ለባለውለተኞቻችን የተዘረጋው የሸዋረጋ ደስታ እና የጓደኞቹ ደጋግ እጆች

 

“ባለውለተኞቻችን በዚህ መልኩ አስታዋሽ አጥተው ተረስተው ማየት በጣም ያማል”
ሸዋረጋ ደስታ

አፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት አካባቢ በሚገኘው ዩኒየን ባርና ሬስቶራንት አዳራሽ ውስጥ በርካታ ሠዎች ተሰባስበዋል፡፡ በሆቴሉ አዳራሽ ውስጥ ከተሰባሰቡት ከፍ ያለውን ቁጥር የያዙት ደግሞ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ውለታን ጥለው ያለፉ የሀገር ባለውለተኛ ጀግኖች ግን ደግሞ የውለታቸውን ያህል ያልተከበሩና አስተዋሽ ያላገኙ ናቸው፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡትና የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናዮችና የክብር እንግዶች ከነበሩት 10ሩም የቀድሞ የኢትዮጵያ ብ/ቡድንና መቻልን ጨምሮ የታላላቅ ክለቦች ተጨዋቾቹና አሰልጣኞች ትናንት በጨዋታ ዘመናቸው በሚያሳዩት ድንቅ የጨዋታ ጥበባቸው በዘመኑ የነበሩትን ሁሉ አስቦርቀዋል፤ ከተቀመጡበት ተነስተው እንዲያጨበጭቡም በድንቅ ችሎታቸው አስገድደዋቸዋል፡፡ በዚህም በርካቶች በወቅቱ ባሳዩት ድንቅ ጨዋታና ለሀገራቸው በዋሉት ታላቅ ውለታ አንቱታንና ከበሬታን አላብሰዋቸው እንደነበር ሁሉም የማይዘነጋው ነው፡፡ እነሱም በወቅቱ በነበራቸው የህዝብ ፍቅርና ክብር ተደስተው የጨዋታ ዘመን ፋይላቸውን ዘግተዋል፡፡
ዛሬስ? ዛሬማ ያ ሁሉ ክብርና ፍቅር አብሯቸው እንደሌለ ይልቁን ውለታቸው ተረስቶና አስታዋሽ እንዳጡ የፊታቸው ገፅታ አፍ አውጥቶ ያሳብቃል፡፡
መቶ አለቅ አይነሸት (ለመቻልና ለኤርትራ)፣ በሀብቱ ገ/ማርያም የመድን አሰልጣኝ (ለመቻልና መድን አሰልጣኝ)፣ መርሻ ሚደቅሳ (ለዋልያ፣ የተጫወተና ለኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ የነበረ)፣ ሲሳይ ተፈራ ሞሪስ (መቻል)፣ ቡታ አስመሮም (መቻል)፣ ሠለሞን ተስፋዬ (ማዕከላዊ ዕዝ ግብ ጠባቂ)፣ ተሾመ ተፈራ (ቀዌ) (ለቡና ገበያ የተጫወተ)፣ ተስፋዬ (መረብ ኳስ) እና አረፋ አይኔ (መቻል እባዬ ሶራ) እነዚህ ሁሉ ስሞች በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ እግር ኳስና ስፖርት ውስጥ ከፍ ብለው ሲሰሙ የነበሩና ዛሬ ግን ውለታቸው ተረስቶ አስታዋሽ ያጡ ባለውለተኞች ናቸው፡፡


ዛሬ ግን ምስጋና ለቀድሞው የንግድ ባንክ ተጨዋችና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባልና የቀድሞ የተጨዋቾችና ደጋፊዎች የመረዳጃ ማህበር ፕሬዚዳንት የነበረው ሸዋረጋ ደስታና ጓደኞቹ ይግባና ባለውለተኞቹ አስታዋሽ አግኝተዋል፡፡ ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አለምንና ሀገራችንን ክፉኛ ያስጨነቀበትና የፈተነበት ወቅት በመሆኑ ከጨዋታና ከስልጠና የራቁት እነዚህ የሀገር ባለውለተኞች አሁን የት ነው ያሉት? ይሄንን ክፉ ጊዜስ እንዴት ነው እያሳለፉ የሚገኙት? በማለት 10ሩን ባለውለተኞች ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ካሉበት ቦታ አፈላልጎ እናንተማ ተረስታችሁ አትቀሩም አለንላችሁ በማለት እነ ሸዋረጋ ደስታ ለ10ሩም ባለውለተኞች ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡
በሸዋረጋ ደስታ አስተባባሪነት አቶ ፍቅሩ ተረፈ እንዲሁም የቀድሞ የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ተጨዋች የነበረው ሰለሞን መንገሻ (ከአሜሪካ)፣ አቶ ተመስገን (ከሶቶይስ) በአንድነት በመሆን ከላይ ለተጠቀሱት 10 ባለውለተኞች ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡
በዕለቱ በዩኒየን ባርና ሬስቶራንት በተደረገው ስነ-ስርዓት ላይ የበጎ አድርጎት ስራው ዋና አስተባባሪ የሆነውና የሀገር ባለውለተኞች በተቸገሩ ጊዜ ከፊት ቀድሞ በመገኘት የሚታወቀው ሸዋረጋ ደስታ “ከውለታችሁና ከታሪካችሁ አንፃር ይህቺ ትንሽ ስጦት የምትመጥናችሁ ባትሆንም አይዟችሁ አለንላችሁ ለማለት ያህል ለአስራችሁም ባለውለተኞች ለእያንዳንዳችሁ 5 ሌትር ዘይት፣ ሁለት አይነት ሣሙና 5 ኪሎ ዱቄት፣ 5 ኪሎ ሩዝ ሁለት አይነት ፓስታ፣ 3 ኪሎ መኮሮኒ፣ የንፅህና መጠበቂያ ሶፍት (ብዛት 12)፣ 2 ሌትር ላርጎና፣ እቃውን ይዛችሁ ስትሄዱ መንገላታት እንዳይደርስባችሁ ለራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል ትንሽዬ ገንዘብ አዘጋጅተንላችኋል በማለት ስጦታውን ከቅርብ ጓደኛውና የድጋፉ ዋና ተባባሪ ከሆነው የሄሮን ኢንተርናሽናል ሆቴል ሀዋሳ ባለቤት አቶ ፍቅሩ ተረፈ ጋር በጋራ በመሆን አስረክበዋል፡፡


ለባለውለተኞች ድጋፍ እናድርግ፣ እናስታውሳቸው፣ አለንላችሁ እንበላቸው ከሚል ቅን ስሜት በመነሣት ፍቅሩ ተረፈን፣ ሰለሞን መንገሻንና ተመስገንን በማስተባበር ትልቁን ስራ የሰራው ሸዋረጋ ደስታ ከርክክቡ በኋላ እንደተናገረው “እናንተ የሀገር ባለውለተኛ ለእኛም ጀግኖቻችን ናችሁ፣ ወንድሞቻችን ናችሁ፣ እርዳታ የሚጀመረው ከቤተሰብ ነው፤ እናንተ ደግሞ ቤተሰቦቻችን ናችሁ፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ውለት የፈፀማችሁ ስለሆነ ይህቺን ጥቂት እርዳታ ከጓደኞቼ ጋር ከፍቅሩ፣ ከሠላሞን መንገሻ (አሜሪካ) ከተመስገን (የሶቶይስ ባለቤት) ጋር በመሆን አለንላችሁ፣ አስታዋሽ አጥታችሁ አትቀሩም በማለት ያደረግንላችሁ ድጋፍ ነው፤ ይሄ መነሻ ነው፤ በቀጣይም ከጎናችሁ መሆናችንን የምናሳይበት ነው” በማለት ተናግሯል፡፡
ሌላው ለባለውለተኞች በተደረገው ድጋፍ ላይ እኔ የድርሻዬን አግዛለሁ አለሁ በማለት እገዛ ያደረገው የሄሮን ኢንተርናሽናል ሆቴል ሀዋሳ ባለቤት አቶ ፍቅሩ ተረፈ በበኩሉ “እውነት ለመናገር ይሄንን በጎ ተግባር የምናደርግበትን መድረክ ያመቻቸውን ሸዋረጋ ደስታን በጣም ነው የማመሰግነው፡፡ እናንተ የሀገር ባለውለተኞች ናችሁ፤ በጨዋታ ዘመናችሁ አስደስታችሁናል፣ አስቦርቃችሁናል፤ እናንተን ሣይና ፊታችሁ ስቆም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፤ ለሀገር ብዙ ሰርታችሁ አስተዋሽ ማጣታችሁ የሚያሳዝን ቢሆንም ለሀገር በሠራችሁት ስራ ግን ልትኮሩ ይገባል፡፡ በክለብ ደረጃም በሀገርም ትልቅ ስራን ሠርታችሁ ውለታን ፈፅማችሁ ያለፋችሁ በመሆኑ ተረስታችሁ መቅረት የለባችሁም፤ ልናስታውሳችሁ ከጎናችሁ ልንቆም ይገባል በሚል ነው ይህቺን ትንሽ ሙከራ ያደረግነው፤ በቀጣይ ከሸዋረጋ ደስታ ከዚህ ሙከራ ተምረን ደስታን ከሰጣችሁን እናንተ ባለውለተኞቻችን ጎን እንሆናለን በማለት አቶ ፍቅሩ ተፈራ (የሄሮን ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት በመጨረሻ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡


ድጋፍ የተደረገላቸው 10ሩ የቀድሞው ባለውለተኞች በተደረገላቸው ድጋፍና በተለይ በዚህ ፈተና በበዛበት ሰዓት አለንላችሁ የሚልና አስተዋሽ በማግኘታቸው በእንባ ታጅበው በተወካያቸው በአቶ በሀብቱ ገ/ማርያም አማካይነት ምስጋናና ምርቃት አቅርበዋል፡፡


የእርዳታ አሰጣጥ ፕሮግራሙ ከመዘጋቱ በፊት አቶ ሸዋረጋ ደስታ ፕሮግራሙ የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ ያደረጉለትን በተለይ ጋዜጠኛ ታሪኬ ቀጭኔ የማስተባበር ትልቁን ሚና በመጫወቱና ከጎኑ የነበሩትን የሚዲያ ሰዎች አመስግኗል፡፡
የዩኒየን ባርና ሬስቶራንት ባለቤት ፕሮግራሙ የሚካሄድበትን አዳራሽ ከመፍቀድ ጀምሮ ለባለውለተኞቹ እና በዕለቱ በስፍራው ለተገኙት የክብር እንግዶች የክብር ግብዣ ማድረጋቸውም የሚታወቅ ነው፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.