በሁለቱም ክለቦች በኩል በቋሚ አሰላለፍ ከሊጉ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸው የተወሰኑ ለውጦችን አድርገው የገቡ ሲሆን በባህር ዳር ከተማ በኩል አንድ ቅያሪ እንዲሁም በወልቂጤ ከተማ በኩል ደግሞ ሁለት ያህል ቅያሪዎች ነበሩ ።
ቀን 8 ሰዓት ላይ በጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በጅማሮው በሁለቱም በኩል ጥሩ ፉክክር የታየበት እና በኳስ ቁጥጥሩም የበላይ በመሆን ግብ ለማስቆጠር ጥረቶች የነበሩበት ነበር ።

ጨዋታው 20 ደቂቃ እስኪሞላው ያን ያህል ከባድ የሆነ የግብ ሙከራ ባንመለከትም በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከጫላ ተሺታ የደረሰውን ኳስ በግራ እግሩ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም የሆነ ግብ አስቆጥሮ ወልቂጤ ከተማን መሪ ማድረግ ቻለ ።

ከግቧ መቆጠር በኋላ የጣና ሞገዶቹ በተሻለ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል ። በ34ኛው ደቂቃ ላይም ከሀድያ ሆሳዕና በነበረው ጨዋታ ድንቅ ግብ ያስቆጠረው ኦሴ ማውሊ በግቡ አቅራቢያ በተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም በወልቂጤ መሪነት ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ በኋላ በመመራት ላይ የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው ጊዜ 3 ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ ። ግርማ ዲሳሳ ወደ ግብ ለመምታት ሲሞክር በሳጥን ውስጥ የነበረው ዳግም ንጉሴ በእጁ በመንካቱ የጣና ሞገዶቹ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ፍፁም አለሙ አስቆጥሮት የጨዋታው ውጤት ወደ 1 ለ 1 ተቀየረ ።

ከአቻነቷ ግብ መቆጠር በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የጣሩ ሲሆን በወልቂጤ ከተማ በኩልም በተለይም ከቆሙ ኳሶቹ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። ነገር ግን በአጋማሹ በሁለቱም በኩል ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ የግብ ሙከራ አላስመለከተንም ነበር ። የጨዋታው ውጤትም ሌላ ግብ ሳያክል 1 ለ 1 ተጠናቋል ።

አስተያየት ይስጡ