በሊጉ የአምስተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ የመጀመሪያ ጨዋታ የተገናኙት በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች የሚመሩት ባህርዳር ከተማ እና መከላከያ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ጨዋታቸውን አድርገው ቢንያም በላይ በፍፁም ቅጣት ምት እና በጥሩ ብቃት ተጨዋቾችን አልፎ ባስቆጠረው ግብ ጦሩ 2 ለ 0 አሸንፎ ወጥቷል ።
በአራተኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች ለውጦችን አድርገው የገቡ ሲሆን ባህርዳር ከተማ አምስት ተጨዋቾች እንዲሁም በመከላከያ በኩል ሁለት ቅያሪዎች ነበሩ ። በባህርዳር ከተማ በኩል ፋሲል ገብረሚካኤል ፤ አህመድ ረሺድ ፤ መናፍ አወል ፤ ፉዐድ ፈረጃ እና ዓሊ ሱሌይማን በመከላከያ በኩል ደግሞ ገናናው ረጋሳ እና ሰመረ ሀፍተይ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ተመልሰው ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።
በጨዋታው ባህርዳር ከተማዎች ከዚህ ቀደም ያደርጉት እንደነበረው ኳስን ከኋላ መስርተው በመጫወት ወደ ፊት በመሄድ የተጫወቱ ሲሆን መከላከያዎች አልፎ አለፎ ኳስን ይዞ ለመጫወት ከመሞከራቸው ውጪ ፈጣን እና ተሻጋሪ ኳሶችን በረጅሙ ወደ ፊት በመጣል ለመጫወት ጥረት አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የግብ ሙከራዎችን ሳያሳየን የቆየው ጨዋታ 21ኛ ደቂቃ ላይ በፍፁም አለሙ ከሳጥን ውጪ በተመታና ኢላማውን ያልጠበቀ የግብ ሙከራ አስመልክቶናል ። 28ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተጀምሮ መሬት ለመሬት የመጣ ኳስ አሌክስ ተሰማ ሊያወጣው ሲል አልፎት ፈቱዲን ጀማል ጋር ቢደርስም ፈቱዲን ተንሸራቶ የመታት ኳስ ለጥቂት በግብ ጠባቂው ክሌመንት ቦዬ ተይዞበታል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም አህመድ ረሺድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው መልሶበታል ። በተለይም ከውሀ እረፍት በኋላ በተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት መከላከያዎች በሰመረ ሀፍተይ አማካኝነት በረጅም ከተላኩ ኳሶች በግንባር በመግጨት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ምንም ግብ ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽን በተመሳሳይ መልኩ የጀመሩት ሁለቱ ክለቦች ወደ ግብ በመቅረብ እና የግብ ሙከራዎችን በማድረግ በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነገር አሳይተዋል ።
52ኛ ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ወሳኝ ተጫዋች ፍፁም አለሙ ከሳጥን ውጪ በቀኝ በኩል ወደ ግብ ጠንከር አድርጎ የመታው ኳስ በክሌመንት ቦዬ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የባህርዳር ከተማ ተከላካዮችን ተጭኖ በመጫወት ኳስ የነጠቃቸው ብሩክ ሰሙ 59ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብ ቀርቦ ያደረገውን የግበሰ ሙከራ ፋሲል ገብረሚካኤል አውጥቶበታል ።
63ኛ ደቂቃ ላይ በመላከያዎች በኩል ወደ ግብ የተሻገረውን ኳስ መናፍ አወል በእጁ በመንካቱ የጣና ሞገዶቹ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠባቸው ። የፍፁም ቅጣት ምቱን ቢንያም በላይ መቶ ፋሲል ገብረሚካኤል ቢመልሰውም ፋሲል በሚመልስበቶ ወቅት የግቡን መስመር አልፎ በመውጣቱ የፍፁም ቅጣት ምቱ ሊደገም ችሏል ። የተደገመውንም የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቢንያም በላይ መትቶ 67ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጠረው ።
ከግቡ በኋላ ተጭነው በመጫወት ወደ ፊት ለመሄድ የሞከሩት ባህርዳር ከተማዎች በሶስተኛው የማጥቃት ዞን ላይ ሲደርሱ ኳሶች በተደጋጋሚ ይበላሹባቸው ነበር ። ይባስ ብሎም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5 ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሌላ ግብ አስተናገዱ ።
የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ቢንያም በላይ 3 የባህርዳር ተጨዋቾችን አልፎ በሳጥን ውስጥ በመግባት ግሩም ኳስ አስቆጠረ ። በቀሩት ደቂቃዎችም ተጭነው በመጫወት ግብ ሲፈልጉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በመከላከያ የ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
ውጤቱን ተከትሎም መከላከያ ነጥቡን 10 ያደረሰ ሲሆን ባህርዳር ከተማ ባለበት 7 ነጥብ ይቆያል ።