”የተለየ ክብደት የምንሰጠው ቡድን አይኖርም” አሰልጣኝ ዉበቱ አባተ
”ጠንካራ የሚባል ቡድን አለን ” ጌታነህ ከበደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ ነገ ምሽት 4፡00 ላይ ኢትዮጵያ ከኬፕ ቨርድ ከምታደርገው ጨዋታ ቀደም ብሎ ዛሬ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሀሳባቸውን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አካፍለዋል።
- ማሰታውቂያ -
ወደ ካሜሩን ለመድረስ የመጀመርያው ቡድን መሆናቸውን በመግለፅ መግለጫቸውን የጀመሩት አሰልጣኝ ውበቱ ከሶስት አፍሪካ ዋንጫዎች በኋላ ወደ መድረኩ በመመለስ ጥሩ ቡድን ይዘው ለመቅረብ እና ማንነታቸውን ለማሳየት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ውድድሩ እንደመመለሳቸው አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ዘንድሮ ለሚተገበረው ቪኤአር ቴክኖሎጂ አዲስ ቢሆኑም ያን ያህል ልዩነት እንደማይፈጥርም ተናግረዋል።
ስለተሰጣቸው ግምት ?
” ሁሉም ሰው ለኛ አነስተኛ ግምት ነው የሰጠን። የፊፋ ደረጃ ላይ ያለን ቦታ ዝቅተኛ ነው። ደረጃው ግን ያለንበትን ሁኔታ አመላካች ነው ለማለት ይከብዳል። ሁላችንም እንደምናውቀው ተጋጣሚዎቻችን ጠንካሮች እና በጥሩ ተጫዋቾች የተዋቀሩ ናቸው። ሆኖም እኛም ለመፎካከር እና ያለንን ነገር ለማሳየት ተዘጋጅተናል። ማንም ባይጠብቀንም ጥሩ ነገር ለማሳየት ዝግጁ ነን። በማጣርያው ላይ ቡድናችንን ተመልክታችሁታል። እንደከዚህ ቀደሙ አይነት ቡድን አይደለም ያለን።
ስለ አዘጋጇ ካሜሩን ?
” ይህን በጥሩም ሆነ ጥሩ ባልሆነ ጎኑ መመልከት እፈልጋለሁ። ካሜሩን ጠንካራ ቡድን መሆኑን እና በሀገሩ እና በደጋፊው ፊት እንደሚጫወት እናውቃለን። ይህ ለእነሱ ጠቃሚ ነው። በሌላ ጎኑ ስናየው ደሞ ለነሱ ጫና የሚፈጥር እና እኛን ከጫና ነፃ እንድንሆን የሚያደርግ በመሆኑ ለኛ ጠቃሚ ነው።”
ስለ ዕቅዳቸዉ ?
”ለህጉራችን እና ለዓለም ምን እንዳለን ለማሳየት ተዘጋጅተናል። በርካታ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች አሉን። ይህን ለእግርኳሱ ዓለም ማስተዋወቅ አለብን። በሌላ በኩል ሌሎቹ ቡድኖች ልምድ አላቸው። ግን የተለየ ነገር ለማሳየት እና ሰርፕራይዝ ቡድን ለመሆን ተዘጋጅተናል። ‘ በማለት አላማቸውን ገልፀዋል።
ስለ ነገዉ የኬፕ ቨርዲ ጨዋታ ?
” የነገው የመጀመርያ ጨዋታ ነው። ስለዚህ ሁለቱም ቡድኖች እኩል እድል አላቸው። እነሱ ጠንካሮች ቢሆኑም እኛም የተሻለ ነገር ለማሳየት ዝግጁ ነን። ምድቡን በተመለከተ ቡድኖቹ ጠንካራ ናቸው፤ እናከብራቸዋለን። የተለየ ክብደት የምንሰጠው ቡድን ግን አይኖርም። ይህ እግር ኳስ ነዉ። ”
ስለ ዝግጅታቸው እና የካሜሩን ቆይታቸው ?
” ሳኡዲ አረቢያ ነበር ሀሳባችን ፤ ግን በነበረው የጉዞ ክልከላ ምክንያት ወደ ካሜሩን መጥተናል። እኛ ከመምጣታችን በፊት ብዙዎች የአፍሪካ ዋንጫ ላይካሄድ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበራቸው። እኛ ካሜሩን በቅድሚያ መድረሳችን ግን ውድድሩ እንደሚካሄድ አመላካች ሆነናል። ከዚህ ባሻገር እዚህ ቶሎ በመምጣታችን ተጠቅመናል። የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ እንድንችል እንዲሁም ሁላችንም በአንድ ቦታ ተሰባስበን ከኮቪድ እና መሰል ችግሮች እንድንርቅ አድርጎናል። ”
” እዚህ እንደመጣን በኮቪድ ተቸግረን ነበር። አምስት እና ስድስት የሚሆኑ ተጫዋቾች ለቀናት ልምምድ መሥራት አልቻሉም ነበር። አሁን ላይ ሁሉም ተጫዋቾች ነፃ መሆናቸው ለእኛ መልካም ዜና ነው። በጉዳት ረገድ ሽመልስ በቀለ እና ዳዋ ሆቴሳ በሀርምስተሪንግ እና የቁርጭምጭሚት ጉዳት ለነገው ጨዋታ መድረሳቸው አጠራጣሪ ከመሆኑ በቀር ሌሎቹ በጥሩ ጤንነት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር አብሮ መግለጫው ላይ የተገኘው አምበሉ ጌነህ ከበደ ደግሞ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል:-
” በማጣርያው ከነ ጋና ጋር ከመጫወታችን በፊት በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከአይቮሪኮስት ጋር ጥሩ ነገር አሳይተናል። የተሻልን ነበርን። ውጤቱ ባይገልፀውም ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር።” ሲልም ቡድናቸው ጠንካራ እንደሆነ ተናግሯል።
©EFF