“በደብዳቤ ጋጋታ አልበረግግም፤ የወከሉኝን የሙያ ጓደኞቼን መብት ለማስከበር እስከመጨረሻው እታገላለሁ”አቶ ሰለሞን አባተ

ኢንስ. ሰውነትን ከሰብሳቢነት ለማንሳት፣ አቶ ሰለሞንን ለማገድና ቴክኒክ ኮሚቴውን ለማፍረስ ታስቧል

በደብዳቤ ጋጋታ አልበረግግም፤ የወከሉኝን የሙያ ጓደኞቼን መብት ለማስከበር እስከመጨረሻው እታገላለሁ”
አቶ ሰለሞን አባተ

ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ስለማንሣትም ሆነ ቴክኒክ ኮሚቴውን ስለመበተን የታሰበ ነገር የለም”
አቶ ባህሩ ጥላሁን


በይስሐቅ በላይ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በቴክኒክ ኮሚቴው መካከል በአሁን ሰዓት ጥሩ የሠላም አየር እየነፈሰ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውጤታማው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራው የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ያቀረበውን ባለ ዘጠኝ ነጥብ ምክረ ሃሳብ “አስተዳደራዊ ነገር ይበዛዋል” በሚል ውድቅ ካደረገው በኋላ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ሰፍቷል፡፡
እስከአሁን ባለው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቴክኒክ ኮሚቴው ምንም አይነት ድጋፍ እያገኘ እንዳልሆነና በቴክኒክ ኮሚቴው ምትክ ሌሎች አካላት የብ/ቡድን ዝግጅት እንዲገመግሙ መደረጉ ነው የተሰማው፡፡

ተጨባጭ ማስረጃ ያልተገኘባቸውና ብዙ ማጣራት የሚፈልጉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ደግሞ አሁን ያለውን የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ከሰብሳቢነት በማንሣት ሌላ ስራ አስፈፃሚን በእሣቸው ምትክ በሰብሳቢነት የማስቀመጥ እንዲሁም ላለፉት 10 አመታት የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴውን በቅንነት ያለ አንዳች ክፍያ ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ሰለሞን አባተን በዚሁ ጋዜጣ ላይ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ተንተርሶ የዲሲፕሊን ግድፈት ፈፅመዋል በሚል ከአባልነትና ከስፖርታዊ እንቅቃሴ ለማገድ ከዚህ በተጨማሪም የቴክኒክ ኮሚቴውን አባላት ከተሳካ ራሣቸው ሪዛይን እንዲያደርጉ ይሄ ካልሆነ ደግሞ የተለያየ ምክንያት በመደርደር ለማፍረስ እንደታቀደ አንዳንድ ሾልከው የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለያየ መንገድ ለማጣራት ሞክረን ማስረጃ ያጣንባቸው ነገር ግን በወሬ ደረጃ በስፋት እንደሚናፈሰው ወሬ ከሆነ ከ31 አመት በኋላ ብ/ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ባሳለፉት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራውን የቴክኒክ ኮሚቴን በምክንያት በመበተን የአዲሱ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ለመሆን አንድ ቡድን ተመራርጦ መጨረሱን እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የዜና ምንጮቻችን በተለይ ለሀትሪክ እንደጠቆሙት አሁን ያለው የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲበተን የተለያየ የማግባባትና ግፊት የማድረግ ስራን ሲሰሩ የነበሩ ወገኖች ቦታውን ለመቀራመት እንዳሰፈሰፉና ቃል እንደተገባላቸው ነው የተሰማው፡፡

ከአሰልጣኝነት እስከ ኢንስትራክተርነት እስከ ዶክተርነት ብሎም እስከ ከፍተኛ ምሁርነት የበቁ ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው የሚመራው ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሱ ማንዋል እና የስልጠና ሲለበስ እንዲኖረው በማዘጋጀትና የታዳጊዎችና የወጣቶች ስልጠና እንዲኖር ያለፈው የቴክኒክ ኮሚቴ በተቀነባበረ ድራማ ተበትኖ ሌላ የተደራጀ ቡድን እንዲገባ መደረጉ ሌላ ያልታሰበ ቁጣን እንዳይቀሰቅስ ስጋት እንዳላቸው በጉዳዩ ዙሪያ ያናገርናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪዎች የገለፁ ሲሆን የሚያስፈልገው አሁን ያለውን የምሁሮችና በስፖርቱ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ያላቸውን የቴክኒክ ኮሚቴውን ስብስብ ማፍረስ ሣይሆን ተቀራርቦ የተሻለ ስራን መስራትን ማስቀደም ይመረጣል፤ ከዚህ ውጪ የሚደረግ ነገር የታሪክ ተጠያቂነትን ያስከትላል” በማለት ያላቸውን ስጋት በተለይ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡

ይህንን ስጋት ተከትሎ እውነታውን ለማጣራት “በእርግጥ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ከብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢነት ሊነሱ? አቶ ሰለሞን አባተስ በሰጡት አስተያየት ሊታገዱ? የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴውስ ፈርሶ በሌላ በተደራጀ ቡድን ሊተካ? በሚል በማከታተል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን “ይሄ ተራ አሉባልታ ነው፤ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ከሰብሳቢነት ለማንሣትና ቴክኒክ ኮሚቴውን ለማፍረስ የተደረገ ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም፤ የአቶ ሰለሞን አባተን ጉዳይ በተመለከተ ጉዳዩ ወደ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ተመርቷል፤ ከዚህ ውጪ የነበረውን የቴክኒክ ኮሚቴ አፍርሶ አዲስ ለማቋቋም ኢንስትራክተር ሰውነትን ስለማንሣት የታሰበ ነገር የለም” በማለት ወሬው ሀሰት መሆኑን የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን በስልክ አነጋግረናቸው በሰጡን ምላሸ አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ ከፌዴሬሽኑና የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ጉዳይ ሳንወጣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቀን 03/02/2013 በቁጥር 2/ኢ.እ.ፌ.ኢ3/1842 ለዲሲፕሊን ኮሜቴው በጽ/ቤት ኃላፊው በአቶ ባህሩ ጥላሁን ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ 1ኛ ከሳሽ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 2ኛ ተከሳሽ አቶ ሰለሞን አባተ በሚል በፌዴሬሽኑ እና በአመራሩ ላይ የተፈፀመ ድርጊትን በሚል የክስ አቤቱታ አቅርቧል፡፡
ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሰለሞን አባተ በሀትሪክ ጋዜጣ በቁጥር 655 ቅዳሜ መስከረም 23/2013 ዓ.ም በነበራቸው ቃለ ምልልስ ለፌዴሬሽኑ፣ ለብሔራዊ ቡድኑ፣ ለፕሬዚዳንቱ የማይመጥን ክብረ ነክ የሆነ የእግር ኳስ ስፖርት ቤተሰቡ ፌዴሬሽኑ እሣት እንደሆነ እንዲያስብና በፌዴሬሽኑ ላይ ያለውን በአጠቃላይ መልካም እይታ ግንዛቤ ጥላሸት የሚቀባ ድርጊት ፈፅመዋል፤ በሚል በአቶ ሰለሞን አባተ ላይ ክስ አቅርቦባቸዋል ክሱ የቀረበለት የዲሲፒሊን ኮሚቴው” ለቀረበብዎት የዲሲፒሊን ክስ ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጡ” በሚል መጥሪያ ለአቶ ሰለሞን አባተ ባሉበት የላከላቸው ሲሆን “በቀረበብዎ ክስ አለኝ የሚሉትን ምላሽ መጥሪያው ከደረስዎት ቀን ጀምሮ ባሉት 10 ተከታታይ ቀናት በአማርኛ ቅጅ ምላሽ እንዲሰጡ” የሚል ሀረግም በመጥሪያው ላይ አስቀምጧል፡፡

ፌዴሬሽኑ ያቀረበባቸውን ክስና የዲሲፒሊን ኮሚቴው የላከላቸውን መጥሪያ ተከትሎ አስተያየት እንዲሰጥ የተጠየቀው የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው አባል አቶ ሰለሞን አባተ “የዲሲፒሊን ኮሚቴ ደብዳቤ ደርሶኝ በጣም ተገርሚያለሁ፤ ላለፉት 10 አመታት አንዳችም ክፍያ ሳይፈፀምልኝ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል የሀገሬን እግር ኳስ በሙያዬ ለማገዝ የበኩሌን አሻራ ለማስቀመጥ ደፋ ቀና በማለት ማሳለፌ ከግምት ውስጥ ገብቶ ሽልማት ወይም ምስጋና ሊቸረኝ ሲገባ በዚህ ደረጃ እኔን ተጠያቂ ለማድረግ መሞከሩ በጣም አስገርሞኛል” ያለው የቴክኒክ ኮሚቴው አባል “የወከሉኝን የሙያተኞች መብት ለማስከበር የሙያተኞች ድምፅ ሆኜ የሀገራችን ሕገ መንግሥት ባጎናፀፈን የመናገር ነፃነት ተጠቅሜ አስተያየት መስጠቴ ሌላ ትርጉም መሰጠቱ ከልብ እንዳዝን አድርጎኛል፤ የተከበሩ የሀገር መሪዎች ሳይቀሩ የትችት ናዳ ሲወርድባቸው ከመወንጀል ይልቅ የህዝቡን የመናገር ነፃነት አክብረው በሚኖሩባት ሀገራችን ለእግር ኳሱ ይጠቅማል፤ ለዕርምት ይረዳል የባለሙያዎች ድምፅ ይከበር በሚል የሰጠሁትን አስተያየት ትችትና ጥቆማ የመናገር ነፃነትን በሚያፍን ሌሎች ሙያተኞችን በሚያሸማቅቅ መልኩ ተተርጉሞ ለሌላ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከሩን ከልብ አሳዝኖኛል” ብሏል፡፡
“በእርግጥ የደብዳቤ ጋጋታ አያስበረግገኝም፤ እኔ አድርባይ አይደለሁም፤ አሁንም ቢሆን ድምፃቸውን እንዳሰማ የወከሉኝን ሙያተኞች መብት ለማስከበር እስከ መጨረሻው መታገሌን እቀጥላለሁ” ያለው አቶ ሰለሞን አባተ “የብ/ቡድን ተጫዋቾች ዳሌ አውጥተዋል፤ ወፍረዋል” በሚል የሰጠው አስተያየትን ተከትሎ “ተጨዋቾች ከመደበኛ እንቅስቃሴ (Active) በሆኑና ከእንቅስቃሴ ውጪ (Inactive) ሲሆኑ አንድ ነው? በማለት ጥያቄውን በጥያቄ የመለሰው አቶ ሰለሞን “ተጫዋቾች ከመደበኛ እንቅስቃሴ ያውም ለ7 ወር ሲርቁ በሰውነታቸው በተለይ በዳሌያቸውና (ጭናቸው) ደረታቸው ላይ ለውጥ ያመጣሉ በተለይ ሆዳቸው አካባቢ ከፍተኛ የስብ ክምችት ስለሚኖርም ይወፍራሉ ደረታቸውም እየሠፋ ይሄዳል፤ እኔ ለመናገርና ለማሳየት የሞከርኩት ይሄንን ነው እንጂ ሀገርን የሚወክሉ ተጨዋቾችን ክብርና ሞራል ለመንካት አይደለም፤ ይሄንን ሳይንስና እውነትን ሰዎች ረግጠውትና ዘንግተውት ለሌላ ፍጆታ አዋሉት እንጂ እኔ ለማለት የሞከርኩት ከእንቅስቃሴ ውጪ በመሆናቸው የሰውነት ለውጥ በተለይ ዳሌና ደረት ላይ ያመጣሉ ለማለት ነው፤ ሌላ አንድ ቀላል ምሣሌ ላሳይህ የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ተጨዋቾች የኮትዲቯር ብ/ቡድንን ሲያሸንፉ በነበራቸው አቋም ላይ ነው ያሉት? ብቃታቸውና አካል ብቃታቸው በቀደመው ቦታ ላይ ነው? በፍፁም አይደለም 7 ወር ከመደበኛ ልምምድና የፉክክር ጨዋታ ርቀው በመቀመጣቸው ብቻ ስፖርት በቋሚነት በለመደው ሰውነታቸው ላይ ለውጥ ማምጣቱ የማይቀር መሆኑን እኔ ሣልሆን ሳይንስ ራሱ በማስረጃ የሚመሰክረው ነው” በማለት ተናገሯል፡፡

የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴውን የመበተን ሃሣብ አለ ይባላል በሚል ለአቶ ሰለሞን በመጨረሻ ለተነሣለት ጥያቄ “በቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ያሉ ሰዎች ገንዘባቸውን፣ ጊዜአቸውን፣ ነዳጃቸውንና ጉልበታቸውን ለእግር ኳሱ ሰውተው በነፃ የሚሠሩ ሙያተኞች ናቸው ሀገራቸውን በማገልገላቸው ከመደሰታቸው ውጪ የሚያገኙት አንዳች ነገር የለም፡፡ የእነዚህን ሰዎች ክብር መንካት አግባብ አይደለም፤ የሲለበስና በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የራስዋ የስልጠና ማንዋል እንዲኖራት የደከሙ ናቸው፤ በዚህ ልታከብራቸው ነው የሚገባው፤ ከ13 ጊዜ በላይ የቴክኒክ ኮሚቴው ደብዳቤ ፅፎ ምላሽ አላገኘም፤ በኮሚቴው ውስጥ ከአሰልጣኝነት እስከ ዶክትርነት፣ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የስፖርት ሳይንስ እውቀት ያላቸው ናቸው፤ እነዚህን ማክበርና ተባብረህ ለመስራት ሲገባ ለመበተን ማሰብ ትርፉ አይታየኝም፤ ከዚህ በተረፈ የሰውን መብት አልንካ እንጂ ለሙያተኞች ክብርና ድምጻቸውን ለማስጠበቅ እስከመጨረሻው መታገሌን እቀጥላለሁ፤ በቀጣይ የሚሆነውን አብረን እናያለን” ሲል የቴክኒክ ኮሚቴው አባል አቶ ሰለሞን አባተ በተለይ ለሀትሪክ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.