የጨዋታ ዘገባ | አፄዎቹ የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በድል ጀምረዋል

በርካታ ክስተቶችን ባስመለከተን ጨዋታ የአምና ሻምፕዮኖቹ ፋሲል ከነማዎች የውድድር አመቱን በጣፋጭ ድል የጀመሩ ሲሆን ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት አዲሱን ዋንጫ ተቀብለው ደስታቸውን ገልፀዋል ።

ጨዋታው አጀማመሩ በሁለቱም በኩል ኳሱን ተቆጣጥሮ የመጫወት ፍላጎት የነበረ ሲሆን ወደ ፊት ሄዶ የተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና ውስጥ በመክተት እና የግብ ሙከራዎች በማድረግ በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የተሻሉ ነበሩ ።

በፋሲል ከተማ በኩል ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት ለመጓዝ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ብዙም ርቀት ሳይጓዝ በሀዲያ ሆሳዕና ተጨዋቾች ይከሽፉ ነበር። በ25ኛው ደቂቃ ሰይድ ሀሰን ከቀኝ ክንፍ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ፍቃዱ አለሙ ለፋሲል ከነማ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ ።

የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ እያለ ፋሲል ከነማ በአስገራሚ ሁኔታ ሁለተኛውን ግብ አስቆጠሩ ።

በሀዲያ የግብ ክልል በቀኝ አቅጣጫ የነበረው ፍቃዱ አለሙ ከሱራፌል ዳኛቸው በረጅሙ የደረሰውን ኳስ መስመር አልፎ ሊወጣበት ሲል በግራ እግሩ ወደ ጎል አቅጣጫ ሲያሻግረው ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ ኳሱ በሀድያ ሆሳዕና ግብ ላይ አረፈ ። ግቡ በተቆጠረበት ወቅት በተለይም ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ኳሷ እንደወጣች በማሰቡ ምክንያት ጎሉ ሊቆጠር ችሏል ። የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በፋሲል ከተማ የ 2 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ገና ሁለት ደቂቃ እንኳን ሳይሞላው የሀዲያ ሆሳዕናው 9 ቁጥር ባዬ ገዛኸኝ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የመታው ኳስ በግሩም ሁኔታ ሚካኤል ሳማኪን አልፎ ግብ ሆነ ። ከዚህ በኋላም ሀድያ ሆሳዕናዎች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው አቻ ለመሆን በተደጋጋሚ ወደ ፋሲል ከነማ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የግቡ ሙከራዎችን ግን በቀላሉ ማድረግ አልቻሉም ።

በፋሲል በኩል መሀል ክፍሉ ላይ የበላይነት በመውሰድ ከፊት መስመር ላሉ ተጨዋቾች ኳሶችን ለማድረስ ቢሞክሩም በቀላሉ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ መግባት አልቻሉም ። 85ኛ ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ኳስ ይዞ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ለማለፍ ሲሞክር በተሰራበት ጥፋት ምክንያት ፋሲል ከነማ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን ፍፁም ቅጣት ምቱንም ሁለቱን ግቦች ያስቆጠረው ፍቃዱ አለሙ መቶት ለራሱም ሆነ ለክለብ ሶስተኛ ጎል በማስቆጠር ውጤቱን ወደ 3 ለ 1 መቀየር ቻለ ።

በዚህም ፍቃዱ አለሙ በ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሀትሪክ መስራት የቻለ ተጫዋች መሆን ችሏል ። ከግቧ መቆጠር 2 ደቂቃዎች በኋላ የሀድያ ሆሳዕናው ተጫዋች ኤፍሬም በበዛብህ መለዮ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። የጨዋታው የመጨረሻ ውጤትም ፋሲል ከነማ 3 ሀድያ ሆሳዕና 1 ሆኖ ተጠናቋል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport