በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የተገናኙት ድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ሁለት የቀይ ካርዶች በታየበት እና ቀዝቀዝ ያለ በነበረው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች በ13ኛው ደቂቃ ላይ በሙኸዲን ሙሳ ባስቆጠሩት የፍፁም ቅጣት ምት አሸንፈው ወጥተዋል ።
ድሬዳዋ ከተማ በስምንተኛው ሳምንት ጨዋታ በሀድያ ሆሳዕናን በተሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የገቡ ሲሆን ደረጄ አለሙ ፤ ሱራፌል ጌታቸው ፤ መጣባቸው ሙሉ ፤ ጋዲሳ መብራቴ እና መኸዲን ሙሳን ጨዋታውን እንዲጀምሩ ሲያደርጉ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ከሀዋሳ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው አሰላለፍ ብሩክ ግርማን ብቻ ቀይረው በማስገባ ጨዋታውን ጀምረዋል ።
አዲስ አበባ ከተማ ዋና አሰልጣኙን እና ምክትሉን በኮቪድ 19 መያዛቸውን ተከትሎ ግብ ጠባቂውን ዳንኤል ተሾመን ቡድኑን በአሰልጣኝነት እየመራ ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን በማድረግ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ13ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ግብ ያስተናገደው ። እንዳለ ከበደ በሳጥን ውስጥ በእንየው ካሳሁን ላይ በሰራው ጥፋት ድሬዳዋ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሙኸዲን ሙሳ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አደረገ ።
ከግቡ መቆጠር በኋላ በአመዛኙ አዲስ አበባ ከተማዎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ የቻሉበት ነበር ። ነገር ግን በሁለቱም በኩል ወደ ፊት በማለፍ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች በቀላሉ እየተበላሹ የግብ ሙከራዎችን እንዳንመለከት አድረጓል ። በ23ኛ ደቂቃ ላይ በመሀል ሜዳው አካባቢ ቻርለስ ሪባኑ ከመሀመድ አብዱለጢፍ የነጠቀውን ኳስ በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ሲያሻግረው ፍፁም ጥላሁን በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ሲሞክር በግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙ የተመለሰበት ሲሆን የተመለሰውንም ኳስ ሪችሞንድ ኦዶንጎ አግኝቶ በጠንካራ ምት ወደ ግብ ሲመታው በድጋሚ ግብ ጠባቂው መልሶታል ።
31ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ከታዩት ሁለት የቀይ ካርዶች የመጀመሪያው የታበት ነበር ። ሱራፌል ጌታቸው በረጅሙ ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል የላከውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዋከኔ አዱኛ ከሳጥኑ ወጥቶ ለመመለስ ሲሞክር አምበሉ ዘሪሁን አንሼቦ መውጣቱን ባለመመልከቱ በግንባር ለማቀበል ሲሞክር ዋከኔ በእጁ በመመለሱ የዕለቱ የመሀል ዳኛ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተወታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሆነ የግብ ሙከራ ሳያስመለክተን በድሬዳዋ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው አዲስ አበባ ከተማዎች ሁለት ያህል ቅያሪዎችይ በማድረግ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት ። በሁለቱም በኩል እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ወደ ግብ በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች የታዩበት ሲሆን አሁንም ግን በሶስተኛው የማጥቃት ክፍል ላይ የሚደረጉ ቅብብሎች እና ውሳኔዎች ውጤታማ አለመሆን ጨዋታውን ቀዝቃዛ እንዲሆን አድርጎታል ። በ54ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ያሻገረውን ኳስ ልመንህ ታደሰ ቢያገኘውም ኳሱን በአግባቡ ሳይጠቀምበት ወደ ውጪ ወቷል ።
በ74ኛው ደቂቃ ላይ እስካሁን የቁጥር ብልጫን ወስደው ሲጫወቱ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎቾ እንደተጋጣሚያቸው ቁጥራቸው ወደ 10 የቀነሰበት ነበር ። መሀመድ አብዱለጢፍ በሪችሞንድ ኦዶንጎ ላይ በሰራው ጥፋት ባየው የቢጫ ካርድ እና ቀደም ብሎም ሌላ የቢጫ ካርድ መመልከቱን ተከትሎ በቀይ ክርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል የነበሩት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ተጨማሪ ግብ እንዳይቆጠር አድርገው ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ ነጥቡን 11 በማድረስ ደረጃውን ወደ 11ኛ ሲያሻሽል ተሸናፊው አዲስ አበባ ከተማ በተመሳሳይ 11 ነጥብ ባለበት 9ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።