በሚሊዮን ሀይሌ እና በቅዱስ ይምሩ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ላይ ደርሷል እኛ ዳግሞ በዚህ ሳምንት የተመለከትናቸው ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
የመጀመሪያው ተሰናባች አሰልጣኝ
ወላይታ ድቻ በይፋ ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር ተለያይቷል። በዚህ አመት ወላይታ ድቻ አሰልጣኙን በውጤት ማጣት ካሰናበቱ ክለቦች ቀዳሚው ሆኗል።

ድሎች
ከአሰልጣኙ ስንብት በኋላ ወላይታ ድቻ ወደ ጅማ አቅንቶ ጅማ አባ ጅፋርን በማሸነፍ ሶስት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል። ድቻ ያስመዘገበውን ድል ተከትሎ በዘጠኝ ነጥብ አስራ ሶስተኛ ደረጃ መቀመት ችላሏል።
በዚህ ሳምንት ከተደረጉት ጨዋታዎች ሁለም በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ሲሆን የሀድያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ብቻ በአቻ ውጤት ተጠናቋል በአንፃሩ ባህርዳር እና ወልዋሎ ያደረጉት ጨዋታ በርካታ ግቦች የተስተናገዱበት ነበር።
መቐለ 70 እንደርታ አሁንም በአልሸነፍ ባይነቱ የቀጠለበትን ድል ሰበታ ላይ ሲያስመዘግብ ሀድያ ሆሳዕና ከተከታታይ ድል በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ነጥብ ተጋርቷል።
ጎሎች
በዚህ ሳምንት በጠቅላላ 25 ግቦች ተቆጥረዋል ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠሩ ግቦች መሀከል በሶስት ከፍ ብሏል።
23 ተጫዋቾች ግቦች ሲያስቆጥሩ ኦኪኪ አፎላቢ እና ወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ ሁለት ሁለት ግቦች ከመረብ ላይ ሲያሳርፉ ቀሪዎቹ ግን በተለያዩ ተጫዋቾች የተቆጠሩ ናቸው።
የአዳማ ከተማው መናፍ ዐወል ከድሬዳዋ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በ6ኛው ደቂቃ በራሱ መረብ ላይ ያሳረፋት ግብ የዚህ ሳምንት ፈጣኗ ጎል ስትሆን። ሁለት ግቦች በራስ መረብ ላይ ሲቆጠሩ በፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ እንዳለ ደባልቄ ሲዳማ ቡና ላይ ያስቆጠራት ብቸኛዋ ግብ ሆና ስታልፍ አብዱለጢፍ መሀመድ ፋሲል ላይ በ90ኛው ደቂቃ ያገባት ግብ ደግሞ በዚህ ሳምንት ዘግይታ የተቆጠረች ናት።
150ኛ የፕሪምየር ሊጉ ግብ አስቆጣሪ !
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረ እስካሁን በጠቅላላ 166 ግቦች ተቆጥረዋል። የቀድሞው የድሬዳዋ ከነማው አጥቂ ናሚቢያዊው ኢታሙናይ ኬይሙኒ ቡድኑ ወልዋሎ ባህርዳርን ሲገጥም 26ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል የሊጉ 150ኛው ግብ አስቆጣሪ አድርጎታል።

የማስጠንቀቂያ ካርዶች !
ሊጉ ዘጠነኛው ሳምንት ላይ ሲደርስ ባለፉት ስምንት የሊጉ መርሀ ግብሮች ላይ 230 የማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርዶች ሲመዘዙ ስምንት የቀይ ካርዶች ታይተዋል ::
ይህም በ 2010 የውድድር አመት በአጠቃላይ በ 15 ሳምንታት ከተመዘገበው 443 ቢጫ ካርዶችና እንዲሁም 25 ቀይ ካርዶች በግማሽ አንሶ ይገኛል ::
ክለቦች እና ማስጠንቀቂያዎቻቸው
ክለቦች እያስመዘጉበት ያሉትን ውቅታዊ ውጤት በማድረግ በውጤቱ ላይ ተፅእኖ አላቸው የሚሏቸውን አሰልጣኞች እና ተጫዋቾችን ከወዲሁ ማስጠንቀቅ ጀምረዋል። ወልዋሎ ደግሞ ለ13 ተጫዋቾች ማስጠንቀቅያ በመስጠት ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል::
አሰልጣኙን ጨምሮ ለአምስት ተጫዋቾች ያስጠነቀቀው ድሬዳዋ ይከተለዋል። ከአሰልጣኙ ጋር በቅርቡ የተለያዩት ወላይታ ድቻ፣ወልቂጤ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ለተጫዋቾቻቸው ማስጠንቀቂያ ከሰጡ ክለቦች መካከል ናቸው።
በደሞዝ ክፍያ እየታመሱ የሚገኙ ክለቦቻችን
ክለቦቻችን ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተጫዋቾች ልምምድ እንዲያቆሙ ምክንያት እየሆነ ይገኛል። ከዚህ የተነሳ በዚህ ሳምን ጨዋታቸውን እንደሚያከናውኑ ጥርጥር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸውም ክለቦች ነበሩ፡፡
ከነዚህም መካከል ባህርዳር ከተማ ጨዋታው ሁለት ቀን ሲቀረው ልምምድ የጀመሩ ሲሆን አዳማ ከተማዎች ደግሞ ጨዋታው በሚደረገበት ቀን ወደ ድሬዳዋ አቅንተው ልምምድ ሳያከናውኑ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ከዚህ ቀደም ጅማ አባ ጅፋር ተመሳሳይ ችግር ተከስቶበች እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም።
አስተያየት ይስጡ