ከአራት ጨዋታዎች ሶስተኛ የ 1 ለ 0 ውጤት በተመዘገበበት ጨዋታ መከላከያ አሸናፊ መሆን ችሏል ።
የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከዚህ ቀደም በሊጉ ጠንካራ ቡድኖች ይዘው ይቀርቡ የነበሩትንና ወደ ከፍተኛው ሊግ ወርደው በዘንድሮው የውድድር ዓመት ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሱትን መከላከያን እና አርባ ምንጭ ከተማን ያገናኘ ነበር ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ የተጀመረው ጨዋታ ገና ከጅምሩ ፈጣን እንቅስቃሴ ያሳየ ነበር በተለይም በመከላከያ በኩል በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመድረስ ቀድመው ጎል ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ነበር ። በተለይም ኦኩቱ ኢማኑኤል 5ኛ ደቂቃ ላይ ያመከናት ግልፅ ኳስ ለመከላከያ የምታስቆጭ ነበረች ። ቀስ በቀስ አርባ ምንጭ ከተማዎች ጨዋታው ለመቆጣጠር እና በተቃራኒ ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል ። በተለይም በአሸናፊ ኤልያስ እና ፀጋዬ አበራ አማካይነት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በሁለቱም በኩል በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ቢሞከርም የመጀመሪያው አጋማሽ ግን ያለምንም ግብ ነበር የተጠናቀቀው ። በሁለተኛው የጨዋታው አጋማሽ አርባ ምንጭ ከተማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ብልጫ በመውሰድ ወደ ጎል ክልል ለመድረስ ቢጥሩም በጨዋታው ጠንካራው የነበረውን የመከላከያ የተከላካይ መስመር ግን ማለፍ አልቻሉም ።
በ58ኛ ደቂቃ ላይ መከላከያዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተቃራኒ የጎል ክልል በመድረስ ግሩም ሀጎስ ከግራ መስመር ወደ ጎል ያሻገራትን ኳስ የፊት አጥቂው ኦኩቱ ኢማኑኤል በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር መከላከያን ቀዳሚ አደረገ ።
ከግቧ መቆጠር በኋላ አርባ ምንጮች በይበልጥ ጫና በመፍጠር ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ ቢጥሩም የመከላከያን የተከላካይ መስመር አልፎ ግብ የሚያስቆጥር ተጫዋች ማግኘት አልቻሉም ። 85ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ የግቡ ቋሚ የመለሰበት የቅጣት ምት በመከላከያ በኩል አሪፍ የሚባል የግብ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል ። ጨዋታውም በመከላከያ አሸናፊነት 1 ለ 0 ተጠናቀቀ ።