የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና መከላከያ መካከል ተደርጎ አዲሱ አቱላ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ መከላከያዎች ሙሉ ሶሰት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል ።
አዳማ ከተማ በ12ኛው ሳምንት ከፋሲል ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ የገቡ ሲሆን በሚሊዮን ሰለሞን እና ዳዋ ሆቴሳ ምትክ አዲስ ተስፋዬን እና አብዲሳ ጀማልን ያሰለፉ ሲሆን በመከላከያ በኩልም በወላይታ ድቻ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ አዲሱ አቱላን እና ኦኩቱ ኢማኑኤልን በሰመረ ሀፍተይ እና ብሩክ ሰሙ ምትክ በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል ።

ጨዋታው በፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በሁለቱም በኩል በቶሎ ወደ ግብ የመድረስ አዝማምያዎች ነበሩ ። በአንፃራዊነት መከላከያዎች ወደ ግብ ክልል የቀረቡባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን 9ኛው ደቂቃ ላይ ተሾመ በላቸው አዲስ ተስፋዬን አልፎ ወደ ግብ ሊሞክረው የነበረውን ኳስ አዲስ እግሩን አስገብቶ ከመምታት ሊያግደው የቻለ ሲሆንጨበቅርበት የነበሩት የዕለቱ አልቢትር ጨዋታውን አስቀጥለዋል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን መከላከያዎች ግብ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ከቀኝ መስመር አቅጣጫ የተገኘው የቅጣት ምት ወደ ሳጥን ሲላክ ጀማል ጣሰው ለማውጣት ሲምክር ኳሱን ያገኘው አዲሱ አቱላ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።

ከግቡ በኋላ አዳማ ከተማዎች የጨዋታ ብልጫውን በመውሰድ ተጫውተው የነበረ ቢሆንም ወደ መከላከያ የግብ ክልል የሚያደርሷቸው ኳሶች በቀላሉ ይበላሹ ነበር ። በ24ኛው ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከአቡበከር ወንድሙ የደረሰውን ኳስ በአግባቡ መምታት ሳይችል ኳሱ ኢላማውን ስቶ ወጥቷል ።
በቀላሉ የመከላከያን የተከላካይ ክፍል አልፈው ወደ ሳጥን ለመግባት የተቸገሩርተ አዳማ ከተማዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ምንም እንኳን አንዱም ኢላማውን የጠበቀ ባይሆንም ። የመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከያ መሪነት ተጠናቋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ግብ ክልል በመቅረብ ከተጋጣሚያቸው በጣም በተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር ። መከላከያዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ከኳስ ጀርባ ሆነው በከፍተኛ መከላከል አጋማሹን የተጫወቱ ሲሆን ይህ አጨዋወት በቀላሉ የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ ያገዳቸው አዳማ ከተማዎች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ሳጠሰን በመላክ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ።

በአጋማሹ የነበረው የመጀመሪያ ሙከራ በመከላከያ በኩል የተደረገ ሲሆን ግሩም ሀጎስ ከቅጣትም ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በጀማል ጣሰው ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። እንደብልጫቸው በሙከራ ያልታጀቡት አዳማ ከተማዎች በ64ኛ ደቂቃ ላይ በዮሴፍ ዮሀንስ ከርቀት በተመታ ኳስ አቻ ለመሆን ያደረጉት ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሷል ። በ72ኛ ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ በአየር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ኳሱ ኢላማውን የጠበቀ ባለመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል ።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ተሻጋሪ ኳሶች በመጠቀም በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም በመከላከያው ግብ ጠባቂ ክሌመንች ቦዬ ግብ ከመሆን ድነዋል ። በመጨረሻም ጨዋታው በመከላከያ አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 17 በማድረስ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 17 ነጥብ በግብ ክፍያ ተሽሎ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
በ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መከላከያ ሀዋሳ ከተማን አዳማ ከተማ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።

አስተያየት ይስጡ