በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በሊጉ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት ያጋጠመው አዲስ አበባ ከተማን በተቃራኒው በሁለቱም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለውን መከላከያን አገናኝቶ የነበረ ሲሆን ሳይጠበቅ አዲስ አበባ ከተማ 1 ለ 0 በማሸነፍ የአመቱ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል ።
አዲስ አበባ ከተማ ከሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸው ያህል አራት ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን በመከላከያ በኩል ደግሞ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
ጨዋታው ገና 1 ደቂቃ እንኳን ሳይሞላው ነበር የመጀመሪያው ግብ የተቆጠረው ። እያሱ ለገሰ ከግቡ ክልሉ በረጅም የመታውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን አግኝቶ በግብ ጠባቂው አናት ላይ አሳልፎ አዲሴ አበባ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ ።
- ማሰታውቂያ -
ይህም ግብ በአመቱ ለአዲስ አበባ ከተማ በኩል የተቆጠረ የመጀመሪያው ግብ ሲሆን ለመከላከያ ደግሞ በአመቱ የተቆጠረበት የመጀመሪያ ግብ ሆኗል ። በጨዋታው በሁለቱም ክለቦች በኩል አጥቅተው ግቦችን ለማስቆጠር ጥረቶች ተደርገዋል ።
15ኛው ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍተይ ከኦኩቱ ኢማኑኤል የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ቢያገኘውም ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። በ20ኛው ደቂቃ ላይ ሳድቅ ተማም ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወቷል ። የአቻነቷን ግብ ፍለጋ ላይ የነበሩት መከላከያዎች በኦኩቱ ኢማኑኤል እና ሰመረ ሀፍተይ አማካኝነት በጭንቅላት በተገጩ ኳሶች ግብ ለማግኘት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል ።
ጨዋታውን በመምራት ላይ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። በመከላከያዎች በኩልም ጫና በመፍጠር ግቦችን ለማስቆጠር ቢሞክሩም ያን ማድረግ ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ በመከላከያ በኩል ጫናዎቹ የቀጠሉ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ተረጋግተው በጥንቃቄ መጫወትን መርጠው ነበር ። ከአጋማሹ ጅማሮ በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች ሁለተኛውን ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው 7 ደቂቃ ብቻ ነበር ። በሙሉቀን አዲሱ ተቀይሮ የገባው ሮቤል ግርማ ከቅጣት ምት የመታው ኳስ የግብ ጠባቂው ክሌመንት ቦዬ ስህተት ታክሎበት ከመረብ አረፈ ።
ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላም መከላከያዎች ይበልጥ ጫናቸወን በማጠናከር ግብ ለማስቆጠር ጥረታቸውን የቀጠሉ ቢሆንም 61ኛ ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ አስተናገዱ ። ሳድቅ ተማም ከክንፍ ከያሬድ ሀሰን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ቢመለስበትም የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ፍፁም ጥላሁን ኳሱን መትቶ በማስቆጠር የመዲናዋን ክለብ መሪነት 3 ለ 0 አደረገ ።
መሪነታቸው ያጠናከሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ኳሱን በመቆጣጠር የጨዋታውን ሚዛን ወደራሳቸው ማድረግ የቻሉ ሲሆን ጥሩ ጥሩ ተጨማሪ ሙከራዎችንም አድርገው ነበር ። በመከላከያ በኩል ለአጥቂው ኦኩቱ ኢማኑኤል የሚደርሱት ኳሶች ውጤታማ ባለመሆናቸው ግብ ለማስቆጠር የተቸገሩ ሲሆን ይባስ ብሎም 86ኛ ደቂቃ ላይ ገናናው ረጋሳ በእንዳለ ከበደ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ወቷል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ መከላከያዎች በተለይም በአዲሱ አቱላ እና በግሩም ሀጎስ አማካይነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለውም ነበር ። በመጨረሻም አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታውን 3 ለ 0 በማሸነፍ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ጣፋጭ ድልን ተጎናፅፏል ።