በ2014 ዓ.ም በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በውድድር ዓመቱ በተደጋጋሚ የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን በጊዜው መክፈል ባለመቻሉ ምክነያት ከተጫዋቾቹ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት እኛም መዘገባችን ይታወሳል ።
ተጫዋቾቹ ለሚመለከታቸው አካላት ቅሬታዎቻቸውን ካቀረቡ በኋላ በሚደረጉ ንግግሮች ወደ ውድድር ተመልሰው የክለቡን ማልያ ለብሰው በመጫወት ላይ ቢገኙም ያቀረቡት ጥያቄ በተገቢው መልኩ ሳይፈታ በመቅረቱ በዛሬው ዕለት ሌላ የቅሬታ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት ለማስገባት ተገደዋል ።
የቅሬታ ደብዳቤው ላይ የክለቡ 21 ተጫዋቾች ስም እና ፊርማ ያረፈበት ሲሆን በዛው ላይ እንደተገለጸውም ከሆነ የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አቅርበው መልስ ሳያገኙ በቀሩበት ጊዜ ክለቡ በ25/09/14 ዓ.ም ለፌዴሬሽኑ በስራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም ብሎ በደብዳቤ እንዳመለከተባቸው ገልፀዋል ።

ነገር ግን ክለቡ ለተጫዋቾቹ መክፈል የሚገባውን የ2013 ዓ.ም ከሁለት እስከ አራት ወራት ድረስ ክፍያ እንዳልከፈላቸው እና የ2014 ደግሞ የመጋቢት ፤ የሚያዝያ እና የግንቦት ወራት ክፍያ እንዳልተከፈላቸው በመግለፅ በቀጣዮቹ 3 ቀናት ውስጥ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ።
ሰበታ ከተማ በሊጉ የ25 ሳምንታት ጉዞ 4 ድል ፤ 5 አቻ እና 13 ሽንፈት አስተናግዶ በደረጃ ሰንጠረዡ 16ኛ ላይ ይገኛል ።
አስተያየት ይስጡ