በሊጉ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ በአዲስ አበባ የነበሩ ሁለት ጨዋታዎች በዝናብ ምክንያት ሳይደረግ ሲቀር አዳማ ላይ ግን ሸገር ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ፋሲል ከነማን 1ለ0 ሲረታ የምድረገነት ሽረ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን አራት ጨዋታዎች ዛሬ በሁለተኛ ቀኑ ሊደረጉ የነበረ ቢሆንም አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የነበሩ ጨዋታዎች ማለት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እያደረጉት የነበረው መርሀግብር ያለ ጎል እየተጓዘ 31ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በጣለው ከባድ ዝናብ መቋረጥ የቻለ ሲሆን ነገ ቅዳሜ ረፋድ 3፡30 ሲል ከቆመበት በአበበ ቢቂላ አርቴፊሻል ስታዲየም የሚቀጥል ይሆናል። አስር ሰዓት ላይ ደግሞ ሊደረግ የነበረው የወላይታ ድቻ እና ነገሌ አርሲ ጨዋታም ሐሙስ ግንቦት 27 እንደሚደረግ ይፋ ተደርጓል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ በቀዳሚነት ምድረገነት ሽረን ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አገናኝቶ በነበረው ጨዋታ 1ለ1 በሆነ ውጤት መቋጨት ችሏል። እጅግ በተሻለ ሽግግር ተፅዕኖ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ነብሮቹ 35ኛው በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር በኩል ደስታ ዋሚሾ ከጥልቅ ቦታ ወደ ውስጥ የሰጠውን ኳስ እዮብ አለማየሁ ወደ ግብነት ለውጧት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በንፅፅር ተሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት ምድረገነት ሽረዎች መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች እየቀሩ ማለትም 88ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አጥቂው ዳንኤል ዳርጌ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ጨዋታው 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ማምሻውን ፋሲል ከነማን ከሸገር ከተማ ጋር አገናኝቶ በነበረው ጨዋታ የአሰልጣኝ እያሱ መርሀፅድቁ ሸገር ከተማ ሦስት ነጥብ አግኝቶ የወጣበት ነበር። ጨዋታው ቀጥሎ እንደነበረው ወረድ ያለ ፉክክር ጎል ሳያሳየን ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት 90ኛው ደቂቃ ሔኖክ አዱኛ ሰንጥቆ ሰጥቶ ዳዊት ካሳው ተቀብሎ ወደ ቀኝ የለቀቀለትን ኳስ ቡልቻ ሹራ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ካሜሮናዊው የግብ ዘብ ሞይስ ፓዎቴ ሳጥን ውስጥ ጥፋት በመስራቱ የዕለቱ ዳኛ ፍቅሩ ለገሠ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሔኖክ አዱኛ ከመረብ አዋህዶ ጨዋታው በሸገር ከተማ የ1ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል።

አስተያየት ይስጡ