በአምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ላይ በመጀመሪያው ጨዋታ የተገናኙት ድሬዳዋ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታቸውን ከ9 ሰዓት ጀምሮ አድርገው ክትፎዎቹ በጌታነህ ከበደ የቅጣት ምት ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል ።

ድሬዳዋ ከተማ በአራተኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ማሸነፍ በቻለበት ጨዋታ የተጠቀመውን ቋሚ 11 ሙሉ ለሙሉ ይዞ የገባ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ሀዋሳ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ በቋሚ አሰላለፍ ከተጠቀሟቸው ተጫዋቾች አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ አብርሃም ታምራትን ወደ ቋሚ አሰላለፍ መልሰው ጨዋታቸውን ጀምረዋል ።
በጥሩ ፉክክር እና ፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማዎች የተሻ የበላይነት የታየበት ነበር ። ቀስ በቀስም ክትፎዎቹ ወደ ጨዋታው በመመለስ መልካም እንቅስቃሴ ማሳነት ችለው ነበር ።

በ10ኛው ደቂቃ ላይ በወልቂጤ ከተማው እስራኤል እሸቱ አማካኝነት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራን ማድረግ ችለው ነበር ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በያሬድ ታደሰ ላይ በተሰራ ጥፋት ክትፎዎቹ ያገኙትን የቅጣት ምት የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ጌታነህ ከበደ አሻማው ተብሎ ሲጠበቅ ቀጥታ ወደ ግብ መትቶ በማስቆጥሮ ወልቂጤ ከተማን መሪ ማድረግ ቻለ ።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት የቻሉት ድሬደዋ ከተማዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በተለይም ለማማዱ ሲዲቤ በረጅም ኳሶችን ሲልኩ ተስተውለዋል ምንም እንኳን ውጤታማ መሆን ባይችሉም ።
36ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን በረጅም ከዳንኤል ደምሴ የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ አግኝቶ ቢሞክረውም ኢላማወን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
በድሬዳዋ ከተማዎች ጫና የቀጠለው ጨዋታም የመጀመሪያ አጋማሹ በወልቂጤ ከተማ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።

ሁለተኛው ኢጋማሽን በፈጣን ማጥቃት የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ተጋጣሚያቸውን መፈተን ቢችሉም የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድ ግን ሊሳካላቸው አልቻለም ።
49ኛው ደቂቃ ላይ የወልቂጤ ከተማው እስራኤል እሸቱ በድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ስህትት ያገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጪ ተቀልብስ ቢሞክረውም ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወቶበታል ።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ፊት ለመሄድ የሞከሩት ድሬደዋ ከተማዎች የማጥቃቱ ክፍል ላይ ሲደርሱ ድክመቶች ይስተዋሉባቸው ነበር ። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃቶችና በድሬደዋ ከተማ ተከላካዮች በሚፈጠሩ ስህተቶች ግብ ለማግኘት ሞክረዋል ።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ደቂቃዎች በቀሩት ጊዜ በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ከመስመር ወደ ግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ የወልቂጤው ተከላካይ ለማውጣት በሚጥርበት ጊዜ በእጁ ቢነካውም የመሀል ዳኛው በዝምታ አልፈውታል ። ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ወርቃማ ዕደል አግኝተው ሊጠቀሙበት አልቻሉም ። በአጋጣሚው ለግቡ በቅርበት ሆኖ መሬት ለመሬት ኳስ የደረሰው አቤል ከበደ ወደ ግብ ቢሞክረውም የግቡን ቋሚ መልሶበት ሊወጣ ችሏል ።

በዚህም ጨዋታውን ክትፎዎቹ በጠባብ ውጤት አሸንፈው ወተዋል ። ውጤቱን ተከትሎም አሸናፊዎቹ ወልቂጤ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 8 ማሳደግ ሲችሉ ተሸናፊዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎቾ ባሉበት 7 ነጥብ ለመቆየት ተገደዋል ።
አስተያየት ይስጡ