በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከሊቪያው አልሀሊ ትሪፖሊው የነገ ጨዋታ በፊት ወልዋሎ ልምምዱን አከናውኗል።

ኢትዮጵያን በመወከል በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ እየተካፈለ የሚገኘው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ የማጣሪያ መርሀግብሩ የሱዳኑን ሂላል አልሳህልን በደርሶ መልስ በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፉን ያረጋገጠ ሲሆን የሊቪያውን አልሀሊ ትሪፖሊን በደርሶ መልስ ያስተናግዳል። እዚሁ ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ነገ ጥቅምት 6/2019 እንደሚደረግ ቀደም ብሎ መርሀግብር ቢያዝልም ወልዋሎ በአሁኑ ሰዓት በገጠመው የፋይናንስ ችግር ምክንያት ተጋጣሚው አልሀሊ ትሪፖሊ ለክለቡ ሙሉ ወጪውን ከመሸፈን ባለፈ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ተከትሎ ከሜዳው ውጪ ሊቢያ ላይ ሁለቱንም የደርሶ መልስ ጨዋታ ለማድረግ በመወሰኑ ነገ ዕርብ የመጀመሪያ ጨዋታውን በትሪፖሊ ስታዲየም ምሽት 2 ሰዓት ሲል ያከናውናል።

18 ተጫዋቾችን ጨምሮ በድምሩ ወደ 58 የሚደርሱ የልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ በግብፅ አድርጎ ከረጅም ጉዞ በኋላ ትላንት ሊቪያ የደረሰው የወልዋሎ የቡድን አባላት በዛሬው ዕለት የመጨረሻ ልምምዳቸውን መስራት የቻሉ ሲሆን ከአርባምንጭ ከተማ ክለቡን የተቀላቀለው ሴኔጋላዊው አማካይ ማማዱ ሴክ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። ነገ የመጀመሪያ ጨዋታው በዛው ትሪፖሊ ከተደረገ በኋላ የመልሱ ጨዋታ ጥቅምት 13/2019 በዛው ሊቪያ ያከናውናሉ።

አስተያየት ይስጡ