በ22ኛ ሳምንት የሶስትኛ ቀን ውሎ ረፋድ 4:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከላይ ከሚገኙት ክለቦች መካከል የሆኑትን ሲዳማ ቡናን እና ፋሲል ከነማን አገናኝቶ ኦኪኪን ቀይሮ የገባው ፍቃዱ አለሙ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ አፄዎቹ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል ።
ሲዳማ ቡናዎች በ21ኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ ተስፋዬ በቀለን እና ሰለሞን ሀብቴን በያኩቡ መሀመድ እና እና መሀሪ መና ምትክ ሲያሰልፉ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ በሳምንቱ ወላይታ ድቻን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 በተመሳሳይ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በከድር ኩሊባሊ እና ይሁን እንደሻው ምትክ ሀብታሙ ተከስተ እና ሽመክት ጉግሳ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል።
በጥሩ የፉክክር መንፈስ በተጀመረው ጨዋታ በሲዳማ ቡና በኩልም ሆነ በፋሲል ከነማ በኩል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ። በሲዳማ ቡና በኩል ከፍሬው እና ዳዊት በሚነሱ ኳሶች የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸውን ለማግኘት ሲጥሩ የነበረ ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩል የሲዳማ ቡናን የኋላ ክፍል ሰብረው ለመግባት የተቸገሩበት እና በተለይም በሲዳማ ቡና ተከላካዮች በቀላሉ ክፍተት እንዳያገኝ የተደረገው ኦኪኪ ኳሶችን ለማግኘት ተቸግሮ ነበር ።
በጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሀብቴ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር ከአንድ ደቂቃ በኋላ ሳልሀዲን ሰይድ ከሀብታሙ ገዛኸኝ የተላከለትን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
አፄዎቹ ከሲዳማ ቡና በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉ ቢሆንም ሶስተኛው የማጥቃት ዞን ላይ ያለው የኳስ ቅብብላቸው በተደጋጋሚ በሲዳማ ቡና ተጫዋቾች አግር ስር ይገባ ነበር ።
በሲዳማ ቡና በኩል 22ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ወርቃማ ዕድል አምክኗል ። ከፍሬው ሰለሞን በረጅም ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ከሳማኪ ሚካኤል ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ኳሱን ወደ ውጪ መቶታል ።
ከውሀ እረፍት መልስ ፋሲል ከነማዎች ተነቃቅተው የተመለሱ ቢመስሉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ሲዳማ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ ።
33ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሀብቴ ያሻገረውን ኳስ ይገዙ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ሞክሮ በሳማኪ ተይዞበታል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ይገዙ ከሀብታሙ ገዛከኝ በተሻገረለት ኳስ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
37ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ታመነ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ ሲወጣ አምሳሉ ጥላሁን ተከቶት ገብቷል ።
39ኛው ደቂቃ ላይ በሲዳማ ቡና በኩል ጠንከር ያለ የግብ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላከውን ጠንካራ ምት ግብ ጠባቂው መልሶበታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ፋሲል ከነማዎች በተሻለ ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ያደረጓቸው ጥረቶች በአጋማሹ ጥሩ በነበረው የሲዳማ ቡና የተከላካይ ክፍል ሳይሳካ ቀርቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ፋሲል ከነማዎች በተሻለ ወደ ፊት በመድረስ ቢጀምሩትም አሁንም የግብ ሙከራዎችን በማድረጉ ክፍተቶች ነበሩባቸው ። ሲዳማ ቡናዎችም በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል መጠጋት ቢችሉም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ደካማ መሆን ግብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል ።
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራ 55ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ከሳጥኑ ውጪ ያደረገውን ሙከራ በቀላሉ ሳማኪ ይዞታል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ሱራፌል ዳኛቸው የፋሲል ከነማን በጨዋታው መጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገ ሲሆን ተክለማርያም ሻንቆ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ፋሲል ከነማዎች ቀስ በቀስ ወደ ሲዳማ ቡና ሳጥን ደጋግመው መግባት የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን 64ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ለግቡ በቅርብ ሆኖ ከሱራፌል የደረሰውን ኳስ አየር ላይ እንዳለ ወደ ግብ ልኮት ተክለማርያም ሻንቆ ይዞበታል ።
75ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው የተጠበቀውን ያህል ለመንቀሳቀስ ያልቻለው ኦኪኪ አፎላቢ ወጥቶ ፍቃዱ አለሙ ወደ ተቀይሮ ገባ ። ፍቃዱ ወደ ሜዳ ከገባ ሰባት ደቂቃዎች በኋላ ከበረከት ደስታ ወደ ግብ ተሞክሮ በሲዳማ ቡና ተጫዋች ተጨርፎ እግሩ ስር የገባውን ኳስ ወደ ግብ በመምታት ለአፄዎቹ ግብ አስቆጥሯል ።
ከግቡ መቆጠር አንድ ደቂቃ በኋላ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ለመላክ ያደረገው ጥረት ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ጨዋታው ቀድሞ ከነበረው የመቀዛቀዝ ሁኔታ የታየበት ሲሆን በተለይም ሲዳማ ቡናዎች የአቻነቱን ግብ ለማስቆጠር ከመጣር ይልቅ ጨዋታው የተጠናቀቀ በሚመስል መልኩ ያሳዩት ደካማ ተነሳሽነት እና እንቅስቃሴ ከቡድኑ ያልተጠበቀ ነበር ። በአንፃሩ አፄዎቹ ያስቆጠሩትን አንድ ግብ አስጠብቀው በመውጣት ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 40 በማድረስ 2ኛ ደረጃን ሲያስጠብቅ ሲዳማ ቡና በበኩሉ በ34 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 5 ( አርብ ) ረፋድ 4:00 ላይ ሲዳማ ቡና መከላከያን ሲገጥም በዕለቱ 10:00 ላይ ፋሲል ከነማ ባህርዳር ከተማን የሚገጥም ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ