በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሳይደረግ በይደር የቆየው የወልዲያ ከተማና መከላከያ ጨዋታ ዛሬ በወልዲያ ሼህ ሙሀመድ አሊ አላሙዲን ስታዲዬም ተደርጎ ጨዋታው በባለሜዳዎቹ ወልዲያዎች 2ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ወራጂቀጠናውን አዞዎቹ ተረክበዋል፡፡
መከላከያ የሊጉን የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ሲያደርግ ወልዲያ ከተማ ቀሪ 2 ተስተካካይ ጨዋታ ከደደቢት እና ወላይታዲቻ እያለው 13ኛ የሊጉን ጨዋታ አከናውኗል፡፡
ወልዲያ ከተማ ከኢትዮ ኢለክትሪክ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ 11 ስብስብ ብርሃኔ አንለይና ኤዶም ኮዲዞን በመቀየር ነጋ በላይና ሙሉቀን አከለን በመጀመሪያ አሰላለፍ ሲያስካትቱ ፡እንግዳው ቡድን መከላከያ፡ በአዲስ አበባ ስታዲዬም መቀለ ከተማን 1ለ0 ሲያሸንፍ ጎሏን ያስቆጠረው ምንይሉ ወንድሙን፡ በአቅሌሲያ ግርማ በመቀየር በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተዋል፡፡
ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመሃል ዳኝነት በመሩት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሺ ጥሩ በተንቀሳቀሱበት፡ኳስን መስርተው ግብ ለማስቆጠር በሞከሩበት እና ፍፁም የጨዋታ የበላይነት በተመለከትንበት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ፡ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ ባለሜዳዎቹ ቀዳሚም የተሻሉም ነበሩ፡፡
በአንፃሩ መከላከያዎች ከ30ኛው ደቂቃ በሇላ የጨዋታውን ሚዛን በማስጠበቅ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የአጥቂ ክፍሉ የግብ ዕድል በመፍጠር በኩል ተዳክሞ የተስተዋለበት ፡የመከላከያ የአጥቂ ክፍል ያለ ምንይሉ ወንድሙ እጅጉን እንደሚቸገር የተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ የተጠናቀቀ ሲሆን
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ እንደመጀመሪው አጋማሽ ኳስን መስርተው በመጫወት የጨዋታውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ በተደጋጋሚ ግብ ለማስቆጠር ወደ መከላከያ የግብ ክልል በመግባት ሲያደርጉት በነበረው ጥረት ወልዲያዎች በ61ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ቢያድግልኝ ኤሊያስ በግንባሩ ወደ ግብ ሲሞክረው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ኳሷን ለማውጣት ሲሞክር የተጨረፈችውን ኳስ አንዷለም ንጉሴ (አቤጋ) ከመረብ ጋር በማገናኘት ወልዲያ ከተማ 1ለ0 መምራት የጀመሩበትን ጎል አስቆጠረ፡፡
መከላከያዎች ከጎሏ መቆጠር በሇላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በመስመር በኩል ረጃጂም ኳሶች በማሻገር የግብ ዕድል ለመፍጠር ያደረጉት ድካም ፍሬ ሳያፈራ ወልዲያዎች፡ በ81ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ቡሩክ ቃልቦሬ በግንባሩ ሲጨርፈው አጠገቡ የነበረው ብርሃኔ አንለይ በጥሩ አጨራረስ ቡድኑ መከላከያን 2ለ0 ያሸነፈበትን ውጤት እንዲመዘገብ ጎሏን አስቆጠረ፡፡
መከላከያ የሊጉን የመጀመሪያ ዙር የጨዋታ መርሃ ግብር በ15 ጨዋታ፡2 አሸንፎ: በ7 አቻ ሲለያይ ፡በ6 ጨዋታ ተሸንፎ በ15ነጥብና በ8 የግብ ዕዳ በደረጃ ሰንጠረዡ በ13ኛነት አጠናቋል፡፡
ወልዲያ ከተማ የዛሬውን ድል ተከትሎ በ13 ጨዋታ በ15 ነጥብና በ1 የግብ ዕዳ ወራጂ ቀጠናውን ለአርባ ምንጭ አስረክቦ በደረጃ ሰንጠረዡ ከ16ኛነት ወደ 12ኛ ከፍ ብሏል፡፡