“ሁሉም አሰልጣኞች ሥራቸውም አቅማቸውም አንድ አይነት በመሆኑ ለእኔ የጨመሩልኝ ነገር የለም”አዲስ ሕንፃ/ሀድያ ሆሳዕና/

“ሁሉም አሰልጣኞች ሥራቸውም አቅማቸውም አንድ አይነት በመሆኑ ለእኔ የጨመሩልኝ ነገር የለም”

“ሱዳን ያስቆጠረችው ግብ ከተሻረበት ቀን ጀምሮ በቃ አልሞትም አልኩ እግዚአብሔርም እያኖረኝ ነው”
አዲስ ሕንፃ/ሀድያ ሆሳዕና/


ተወልዶ ያደገው ደብረዘይት አካባቢ ሲሆን ከርሱ በፊት የነበሩ ካልሆነ በስተቀር ተምሣሌት ሳይኖረው ወደ እግር ኳሱ ተቀላቅሏል፡፡ እንግዳችን ከት/ቤት ጀምሮ ላለፉት 14 አመታት ስኬታማ የእግር ኳስ ህይወት እንደነበረው ይናገራል፡፡ በመድን ድርጅት የተጀመረው የእግር ኳስ ህይወቱ ለኢትዮጵያ ባንኮች፣ ለደደቢት ለሱዳኑ አልአህሊ ሸንዲና ለአዳማ ከተጫወተ በኋላ ለ2013 የውድድር አመት ለሀዲያ ሆሳዕና ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል፡፡ እንግዳችን አዲስ ህንፃ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ በቅርብ ጊዜ በነውጠኞች ቤቱ ቢፈርስበትም ስለ ጉዳዩ ብዙ መናገር እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡ በበርካታ ጉዳዮችም ላይ የድፍረት ምላሹን የሰጠው አዲስ ስለ አሰልጣኞች ብቃት፣ ስለ አፍሪካ ዋንጫ ቆይታው፣ ስለ አልአህሊ ሸንዲ፣ ከሱዳን ጋር በነበረው ጨዋታ ስለተቆጠረበት ግብ፣ የኛ ሀገር ኳስ ስላለማድጉ አላሳካሁትም ስለሚለው ነገር፣ የገንዘብ እንጂ የማሊያ ፍቅር የላችሁም ስለሚለው ትችት፣ ስለ ሀዲያ ሆሳዕና ጉዞው፣ አብሮት በክለብ ደረጃ ሊጫወት ስለሚፈልገው ተጨዋች፣ የክለቦች የደመወዝ መክፈል አቅም መዳከምና ሌሎች ጉዳዮች የሰጠው ምላሽ ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- ፕሮፋይልህን ስመለከት ያየሁትና ትኩረቴን የሳበው አንድ ፎቶ ከነዋይ ደበበ ጋር የተነሳኸው ነውና አድናቂው ነኝ?

አዲስ፡- /ሳቅ/ የድሮ ዘፈንና ድምፃዊ ደስ ይሉኛል ከንዋይ ጋር ደግሞ አሜሪካ ተገናኝተን የተነሳነው ፎቶ ነው፡፡ የድሮ ዘፈኖች ደስ ይሉኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ባለፉት 14 አመታት ለ5 ክለቦች ተሰልፈህ ተጫውተሃል… ከነዚህ ክለቦች ስኬታማው ጊዜህ የቱ ነው?

አዲስ፡- ከደደቢት ጋር የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን የሆንኩበትና ከብሔራዊ ቡድን ጋር ለደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫ ያለፍኩበት በስኬት የምጠራው ጊዜዬ ነው፡፡ ከዚያ ወጪ ኳስ ሣቆም የማውራው ታሪኬ ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን፣ ከሱዳን ጋር ስንጫወት በረኛ ሆኜ ማሳለፌ እኔ በረኛ ስገባ ግብ መቆጠሩ.. ብዙው ታሪኬ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-እስቲ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍንበትን ጊዜ አስታውሰኝ ስሜቱ ምን ይመስል ነበር?

አዲስ፡- የሚገርም ጊዜ ነበር ምርጥ ስብስብ ይዘናል ሙሉ ህዝቡ ደጋፊያችን ሆኖ ከጎናችን ቆሟል በኔ እምነት የማይደገም ጊዜ ነው ብዬ አምናለው… ምናልባት እግዚአብሔር ዳግም ካላመጣው በስተቀር… የሚገርም ፍቅር ነበርን አሰልጣኙና ተጨዋቹ በደንብ ተዋህዷል ተስማምቷል ከኔ ይልቅ እገሌ ይገባ የሚባልበት ቡድን ነበረን፡፡ አንዴ ሽመልስ ተቀያሪ ሆኖ ቱሳ ሲገባ አይ ሽሜ ይግባ እርሱ ጥሩ አቅም እያሳየ ነው የእኔ ችግር የለም ልቀመጥ ያልኩበት ቡድን ነበርን… ያ ብሔራዊ ቡድን ከውጤቱ በላይ የነበረው ፍቅርም ይገርማል፡፡

 

ሀትሪክ፡-በወቅቱ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድናችን ለ2 የተከፈለ ነበር …የአሰልጣኝ ሰውነት ቡድንና ሌሎች አባላት ተብሎ ለሁለት መከፈላችሁ ይነገር ነበር ወሬው እውነት ነበር?

አዲስ፡- ይባላል ምን የማይባል ነገር ነበር፡፡ ደጋፊው ሌላ ይላል የቡና ደጋፊዎች የተለየ ነገር ይሉ ነበር አሰልጣኙ ውጤት ስለነበረው ግን ማን ሊናገረው? በጣም ጥሩ ውጤት የነበረው ብሔራዊ ቡድን ነበረን፡፡ ሁሉም ሳይለያይ ከራሱ ይልቅ ለቡድኑ ውጤት ሲያስብ ያየሁበት ስብስብ እንደነበር ነው የማውቀው፡፡ ግን ብሔራዊ ቡድን በአንዴ እንዴት ይበተናል? ሲኒየር ይዘህ ወጣቶችን ሁለት ሶስት እያልቅ ትቀላቅላለህ እንጂ በአንዴ መበተን ተገቢ ውሳኔ አልነበረም፡፡

ሀትሪክ፡- ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው በእድል ነው ያን ያህል ሊጋነን አይገባም በ4 ጨዋታ ብቻ ማለፍ ኩራት ሊፈጥር አይገባም የሚል ሃሣብ ያላቸው ሰዎች አሉ …ትቀበለዋለህ?

አዲስ፡- እንኳን ያኔ አሁን ድረስ ለአፍሪካ ዋንጫ በተከታታይ የምናልፍ ይመስለኝ ነበር የፌዴሬሽኑና የጋዜጠኞች ችግር ነው እንዲህ ያደርገው… ከውጪ አሰልጣኝ የሚያመጡት ጋዜጠኞች ነበሩና ቡድኑ ፈራረሰ፡፡ ከውጤት አንፃር ካየህ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈን… ለአለም ዋንጫ ለማለፍ 180 ደቂቃ ብቻ ነበር የቀረን… ከዚህ ሌላ ምን ውጤት ይምጣ? በእድል ነው ለሚሉ አንድስ ጨዋታ አሸንፈው ያውቃሉ? ከኢትዮጵያ ወጥቶ ያሸነፈ ቡድን አለን? ያኔ የነበረው ቡድን ነው ይህን ያደረገው እግር ኳሱ አካባቢ ያለ ሰው ከኛ ጭምር ምቀኛ ነው… ከኛም በኋላ ጥሩ እድል አልነበረንም? ነበረን… ግን መች ተሳካ?

ሀትሪክ፡-በረኛ ገብተህ በነበረበት የኢትዮጵያና የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ጨዋታ ላይ 2ለ0 እየመራን ባለቀ ሰዓት ትክክለኛ ግብ ተቆጥሮብን ዳኛው ግን ሻረው.. አልደነገጥክም?

አዲስ፡- ጨዋታው የተካሄደው ሱዳን ቢሆን ኖሮ ይፀድቅ ነበር ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለሚወደኝ ተሻረ፡፡ ከምለው በላይ ደንግጫለሁ፡፡ ከዚያ ቀን በኋላ ነው አልሞትም ያልኩት… ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፍን ያለ ህዝብ ያ ጎል ቢጽድቅ ገብቶ ምን ያደርገኝ ነበር? አይገለኝም ብለህ ነው? ሱዳን ያስቆጠረችው ግብ ከተሻረበት ቀን ጀምሮ በቃ አልሞትም አልኩ እግዚአብሔርም እያኖረኝ ነው፤

📸 Mandatory Credit: Photo by Armando Franca/AP/Shutterstock

ሀትሪክ፡-በጨዋታ ዘመንህ በኔ ላይ ምርጥ ነገር ጨምሯል ብለህ የምታደንቀው አሰልጣኝ ማነው?

አዲስ፡- ብዙ ለይቼ እገሌ ነው የምለው አሰልጣኝ የለም ሁሉም ግን ለኔ ጥሩ ናቸው

ሀትሪክ፡- በኔ ላይ የተለየ ነገር የጨመረ የለም ሁሉም እኩል ናቸው እያልክ ነው?

አዲስ፡- /ሳቅ/ የተለየ ነገር የጨመረልኝ አሰልጣኝ የለም እንደሚታወቀው ሁሉም አሰልጣኞች አንድ ሥራቸውም አቅማቸውም አንድ በመሆኑ ለእኔ የጨመሩልኝ ነገር የለም… ውጪ ቢሆኑ እንኳን የተለየ ኳሊቲ ይኖራቸው ነበር በተለምዶ የሚያሰሩት አንድ አይነት ስለሆነ የተለየ ነገር አልገጠመኝም ያም ሆኖ ግን ሁሉንም አሰልጣኞቼን አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የኛ ሀገር ኳስ እያደገ ሄዷል ማለት ይቻላል?

አዲስ፡- እያደገ የመጣው ካልክ ደጋፊው ነው በየክልሉ ደጋፊው በዝቷል እንጂ ኳሱ ያው ነው ለውጥ የለውም፡፡

ሀትሪክ፡-ኳሱ አላደገም የተጨዋቾች ክፍያ ግን በተቃራኒው ከፍ ብሏል አይመ ጣጠንም የሚሉ ሰዎች ልክ ናቸዋ!?

አዲስ፡- አይ አይ.. እንደ ውጤት እንጂ እንደ ምንሰራው ስራ ካየነው ያንሰናል… እንዲያውም እንደ ድሮው ደመወዝ 5 ሺህ ብር ሆኖ የፊርማ ክፍያ ቢሰጠን ይሻላል፡፡ አሁን ስታስብ በ2 አመት ውስጥ ወደ 4 ሚሊዮን ብር ይወጣል በፊት በነበረው ቢኬድ የሚያወጡት ከ1 ሚሊዮን ብር አካባቢ ብዙም አይበልጥም 1 ሚሊዮን የፊርማ ክፍያ 5 ሺ ብር ደመወዝ ያዋጣል ለተጫዋቾችም ይጠቅማል 1 ሚሊዮኗ በአመቷ አንድ ነገር ላይ ውላ 2 ሚሊዮን ልትደርስ ትችላለች፡፡ አሁን ባለው ሂደት የ50 ሺህ ብር ገደቡ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ፌዴሬሽኑ መብት አለው ብዬም አላምንም ይሄኮ ገበያ ነው የኳስ ህይወትኮ ገበያ ነው እቃ ሄደህ እንደምትገዛው ማለት ነው፡፡ በራሳችን ጉልበት ነው የምንደራደረውና ተመን ማውጣት የለባቸውም ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- በ14 አመት ቆይታህ ገንዘብ የጠየቀህ አሰልጣኝ ወይም የአሰልጣኝ ተወካይ የለም?

አዲስ፡- /ሳቅ/ አንድም ሰው ጉቦ የጠየቀኝ አልገጠመኝም ምንም የለም ወሬው አለ ሁሉንም አሰልጣኞችኮ አታምናቸውም ከኔ የጠየቀ አሰልጣኝ ግን የለም ከሌሎች ተጨዋቾች ጠየቁ ሲባል ይሰማል፡፡

ሀትሪክ፡-ተፈልገህ ስለምትገባ ይሆን?

አዲስ፡- እሱን እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው አንዱ ምክንያት ሲሆን ይችላል አንዳንዴም ስፖርተኞችም ሲቸገራቸውም ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡

ሀትሪክ፡-በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ አላሳካሁትም የምትለው ጉዳይ አለ?

አዲስ፡- አላሳካሁም ብዬ የምቆጭበት ነገር የለም እግዚአብሔር ይመስገን ዋንጫ ከደደቢት ጋር አግኝቻለሁ ከሀገሬ ጋር ለአፍሪካ ዋንጫ አልፌያለሁ ያ የተጨዋቾች ህልም ነው ያን አድርጌያለሁ ምናልባት ግን የአመቱ ኮከብ ተብዬ አለመመረጤ ቅር ቢለኝም የፓሽን ስፖርት መጽሔት የአመቱ ኮከብ በመባሌ ተፅናንቼያለሁ ከሞላ ጎደል በኳስ ጨዋታ ዘመኔ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የአሁኖቹ ተጨዋቾች የገንዘብ እንጂ የማሊያ ፍቅር የላቸውም ይባላል… ምን ምላሽ አለህ?

አዲስ፡- በራሴ የሚሰማኝን ልግለፅልህ… ባለሁበት ክለብ ስጫወት ለክለቡ የምችለው አደርጋለሁ፡፡ ግጥሚያው ላይ ያለኝን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ የማደርገው እንዲህ ነው፡፡ ገንዘብ ገንዘብ የሚባለው ግን ስራኮ ነው እንጀራ ነው እንደዚህ የሚባል ነገር አይመቸኝም፡፡ ለቡድኑ ያለኝን ፍቅር የምገልፀው በስራዬ በተሰጠኝ ኃላፊነት ታማኝ በመሆን ነው፡፡ ከሰውም ሲባል የምሰማው የቡና ቤት ነው ለክለቡ ማልያ ፍቅር ስትል ገንዘብ ቀንሰህ ተጫወት ይላሉ ሲባል እሰማለሁ፡፡ በኔ በኩል ግን አልቀበልም በስራዬ እንደማልደራደር ታማኝ እንደምሆን ክፍያው ላይም በተመሳሳይ ጠንክሬ ነው የምደራደረው፡፡

📸 Mandatory Credit: Photo Hossana sport page

ሀትሪክ፡-ወደ 5 ክለቦች ተዘዋውረህ ተጫውተሃል… ሳትፈልግ በግድ የወጣህበት ክለብ አለ?

አዲስ፡- እስካሁን የለም ደደቢትም ፈልጌ ነው የወጣሁት ወደ አልአህሊ ሸንዴ ለመጓዝ ስለፈለኩ… መድን ግን ያደኩበት የመጀመሪያ ክለቤ እንደመሆኑ ሳልፈልግ የወጣሁ ይመስለኛል፡፡ አመራሮቹ እኛ ጋር ነው ያደገው ብለው ገንዘቡን ሲቀንሱብኝ ነው የወጣሁት፡፡ እዚያ አድጌ 12 ግብ አስቆጠርኩ ከውጪ የመጣና 6 ግብ ያስቆጠረ ተጨዋች ደግሞ ከኔ በጣም የሚበልጥ ክፍያ አገኘና ጨምሩ ብዬ ስናገር እኛ ክለብ ውስጥ አድገህ እንዴት እንዲህ ትጠይቀናለህ ብለው እንቢ ሲሉኝ ሳልፈልግ ወደ ንግድ ባንክ ተቀላቀልኩ፡፡

ሀትሪክ፡-በቅርቡ ቤትህ ላይ በደረሰ አደጋ የስፖርት ቤተሰቡ በጣም አዝኖ ነበር.. አሁን ምን አይነት ሁኔታ ላይ ነህ?

አዲስ፡- ከቤተሰቤ ጋር በሚገባ አገግመናል እግዚብሔር ይመስገን፡፡ ቤቴን አሰርቼ ገብቻለሁ ባለቤቴና ልጆቼም አገግመውና ረስተውት ህይወት ቀጥሏል፡፡ በጣም አስደንጋጭ ሁኔታ ነበር የነበረው ዳግም በሀገር ደረጃ እንደማይከሰት ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚህ አጋጣሚ አጠገቤ ደብረዘይት ያሉት ጓደኞቼን መላው የኢትዮጰያ ህዝብንም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ያለፈ የታሪኬ አካል ሆኖ አልፏል በጉዳዩ ላይ ከዚህ በላይ ባላወራ ደስ ይለኛል የምፈልገው ሙሉ በሙሉ መርሳት ብቻ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ትዳር ምን ይመስላል…? አባትነትና ባልነት እንዴት ይዞሃል?
አዲስ፡- ደስ ይላል… ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቦቼ ጋር ለማሳለፍ ችያለው በነገራችን ላይ ደብረዘይትኮ ብዙም ቫይረሱ አልገባም ነበር አሁን ነው እየጨመረ የመጣው፤.. ትሬኒንግ ስለምሰራ ሁሌም ነው የምወጣው… ይሄኔም ይዞኝ ለቆኝ ይሆናል /ሳቅ/ አይታወቅም ጉንፋን ነው ብለንም ለቆን ሄዶ ይሆናል፡፡ ስለባለቤቴ መናገር የምፈልገው እወዳታለሁ ሙና አባተ ትባላለች ልጆቼ ሁለት ወንዶች ናቸው ናታኒየም አዲስና ቤሴኒየም አዲስ ይባላሉ፡፡ እንደምወዳቸው መናገር እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የልጆችህ ስሞች ግራ ያጋባሉ ለየት አሉብኝሳ?

አዲስ፡- ትርጉሙን በጣም የምታውቀው እናትየዋ ናት፡፡ ለኔም ወጣ ብሎብኛል በግዴታ ነው የተቀበልኩት፡፡ የግድ ተቀብለን እየኖርን ነው፡፡ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አቀናህ… አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ተከትለህ ነው?

አዲስ፡- አዳማ የነበረኝ ኮንትራት ተጠናቆ ለ1 አመት ለ2013 ለመጫወት ለሀዲያ ሆሳዕና ፈርሜያለው የዚህ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መሆኑ ሁሉን ነገር ቀላል አድርጎታል ከአሰልጣኙ ጋር ከባንክ ተጨዋችነት ዘመኔ የጀመረ ትውውቅ ነው ያለን፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና የተሻለ ደረጃ እንዲኖረው ለማድረግ የምችለው አቅም አወጣለሁ ብዬ አስባለው፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ልምድ ስላለኝ ከአዳማ ከኔ ጋር ከሄዱት በርካታ ተጨዋቾች እና ከሌሎቹ የቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ከአሰልጣኙ የሚሰጠኝን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ 10 የሚጠጉ ተጨዋቾች ከአዳማ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ተጉዛችኋል… እንዲህ ገጥሞህ ያውቃል?
አዲስ፡- ብዙ ጊዜ አይገጥምም፡፡ አሰልጣኙ ግን ማድረግ ያለበትን ለማድረግ የሚፈልገውን ተጨዋች ሰብስቧል፡፡ ያም ቢሆን በቡድኑ ውስጥ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ሀድያ ሆሳዕና ጥሩ ተፎካካሪ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

📸 Mandatory Credit: Photo Hossana sport page

ሀትሪክ፡-አዳማ እናንተን ከሚያሰናብትና ሌሎችን ከሚያስፈርም ቢያቆያችሁ አይሻ ለውም ነበር?

አዲስ፡- ብሩን ከየት አምጥተው ሊከፍሉ? የላቸውምኮ… ወጣቶች ላይ አተኩሮ ከታች አሳድጎ ካልሆነ በስተቀር የሚከፍለው ብር የለውም፡፡

ሀትሪክ፡-ለ14 አመታት እግር ኳስ ተጫውተሃል… ህይወትህ ከኳስ ጋር ተቆራኝቷልና… ስለዚህ ምን ማለት ይቻላል?

አዲስ፡- እግር ኳስኮ ለኔ ህይወቴ ነው ዋናና ብቸኛውም ስራዬ እግር ኳስ በመሆኑም ደስተኛ ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ስራ ሰጥቶኛል፡፡ ኑሮዬን መራሁበት ራሴን ቤተሰቦቼን ትዳሬን አስተዳደርኩበት እግዚአብሔር በሰጠኝ ስራዬ ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-በተቃራኒነት ለተደጋጋሚ ጊዜያት ተፋልሞህ ያስቸገረህ ተጨዋች አለ?

አዲስ፡- በጣም ያስቸገረኝ ተጨዋች አለ ብዬ አላስብም፤ በተደጋጋሚ የማስታውሰውም የለም… አንዳንዴ ግን በጨዋታ ላይ ብቻ ይሆንና ማስታወስ አልችልም ጨዋታው ካለቀ በኋላ ወዲያው ስለምረሳው በዚህ ደረጃ ያስቸገረኝን አላውቅም በተቃራኒው ግን በክለብ ደረጃ አብሬው ያልተጫወትኩት ሽመልስ በቀለን ነው ከርሱ ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ለሱዳኑ አልአህሊ ሸንዲ ተጫውተሃልና? ስንት አመት ተጫውትክ ቆይታህስ ምን ይመስላል?

አዲስ፡- ወደ 3 አመት አካባቢ ለአልአህሊ ሸንዲ ተጫውቻለሁ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ፡፡ መምጣት ሳይገባኝ በራሴ ውሳኔ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ ደመወዜ ወደ 3 ወር አካባቢ ባለመከፈሉ ነው ጥዬ የመጣሁት፡፡ ቆይ ቆይ ሲሉኝ አናደውኝ ጥዬ መጣሁ፡፡ 2 አመት ጨርሼ ለሌላ 2 አመት ውሌን አድሼ ግማሽ ብር ወስጄ ነው የመጣሁት… አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር አብረን ሰርተናል ሲመጣ በምክትል አሰልጣኝነት ሲሆን በኋላ ላይ ምክትሉ ሲነሳ ዋና አሰልጣኝ አድርገውት በዋና አሰልጣኝነት ሰርቷል ሊጉ ፕሮፌሽናል በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት ሊግ ነው፤ የኃይል አጨዋወት ይበዛበታል፡፡ እዚያ ሊጉ ጠንካራ ነው ጨዋታ ያለው ግን እዚህ ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን አልአህሊ ሸንዲ ጋር የነበረኝ ጊዜ ጥሩ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ከአልአህሊ ሸንዲ ወደ አዳማ ከተማ ነው የተዛወርከው ደመወዝ ከማይከፍል የውጪ ክለብ ደመወዝ ወደ ማይከፍል የሀገር ውስጥ ክለብ ዝውውር አደረክ ማለት ይቻላል?

አዲስ፡- /ሳቅ/ አዳማም እውነት ነው የ2 ወር ደመወዝ አልከፈለንም ገጠመኙ ይገርማል የ2011 ግንቦት ሰኔ ደመወዝ አልተከፈለንም የ2012 የ2 ወር ክፍያ በድጋሚ አለበት፡፡ ድሃ ይበላዋል እንጂ አይቀርም መክፈላቸው የግድ ነው አንድ ሰው ቀጥሬ ተሯሩጦ አስጨርሶ ይብላ እንጂ ታፍኖ አይቀርም፡፡ በሰዓቱ አይሰጡም… ለዚህ ነው ክፍያው እንደበፊቱ ቢሆን ጥሩ ነው የምለው የከነማ ቡድኖች በወር የሚያወጡት ብዙ መሆኑ ነው የጎዳቸው… በድሮ ቢሆን አንዴ ይከፍላል በቃ በወር 2 ሺህ ብር ወደ 24 ወር ብንመታው 50 ሺህ ብር አካባቢ ቢሆን ነው አይከብድም ነበር…አሁን ግን ለ1 ተጨዋች ወደ 100 ሺህ ብር እየከፈሉ ያ ሁሉ ተጨዋች የሚከፈለው የትየሌለ ነው ያ ነው የከበዳቸው… የቅዱስ ጊዮርጊስ ነገር ይመቸኛል ለተጨዋች አሪፍ አካሄድ ነው አንዴ ሰጥቶ ደመወዝ 10 ሺ ብር ይከፍልሃል ያ ነው ህይወትህን የሚቀይረው… ስፖርተኛም እንዳይወድቅ የሚያደርገው ያ ነው… ደመወዝህኮ በወር በወር ቢመጣ ታጠፋዋለህ የቤት ወጪ የአስቤዛ የነዳጅ የልብስ ስትል ያልቃል በፊት በነበረው አካሄድ ቢቀጥል መፍትሔ አለው ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ በኔ ነገር ላይ ጠጠር ወርወር አድርገንዋል ከጎኔ ነበሩ ለምትላቸው ሰዎች የምትለው ካለ?

አዲስ፡- የቅድሚያ ምስጋናዬ ለእግዚአብሔር ነው ትልቁ ምስጋና ለራሱ ይድረሰው ከዚያ ባለቤቴና ልጆቼ ቤተሰቦቼ አብረውኝ ከጎኔ ለነበሩና አሁንም ላሉ ጓደኞቼ በአጠቃላይ ለረዱኝ ላገዙኝ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡


አዲስ ሕንፃ /ሀድያ ሆሳዕና/
ስለ አባይ ግድብ

እስከዛሬ ድረስ ይህን አለማየታችን ያበሳጫል፤ በመጀመሪያ በግድቡ የውሃ ሙሌት ዜና ተደስቻለሁ፡፡ ይህንንም በማየታችን እድለኞች ነን የግብፅ ጉዳይን ስናየው ብዙም አላሳሰበኝም ባለስልጣናትና ባለሙያዎቹ ሁሉንም ነገሮች ያወቁታል፡፡ የኛዎቹም ለዚህ ነው ደረታቸውን ነፍተው ሳይፈሩ የውሃ ሙሌቱ የተካሄደው፡፡ ለፍፃሜውም ህብረሰተሰቡ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ማድረግ አለበት ማለት እፈልጋለው፡፡ በግሌ ከአንዴም ሁለቴ በክለብና በብሔራዊ ደረጃ ቦንድ በመግዛት ያለኝን ድጋፍ ገልጫለሁ የሚጠበቅብኝን በማድረጌ ደግሞ ደስተኛ ነኝ፡፡
ስለ ኮሮና ቫይረስ

ከኮቪድ 19 ለማምለጥ ራሳችንን መጠበቅ ይገባል ዋናው ግን እግዚአብሔር በሽታውን ከሀገራችን ያጥፋልን ማለት ነው የምችለው… በትንፋሽ ይባላል ጉንፋን ሆነኮ… በመነካካት ይባላል ግራ ያጋባል እግዚአብሔር ካላጠፋልን በስተቀር ለኛ ከባድ ይመስለኛል፡፡ የኛ ማህበረሰብ ሁሌ መሳሳም መጨባበጥ ነው ትልቅ ችግር ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ክፉ በሽታ ለማምለጥ ከእግዚአብሔር ጋር ጥንቃቄ ያስፈልጋል ማክስ ማድረግን ጨምሮ የተሰጡትን መከላከያዎች መጠቀም የግድ ያስፈልጋል ዋናው ግን እግዚአብሔር ከሀገራችን ያጥፋልን ማለት ነው የምፈልገው፡፡
“በኢትዮጵያ ቡና ቀሪ ውል አለኝ ክለቡን

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport