ለአለም ዋንጫ ማጣርያ እየተዘጋጁ ያሉት የዋሊያዎቹ አራት አባላት ዛሬ ጠዋት ከቡድኑ ተባረዋል።
ዋሊያዎቹ ትላንት ኡጋንዳን 2ለ1 በረቱበት ጨዋታ ምሽት ሊዝናኑ ወጥተው 5.30 ድረስ ባለመመለሳቸው የፋሲል ከነማዎቹ ሱራፌል ዳኛቸውና በዛብህ መለዮ፣ የኢትዮጵያ ቡናው ዊሊያም ሰለሞንና የባህርዳር ከተማው ፍጹም አለሙ ዛሬ ጠዋት ከቁርስ በኋላ ከቡድኑ ስብስብ መባረራቸው ታውቋል።
እንደ ሀገር ትልቅ አደራ ያለባቸውና ከጋና ጋር ለወሳኝ ጨዋታ የተዘጋጁት የዋሊያዎቹ አራቱ ተጨዋቾች ድርጊት አሳዛኝ ሆኗል።
ለአራቱም ተጨዋቾች ይቅርታ አንዲደረግላቸው አምበሉ ጌታነህ ከበደ ያደረገውም ጥረት በዲሲፕሊን በማይደራደሩትና ይህንንም ደጋግመው ባሳዩት አሰልጣኝ ውበቱ ጠንካራ ቁጣ ሳይሳካ ቀርቷል።
ከብሄራዊ ቡድኑ ካምፕ ታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ አሰልጣኙ “ዲሲፕሊን የማይከበር ከሆነ ማንም ይሁን ማን ይባረራል” ሲሉ ዝተዋል።
እንደ አንዳንድ መረጃዎች ሌሎች የቡድኑ አባላትም ውጪ ማምሸታቸው ባይነቃም በተለይ አሰልጣኙ ለአፍሪካ ዋንጫ የእጣ ማውጣት ስነስርአት ካሜሩን እያሉ እየወጡ ያመሹ እንደነበርም ታውቋል።
በመጪው እሁድ ወደ አክራ የሚያቀኑት ዋሊያዎቹ ውስጥ መከፋፈል እንዳይፈጠር የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ጠንካራ ስራ ይጠበቅባቸዋል።
ከአራቱ ተጨዋቾች ውጪ ሌሎቹ የቡድኑ አባላት በአሁኑ ወቅት ከባህር ዳር አዲስ አበባ ጁፒተር ሆቴል መግባታቸው ታውቋል።
አስተያየት ይስጡ