በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሚታይ ትልቅ አሻራ ከጣሉ ክለቦች መሀል አንዱ የሆነው መቻል ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ለመቅጠር ከጫፍ መድረሱ ተነገረ።
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ40 ነጥብና 3 ግብ 9ኛ ደረጃ ይዘው የጨረሱት መቻሎች የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ኮንትራት መጠናቀቁን ተከትሎ ውሉን ለማራዘም የነበራቸውን ፍላጎት በመተው ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር መደራደርን መምረጣቸው ታውቋል ።
- ማሰታውቂያ -
በዋሊያዎቹ የአሰልጣኝነት ጉዞ ዋናና ምክትል አሰልጣኝ ሆነው የሰሩት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በባህርዳር ከተማ እንደሆነው ሁሉ በመቻል ለመድገም ጫፍ መድረሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል። አአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ባህርዳር ከተማን ሲለቅ የተተካው ኢንስትራክተር አብርሃም አሁንም ኮንትራቱ በመጠናቀቁ ከመቻል የተለያየውን አሰልጣኝ ፋሲልን ለመተካት ከጫፍ መድረሱ ገጠመኝ ነው ? ወይስ አሰልጣኝ ፋሲል የኢንስትራክተር አብርሃም መንገድ ጠራጊ የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።
የመቻል አመራሮችና ኢንስትራክተር አብርሃም ድርድር በጥሩ መግባባት እየተካሄደ ሲሆን የፊፋ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም በካፍና ፊፋ ሙሉ እምነት ተጥሎት ለአህጉሪቱ ባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት በተደጋጋሚ ወደ ውጪ የሚወጣ መሆኑ ላይ እየተነጋገሩ መሆኑ ታውቋል።
ከሁለቱም ወገኖች የወጣ መረጃ ባይኖርም ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት የኢንስትራክተር አብርሃም ቅጥር ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።