👉ሁሉም አባላቶቼ ነጻ ናቸው /ፈረሰኞቹ/
👉ኮቪድ ፖዘቲቭ የሆኑ ተጨዋቾችን ማሰለፍ
አይቻልም / የሊግ ኩባንያ የህክምና ክፍል/
ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ራሳቸውን ከኮቪድ 19 እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን መመርያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የህክምና ኮሚቴ አሳሰበ።
በድሬዳዋ ከተማ ከ9ኛ-14ኛ ሳምንት በተካሄደው ውድድር አንድም በኮቪድ 19 የተያዘ አለመኖሩን አስታውሶ በ15ኛ ሳምንት ግን በተለይ በሆስፒታሎች አካባቢ የተያዡ ቁጥር መጨመሩን ከግምት በማስገባትና ህብረተሰቡ ላይ ያለው ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ክለቦች አባላቶቻቸው እንዲጠነቀቁ እንዲያደርጉ በህብረተሰብ ጤና ሳይንስና በሊጉ የውድድር ክፍል ሰብሳቢ ዶ/ር ወገኔ ዋልታንጉስ ማሳሰቢያ ቢሰጥም በ15ኛው ሳምንት ግን በተደረገው ምርመራ በኮቪድ የተያዙ ተጨዋቾችና የቡድን አባላት እየተገኙ መሆናቸው ታውቋል።
ያም ቢሆኖ ግን አንዳንድ ክለቦች ከአራት የማይበልጡ ተጨዋቾቻቸው ፖዘቲቭ ሆነዋል በሚል የተሰጠውን ውጤት በመቀበል ተጨዋቾቻቸውን ሲያሳርፉ በርካታ ተጨዋቾቹ ኮቪድ 19 ተገኝቶባቸዋል የተባለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን የኮሚቴውን ውሳኔ በመቃወም የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል። ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባት ቋሚ ተሰላፊዎችና ሁለት አሰልጣኞችን ጨምሮ 11 አባላቱ በኮቪድ መያዛቸው ከሊግ ኩባንያው የህክምና ቡድን ተገልጾላቸዋል ይህን ተከትሎ ነገ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ላይ እንደማይሰለፉ ተረጋግጧል።
ክለቡ እንደገለጸው ግን “ህግን ማክበራችን አይቀርም የተባሉትን ተጨዋቾች አናሰልፍም እንዴት ግን ሰባት ቋሚ ተጨዋቾች ሊያዙ ቻሉ? እንዴትስ ሁለት አጥቂ ሁለት ተከላካይ ሁለት አሰልጣኝ ፖዘቲቭ ናቸው ሊባል ይችላል? በኮሚቴው ውሳኔ አዝነናል ውጤቱን በፍጹም አንቀበለውም ህጉን አክብረን እንጫወታለን ነገር ግን ለፍትህ መከበር የምንሄድበት ቦታ ድረስ እንጓዛለን በክለባችን መብት ላይ አንደራደርም” ሲል ገልጿል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶችን በይበልጥ ያበሳጨው የአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጉዳይ ነው… ” የህክምና ኮሚቴውን ውሳኔ ከሰማን በኋላ ለዕረፍት አዲስ አበባ የሄደውን አማኑኤልን ወደ ድሬዳዋ መልሰን የፊት መስመራችንን ይመራል ብለን አመጣነው ኮሚቴው ግን ተጨዋቹን መርምሮ እሱም የኮቪድ 19 ተጠቂ ነው ብሎ ውጤቱን ገልጾልናል ይሄ የሚያሳዝን ውሳኔ ነው በፍጹም አንተወውም ግዴታችንን ተወጥተን መብታችንን እናስከብራለን እንዴትስ ይሄን ያህል ቋሚ ተጨዋቾቻችን በኮቪድ 19 ተይዘዋል ተብለን ተጫወቱ እንባላለን የትኛው ዓለም ላይስ ይሄ ተደርጓል.?” በማለት ጠይቀዋል።
አማኑኤል ገ/ሚካኤልን ጨምሮ 8ቱ ቋሚ ተሰላፊዎች ነገ እንደማይሰለፉና ከተጨዋቾቹ ተለይተው ከሆቴል እንደማይወጡ የተገለጸ ቢሆንም ክለቡ ግን “ሁለት ቦታ ምርመራ አስደርጌ ሁሉም የቡድኔ አባላት ከኮቪድ ነጻ መሆናቸውን በማረጋገጤ ስለጤናቸው ስጋት የለብኝም” በማለት አቋሙን አሳውቋል። ዛሬ በነበረው የልምምድ መርሃግብር ላይም ሙሉ የቡድኑ አባላትም በመልካም ጤንነት መስራታቸውም ታውቋል።
የህክምና ክፍሉ የላከውን ውጤት ተቃውመው በግላችን አስመርምረን ነጻ ሆነናል እያሉ ያሉ ክለቦች አሉ የኮሚቴው ምላሽ ምንድነው? ለሚለው ህክምና ክፍሉ በሰጠው ምላሽ በምርመራ ውጤቱ ትክክለኛነት ላይ ጥርጥር የለብንም” እያለ ነው… “በኛ በኩል የደረሰን የየትኛውም ክለብ ተቃውሞ ወይም ቅሬታ የለም ከዘንድሮ የሊግ ውድድር ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ
የመረጃ ክፍተት እንዳይፈጠር ሁሉም ክለቦች በአንድ ቦታ እንዲመረመሩ በጋራ ተፈራርመው ከወሰኑበት ቀን ጀምሮ ህክምና ክፍሉ ምርመራ አድርጎ ውጤት ሲያሳውቅ ቆይቷል አሁንም የተለየ ነገር የለም ልዩነቱ ውጤቱ ፖዘቲቭ መባሉ ነው የምርመራውን ውጤት ያልተቀበሉ ወገኖች ውጤቱ ኔጌቲቭ ነው ሲባል እንዴት ተቀበሉ ?” ሲል ኮሚቴው ጠይቋል።
” በእኛ በኩል ውጤቱን አንጠራጠረውም በመመሪያው መሠረት የየክለቦቹ ዶክተሮችና ቡድን መሪዎች በተገኙበት ምርመራው ተደርጎና በ30 ደቂቃ ውስጥ ውጤቱ ታውቆ የክለቡ ዶክተርና የቡድን መሪ ፈርመው ይዘው ይሄዳሉ በዚህ የምርመራ ውጤቱን የተቃወመ ወገን አልነበረም በእኛ በኩል ከሙያ ዲሲፕሊኑ አንጻር ማንንም አንጎዳም አንጠቅምም በቀጣይም ጨዋታው ሊካሄድ 75 ደቂቃ ሲቀር ለአርቢትሮችና ለጨዋታ ኮሚሽነሮች ውጤቱን በማሳየት የሚሰለፉና የማይሰለፉትን የመለየት ስራ ይሰራል” በማለት ውጤቱ ላይ ምንም ስጋት እንደሌለባቸው አስረድተዋል።
ሊግ ኩባንያው በበኩሉ “በህክምና ኮሚቴውና በኮሚቴው ሃላፊ ላይ ጥርጥር የለኝም” ብሏል። ” ሁሉም ክለቦች ተስማምተው የፈረሙትን መመርያ እንዲያከብሩ እንጠይቃለን ቋሚ ሰራተኛ ሆኖ የህክምና ኮሚቴው ሃላፊ በሆነው የህክምና ዶክተራችን ላይ ጥያቄ የለንም የፊፋ የሜዲካል ላይሰንስ ባለው ዶክተር ስራችንን እያሰራን በመሆኑ ደስተኞች ነን ሙሉ ሃላፊነቱንም እንወስዳለን” በማለት በተሰራው ስራ ላይ እምነቱ እንዳለው አሳውቋል።
ነገ ምሽት 1ሰዓት ላይ ያለወሳኝናጨቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾቹ የሚገባውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማየት በርካቶች የጓጉበት ሆኗል።
አስተያየት ይስጡ