የጨዋታ ዘገባ | የጣና ሞገዶቹ የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸውን በድል ተወጥተዋል !!

በ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር የመጀመሪያ ሳምንት ሶስተኛ ቀን ጨዋታ በባህርዳር ከተማ እና አዲስአበባ ከተማ መካከል ከቀኑ 9:00 ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ተደርጎ በጣና ሞገዶቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

አስቀድሞ በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በአስደናቂ ብቃት የዉድድሩ ዋንጫ ባለቤት የሆነዉ ባህርዳር ከተማ በተቃራኒው አምና በከፍተኛ ሊጉ ሲወዳደር የቆየዉ እና በዘንድሮ ወደ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተመለሰው አዲስአበባ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች ማራኪ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ነበር፤ በተለይ በባህርዳር ከተማ በኩል ኳስን መስርተው ለመጫወት ሲሞክሩ የተስተዋለ ሲሆን በአንፃሩ በእስማኤል አቡበከር የሚመራው አዲስአበባ ከተማ በበኩሉ የጣና ሞገዶቹን ኳስ በማበላሸት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በአንድ ሁለት ቅብብል ለመድረስ ሙከራ ሲያደርጉ ተመልክተናል።

በዚህ ሂደት የቀጠለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በ22ኛዉ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ግብ አስተናግዷል። መሀል ለመሀል ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ከቀኝ መስመር በኩል ከመሳይ አገኘዉ የተሻገረለትን ኳስ የመስመር አጥቂው ተመስገን ደረስ ወደ ግብነት በመቀየር የጣና ሞገዶቹ 1ለ0 እንዲመሩ አስቻለ።

ከግቧ መቆጠር በኋላ የበለጠ ተጭነዉ በተቃራኒ የግብ ክልል አካባቢ መጫወት የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም የአዲስአበባ ከተማን መረብ ድጋሚ መድፈር ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ አዲስ አበባ ከተማዎች ከመጀመሪያዉ አጋማሽ አንፃር ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማግኘት ሲሞክሩ የተስተዋለ ሲሆን በአንፃሩ የጣና ሞገዶቹ መሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ አህመድ ረሽድን ቀይረዉ ወደ ሜዳ በማስገባት ከአማካዩ ፍፁም አለሙ ጋር በግራ መስመር ላይ አደገኛ የማጥቃት ሀይልን በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩ ተመልክተናል።

በተለይ ደግሞ በ52ኛዉ ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ከግራ መስመር ለአጥቂዉ ተመስገን ደረሰ ያቀበለዉን ኳስ ተመስገን ደረሰ ወደ ግብ መቀየር ሳይችል ቀርቶ ኳሷን አምክኗታል። በ55ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ የጨዋታ ብልጫውን መዉሰድ የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች ሁለተኛ ግብ ማግኘት ችለዋል። ግርማ ዲሳሳ መሀል ለመሀል ያቀበለዉን ኳስ የፊት አጥቂዉ ኦሴ ማዉሊ ወደ ግብነት ቀይሮ የጣና ሞገዶቹን መሪነት ወደ 2ለ0 ከፍ ማድረግ ችሏል።

በተደጋጋሚ ከቆሙ ኳሶች እንዲሁም በረጃጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት ሲታትሩ የነበሩት አዲስአበባ ከተማዎች ዉጥናቸዉ ሰምሮ ግብ ማግባት ባይችሉም በአጥቂያቸዉ ፍፁም ጥላሁን አማካኝነት የተወሰኑ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

በመጨረሻም ጨዋታዉ ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች በቀሩበት ሰዓት የአዲስአበባ ከተማዉ ተከላካይ መቆጣጠር ያቃተዉን ኳስ በመጠቀም አጥቂው ኦሴ ማዉሊ ለራሱ ሁለተኛውን እንዲሁም ለክለቡ ሶስተኛ ግብ በማስቆጠር የጣና መገዶቹ የ3ለ0 ጣፋጭ ድል እንዲጎናጽፉ ማድረግ ችሏል።

Writer at Hatricksport

Facebook

Ermias Misganaw

Writer at Hatricksport