በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ለረጅም ደቂቃዎች ሲመሩ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በተጨማሪ ሰዓት በተቆጠረባቸው ግብ ተከታታይ ሶስተኛ ጨዋታ ድል ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
አዳማ ከተማ በአራተኛውዘ ሳምንት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ አራት ያህል ቅያሪዎችን በማድረግ ፍራኦል ጫላ ፤ አቡበከር ወንድሙ ፤ አሚን ነስሩ እና ታደለ መንገሻን ወደ ቋሚ 11 ሲመልሱ አዲስ አበባ ከተማዎች ግን በአራተኛ ሳምንት ፋሲል ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ የተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ይዘው ገብተዋል ።

በተመጣጣኝ ፉክክር የጀመረው ጨዋታ ገና በጊዜ ነበር በግብ ሙከራዎች መታጀብ የቻለው ። 3ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል ጫላ ከመስመር የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት የግቡ ቋሚ መልሶበታል ። የተመለሰው ኳስ በረጅም የደረሰው አቡበከር ወንድሙ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ተመልሶበታል ።
በጨዋታው አዳማ ከተማዎቾ ኳሱን በመቆጣጠር ተሽለው ቢታዩም ወደ ግብ በመድረስ ግን አዲስ አበባ ከተማዎች ብልጫ ነበራቸው ምንም እንኳን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረጉ ባይሳካላቸወም ።

40ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል ጫላ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ዳንኤል ተሾመ በድንቅ ብቃት መልሶበታል ። የመጀመሪያው ኢጋማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው በሳጥን ውስጥ ፍፁም ጥላሁን በአሚን ነስሩ በተሰራበት ጥፋት ምክንያት አዲስ አበባ ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ጥፋቱ የተሰራበት ፍፁም ጥላሁን 45ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ አዲስ አበባ ከተማን መሪ አደረገ ።

የሁለተኛው አጋማሽ በአዳማ ከተማዎች የበላይነት የተጀመረ ነበር ። 49ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ ዳዋ ሆቴሳ ተከላካዮችን በመሸወድ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ቢሞክረውም ዳንኤል ተሾመ አድኖበታል ። የአዳማ ከተማ ጫና የበዛባቸው መሪዎቹ አዲስ አበባ ከተማዎቾ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ተገደው ነበር ።

76ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከሚሊዮን ሰለሞን የደረሰውን ኳስ በመቀስ ምት ቢሞክረውም ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል ። ወደ ጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይም አዳማ ከተማዎች ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጎቸው ሙከራዎች በጨዋታው ጥሩ በነበረው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ መክነውባቸዋል ።

የጨዋታው መደበኛ 90 ደቂቃ አልቆ 6 ያህል ደቂቃዎች መጨመራቸውን አራተኛው ዳኛ አሳዩ ። የተጨመሩት ደቂቃዎች ተጠናቀው የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ አዳማ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግብ ሲመታው ኳሱን ያገኘው አብዲሳ ጀማል አስቆጠረው ። ጨዋታውም በአንድ አቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ግድ ሆነ ።

ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ ነጥባቸውን 6 ሲያደርሱ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ 7 ነጥብ ላይ ደርሰዋል ።

አስተያየት ይስጡ