አቋማቸው ማስተካከል አለባቸው፡፡ ወልቂጤ ከተማን ተመልከት ከየሆነ ጨዋታ በኋላ ይድነቃቸው ከዳኔ ዜጋውን በረኛ ተቀያሪ ወንበር ላይ እንዲቀመጥ አድርጎል ይሄ እምነት ሌሎች ክለቦች ላይም መታየት አለበት ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የውጪ ዜጋ አይኑር የምትል ይመስላል?

አቤል፡- አይምጡ አላልኩም አይጫወቱ የሚልም ቃል አልወጣኝም እኛም ነገ ፕሮፌሽናል ሆነነ ልንወጣ እንችልልኮ .. ፈልገን ለውጪ ክለቦች ሲቪ ልከን የሌላ ሀገር በረኛ አንፈልግም ተብለናል ይሄ ግን በኢትዮጵያ የለም በፊፋም ሆነ በካፍ አታስፈርሙ አይሉም ሀገሪቷ ግን ለራሷ ስትል ውሣኔ መወሰን አለባት፡፡

ሀትሪክ፡- በአሰልጣኝ ይሁን በደላላ ገንዘብ አምጣ ቦጭቅ ያለህ የለም..?

አቤል፡- ውል ገብቼ አብሬያቸው የምሰራቸው ኤጀንቶች አሉኝ ይሄን ኃላፊነት ለአክብረትና ታማር ሰጥቻለሁ… ከተፈራረምን 6 አመት አልፎናል ከማገኘው ገንዘብ ላይ በፐርሰንት እየወሰዱ የኔን ጉዳይ እንዲይዙ ተፈራርሜ ስራ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ከየትኛውም አሰልጣኝ ጋር በገንዘብ ጉዳይ ተነጋግሬ አላውቅም አንዴ መጥቶ መልሻለሁ፡፡ በሰራሁት ልክ ይከፈለኛል የእኔን ጉዳይ የያዙ ሕጋዊ ኤጀንቶች አሉኝ በቃ፡፡

ሀትሪክ፡- ቀልደኛ ነው ሲነሳበት ደግሞ ቁጡ ነው አሉኝ ሁለቱ የተቃረኑ ባህሪዎች እንዴት አስማማሃቸው?

አቤል፡- /ሳቅ/ ማስመሰል ሳይሆን ያለሁበት ቦታና ሁኔታ ይወሰነዋል በስራ ሰዓት መቀለድ አልወድም ልምምድ ላይ የተወሰነ ሳቅ ጨዋታ ሊኖር ይችላል ከዚያ በኋላ ስራ ነው ትኩረት ያሻዋል በልምምድ ሰዓት ሲሪየስ ነኝ፡፡ አንዳንዴም ሳይቀርቡህ ስም የሚሰጡህ አሉ ጉረኛ የሚልህም አይጠፋም ጉረኛ የሚለው የኔ ሁለተኛ ስሜ ነው /ሳቅ/ ጉራን ግን አላውቀውም፡፡ ሲሪየስ ነኝ ፊቴ ትንሽ ኮስተር ይላልና ጉረኛ ይሉኛል ብዙ ሰው ኮስታራ ስለሆንኩ የማልስቅ ጥርስ የሌለኝ ይመስለዋል /ሳቅ በሳቅ/ በጣም እጫወታለሁ ለማላውቀው ሰው ጋር ግን መጀመሪያ መተዋወቅ ይቀድማል፡፡ ከተዋወቅን በኋላ ሲቀርቡ ግን የሰጡኝን ስም አንስተው ይቅርታ ጠይቀውኛል… ገጥሞኝ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ዝምታን ብዙ ሰው አይወድም እንጂ ጉረኛም አስቸጋሪም አይደለሁም

ሀትሪክ፡- የፕሮፌሽናል ተጨዋቾችና ባለሙያዎች ማህበር የቦርድ አባል ነህና ምን እየሰራችሁ ነው?

አቤል፡- የተጨዋቾች ማህበር በሀገራችን መመስረቱ ለተጨዋቾች ትልቅ ትንሣኤ ነው.. ማህበሩ ለተጨዋቾች መብት የሚከራከር የሚያስጠብቅም ተቋም ነው ማህበሩ ሲመሰረት እኛ አምነን ተጨዋቾቹ ደግሞ እንዲያምኑበት አድርገን በርካታ አባላትን አካቷል ተጨዋቾች ሲጎዱ ይጠይቃል… ሌሎች በጎ አድርጎት ስራዎችን ይሰራል፡፡ ማህበሩ እንደጅማሬ ካየነው ጥሩ ተጉዟል ማለት እችላለሁ፡፡ ልምድ ያላቸውና የተሻሉ ሰዎች ተካተውበት ከነርሱ ጋር የልምምድ ልውውጥ አድርገን ጥሩ ስራ ተሰርቷል፡፡ ጅማሮው በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ ነውማለት እችላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ፍቅረኛ አለህ.. አገባህ.. ወለድክ?

አቤል፡- /ሳቅ/ ፍቅረኛ አለችኝ ነገር ግን ወደ ትዳሩ አልገባሁም.. ጉዟችንን ሳየው ግን የሚመራን ወደ ትዳሩ ነውና በቅርቡ ጋብቻው ይፈፀማል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- የጋብቻ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደምጠራ ተስፋ አደርጋለሁ?

አቤል፡- /ሳቅ በሳቅ/ ምንም ጥያቄ የለውም አዲስ ሱፍ ግዛ…

ሀትሪክ፡- መግቢያው አዲሱ ሱፍ ነው እንዴ?

አቤል፡- /ሳቅ በሳቅ/ አይደለም እኛ የምንፈልገው አንተን እንጂ ሱፉንማ አይደለም ነገር ግን ለአዲስ ትዳር አዲስ ሱፍ የግድ ነው/ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ… የመጨረሻ የምስ ጋና ቃል ካለህ?

አቤል፡- ሁላችንም እንኳን ለዘመን መለወጫ አደረሰን ዘመኑ የሠላም፣ የፍቅር፣ የጤና፣ የመተሳሰብና የመደማመጥ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ሀትሪኮችም አሁን አሪፍ አሪፍ ስራዎች እየሰራችሁ ነው በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ስራ የምትሰሩበት ጉዟችሁም የስኬት እንዲሆን ምኞቴን እገልፃለሁ… ለዚህ ያበቃኝ እንድናወራ ስላለን ኖረን እንድንመካከር ያደረገን እግዚአብሔር ይመስገን በኔ ህይወቴ ውስጥ ያለፉ አሰልጣኞችና ተጨዋቾችን አመሰግናለሁ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ዮሐንስ ሳህሌን አመሰግናለሁ እግዚአብሔር ያክብራችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ሜዳ ላይ ድጋሚ የምንገናኝበት አመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ የምወዳቸው ቤተሰቦቼን፣ የፍቅር ጓደኞቼን ከልብ አመሰግ ናለሁ መልካም ዘመን ይዘንላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport