መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ “ድህነትን ሳንፈራ እግር ኳስን ልንፈራ አይገባም፤ እኛ ቤተሰብ ውስጥ ኳስን የሚፈራት የለም”ጅብሪል ናስር /ወልቂጤ ከተማ/
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግወልቂጤ ከተማዜናዎች

“ድህነትን ሳንፈራ እግር ኳስን ልንፈራ አይገባም፤ እኛ ቤተሰብ ውስጥ ኳስን የሚፈራት የለም”ጅብሪል ናስር /ወልቂጤ ከተማ/

አጋራ
አጋራ

 

“ጥሩ እግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን ችሎታ ብቻ በቂ አይደለም፤ የራስ መተማመን ሊኖርህ ይገባል፤ እኔ እየተጓዝኩ ያለሁትም በዚሁ መልኩ ነው”

“ድህነትን ሳንፈራ እግር ኳስን ልንፈራ አይገባም፤ እኛ ቤተሰብ ውስጥ ኳስን የሚፈራት የለም”ጅብሪል ናስር /ወልቂጤ ከተማ/

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በሁለተኛው ዙር የዝውውር መስኮት ከሰበታ ከተማ ቡድን በመምጣት ተቀላቅሏል። ወልቂጤ ከተማ እያደረጋቸው ባሉት የእዚህ ዙር ሁለት ጨዋታዎች ላይም ተቀይሮ በመግባት ለ10 እና ለ30 ደቂቃዎች ሊጫወትም ችሏል። በተለይ ቡድኑ ዛሬ ከወላይታ ድቻ ጋር ተጫውቶ 1-1 በተለያየበትና የቡድናቸው ተጨዋች አህመድ ከጨዋታ ውጪ ሆኖ ባስቆጠረበት ጨዋታ ላይ ወደ ሜዳ ከገባበት ደቂቃ ጀምሮ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየውን ጅብሪል ናስርን ሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ ከጨዋታው በኋላ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግራው ምላሽን ሰጥቷታል።
የሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፁ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ እና ጅብሪል ናስር ያደረጉት ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል።

ከወላይታ ድቻ ጋር ስላደረጉት እና አቻ ስለተለያዩበት የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ

“የቡድናችንን የዛሬው ጨዋታ በተጠባባቂ ስፍራ ላይ ሆኜም ሆነ ተቀይሬ ከገባው በኋላ እንደተመለከትኩት መጀመሪያ ላይ በእኛ ቡድን ተጨዋቾች ላይ እርስበርስ ያለመነጋገርና ያለመረጋጋት ችግር ይታይ ነበር። ይህንም አሰልጣኛችን በደንብ አስተውሎት ስለነበርና እኔም ተቀይሬ ከገባው በኋላ ክፍተቱን ስለተመለከትኩኝ አሰልጣኙ የሰጠንን ታክቲክ ተግብረን ጨዋታውን ከ 1-0 መመራት በአቻ ውጤት ልናጠናቅቅ ችለናል”።

በጨዋታው እንቅስቃሴ ማን የተሻለ እንደነበር

“እኛ ነና! ምክንያቱም በአብዛኛው የጨዋታው እንቅስቃሴ ኳሱን ይዘን እንጫወት ነበርንና የእነሱ አጨዋወት ደግሞ ካላቸው አቅም አኳያ የመልሶ ማጥቃትን ታክቲክ ይከተሉ ስለነበር እና ወደፊትም ኳስ እየጣሉ ለመጫወት ይሞክሩ ስለነበር የእኛ ቡድን ከያዛቸው ኳስ የሚችሉ ተጨዋቾች አንፃርና በምንከተለውም አጨዋወት በኳሱ እኛ ተሽለን ታይተናል”።

ለወልቂጤ ከተማ ተቀይረህ ገብተህ ጥሩ እና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ስለማሳየትህ

“በዛሬው ጨዋታ ላይ ከእኔ ይልቅ ኳሱን ከውጪ ሆነው የተመለከቱኝ ሰዎች ስለ ችሎታዬ ሲነግሩኝ በጣም ነው የተደሰትኩት። ብዙ ሰዎችም ደውለውልኝ በርታም ነው ያሉኝና አመሰግናቸዋለሁኝ”።

በዛሬው ጨዋታ ላይ እንደ ራሱ ምልከታ ጥሩ እንቅስቃሴን አድርጌ ከሜዳ ወጥቻለሁ ብሎ ያስብ እንደሆነ

“በእግር ኳስ ጨዋታ ሁሌም ወደ ሜዳ ስትገባ በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ስለመሆንህ እና አለመሆንህ ከምታሳየው አጨዋወት በመነሳት የግጥሚያው መንፈስ በደንብ አድርጎ የሚነግርህ ነገር አለና እኔም ተቀይሬ ከገባሁበት ደቂቃ ጀምሮ ጥሩ እንቅስቃሴን ነው በሜዳ ላይ ያሳየሁት። ጥሩ ለመጫወቴም ከበፊት አንስቶ በተፈጥሮዬ ይዤ የመጣሁት የራስ መተማመን ብቃትና ግጥሚያን ያለ መፍራት ባህሪዬ በጣሙን ሊረዳኝ ችሏል። ምክንያቱም እግር ኳስን ስታስብ ከችሎታ በላይ 90 በመቶው የአንተ ኮንፊደንስ ነው። ችሎታህ ሁሌም ከአንተ ጋር አብሮ ያለ ነው። ኮንፊደንሱ ከሌለ ግን ኳሱን ልትጫወተው አትችልምና እኔ ከችሎታዬ በላይ በተፈጥሮዬ ኳስን ሳልፈራት ስለምጫወት ነው ጥሩ ልንቀሳቀስ የቻልኩት”።

የኢትዮጵያ ቡናዎቹ አቡበከር እና ሬድዋን ናስር ታላቅ ወንድም ሆነህ ባለህ ጥሩ የኳስ ችሎታ እንደ እነሱ በተለይም ደግሞ እንደ አቡበከር ስምህ በጎላ መልኩ ላለመጠራቱ ምክንያት ስለሆነብህ ነገር

“የእውነት ነው፤ ኳሱ ላይ ባለኝ ችሎታ እኔን የሚያውቀኝ ያውቀኛል። ከሁለቱ ወንድሞቼ በላይም ቀድሜም ነበር መታወቅ የነበረብኝ። ያም ሆኖ ግን በአንድ ወቅት በጣም ታምሜ እና ብዙም ደም ፈሶኝ ለሞት በሚያቃርበኝ ደረጃም ላይ ደርሼ ስለነበር ያ ሁኔታ ነው እኔን ለሁለት ዓመታት ያህል ከኳሱ ስላራቀኝ ታዋቂ ተጨዋች እንዳልሆን ተፅህኖን የፈጠረብኝ። ከዛም በኋላ ቢሆን ወደ እግር ኳሱ በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ልገባ ብችልም በተለያዩ ምክንያቶች ነው በምፈልገው ደረጃ ላይ እንዳልገኝ ያደረገኝ። አሁን ግን ከሰበታ ከተማ ወደ ወልቂጤ ከተማ በዝውውር መስኮቱ ቡድኑን በሁለተኛው ዙር ላይ ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ አሰልጣኛችን በሰጠኝ የመጫወት እድል የመጀመሪያው ግጥሚያ ላይ 10 ደቂቃ በዛሬው ጨዋታ ላይ ደግሞ 30 ደቂቃ እንድጫወት እና ተደጋጋሚ ግጥሚያንም ያደረግኩበት ሁኔታ አለና ይሄ የምጫወትበት ደቂቃ እየጨመረ ሲመጣ የበለጠ ችሎታዬን እንደማሳይ እርግጠኛ ነኝ።
የወልቂጤ ከተማን ቡድን በቅርቡ ተቀላቅዬ ራሴን ስመለከት ምነው ቀደም ብዬ ወደ ቡድኑ በገባሁ ብዬም ተመኝቻለሁ። ይሄን ያልኩትም የቡድኑ ተጨዋቾች ኳስን ስለሚችሉና እኔም ጥሩ አጋዣቸው እሆናለው ብዬ ስላሰብኩም ነው”።

ስለ እግር ኳስ ጅማሬው፣ ተጫውቶ ስላሳለፈባቸው ክለቦች እና ወደ ቡድኖቹ ስለገባበት መንገድ

“እግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት ተወልጄ ባደግኩበት ጉቶ ሜዳ ላይ ነው። ይኸው ሜዳ ከእኛ ቤት አጠገብም ነበር። ያኔ ብዙዎቹ የሚጫወቱበት ኳስም እኛ ግቢ ውስጥ ዘሎም ይገባ ነበርና እነዚህ ነገሮች እና የአካባቢያችን የቀድሞ ተጨዋቾች እነ ደረጄ /ሊቴ/ ዳዊት ቀለምወርቅ እና እነሱን የመሳሰሉ ሌሎች ልጆችን ሲጫወቱ በማየታችንም ነበር ለኳሱ ጥልቅ ፍቅር አድሮብኝ መጫወትን የጀመርኩት።

በክለብ ደረጃ ለእኔ የመጀመሪያ ክለቤ የደደቢት ታዳጊዎች ነበሩ። እዛ ብገባም ነገሮች ሳይስተካከሉልኝ ሲቀሩ ኳስን አቆምኩ። ከዛም መሀል ባልገባ ስጫወት ያዩኝ አራዳዎች ያለምንም ሙከራ እኔን ለቡድናቸው አስፈረሙኝ። በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ሙከራ የሚባል ነገርን እኔ አልወድም። ምክንያቱም ከ50 ተጨዋቾች ውስጥ አንተ በኳሱ ተሽለህ ልትባረር ትችላለህና ያን ስለማውቅ ወደ አራዳ ያለ ሙከራ ስገባ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። እዛ እንደገባሁም በ2008 ዝዋይ ላይ የብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ነበርና ኮከብ ተብዬ ተሸለምኩኝ። ከዚህ ቡድን በኋላ ቀጥዬ የገባሁበት ቡድን ጅማ አባጅፋር ነው። ወደዚህ ቡድን እንድመጣም ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረጉልኝ በወቅቱ የክለቡ ስራ አስኪያጅ የነበሩት የአሁኑ የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ነበሩና ችሎታዬን አይተው በእሳቸው አማካኝነትም ነበር የገባሁት። እሳቸው ለእኔ ጥሩ ሰው ናቸው ያለኝን አቅሜንም ያውቃሉ። ስለ ወንድሜ አቡበከርም ጥሩ ችሎታ እንዳለው ያኔ ይነግሩኝም ነበር። ያም ሆኖ ግን በዚህ ቡድን ቆይታዬ ላይ ጥሩ ጊዜን ባሳልፍም ጅማን ወደ ፕሪምየር ሊግ ካሳደጉት ተጨዋቾች መካከል አንዱም ብሆንም ከቡድኑ አንድ አካል ጋር በመጣላቴ ክለቡን ልለቅ ቻልኩ። ከጅማ በኋላ ሌሎች የተጫወትኩባቸው ቡድኖች በአሰልጣኝ አስራት አባተ ይመራ የነበረው ቢሾፍቱ ከተማ ነበር። ለዚህ ቡድን ስጫወት አቻ በተለያየንበት ጨዋታ የመጀመሪያ ጎሌንም አስቆጥሬም ነበር። ደጋፊዎቹም ስለኔ በሰሙት ነገር የቀጣይ ጨዋታን ልናደርግ በተቃረብንበት የመጨረሻ ዐርብ ቀን የእርስ በርስ የልምምድ ጨዋታችን ላይ ጉዳትን ላስተናግድ በመቻሌ እና መራመድም ባቃተኝ ሰዓት ላይ ይሄን ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው በወንድሜ አቡበከር አማካኝነት የቡናው ፊዚዮቴራፒ ይስሃቅ ሽፈራው ጋር እየታከምኩ በነበርኩበት ሰዓት ቡድኔ ጋር ለቀናቶች በመቅረቴ እና ማስረጃንም ላቀርብ ብችልም በዚህ ጉዳይ ላይ የእኔን ህመምን ብዙም ሊያምኑት ስላልቻሉ ከክለቡ ጋር ልለያይ ቻልኩ።ወደ ክለቡ መልቀቂያ ልወስድ ስመጣ በድጋሚ የምጫወትበት እድል ነበረኝ። ከዛ በልዩነት ወደዛ ሳልመለስ ለጉለሌ ቡድን ለመጫወት ገባሁኝና የተጫወትኩባቸው ቡድኖች ቆይታዬ እንግዲህ እነዚህን ነው የሚመስሉት”።

በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ትልቅ ደረጃ ላይ ስለመድረስ ራዕዩ

“በዚህ ደረጃ በኳሱ ጥሩ ስፍራ ላይ እንደምደርስ ምንም አይነት ጥርጥር የለኝም። ከላይ ሀሳቤንም ገልጬልሃለሁ። የአንድ እግር ኳስ ተጨዋች ትልቁ ብቃት በራስ መተማመን መቻሉ ነው። ይሄ ደግሞ በተለይ እኛ ቤት ውስጥ በሚገባ ያለ ነው። እኛ ቤት ወደሜዳ ከተገባ በኳስ ልቡ የሚፈራ ማንም የለም። በራሳችን ስለምንተማመንም ነው ሁለቱ ወንድሞቼ አሁን ላይ በትልቁ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ እየተጫወቱ ያሉት እኔም በራሴ ስለምተማመን በቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቴ ከፍተኛ ደረጃም ላይ እደርሳለሁ። ለሌሎች ኳስ ተጨዋቾችም የምመክረው ነገር ሜዳ ሲገቡ በኳስ መጫወቱ ላይ እንዳይፈሩ ነው። አንዳንዶች ገና ሜዳው ተሰምሮ ሲያዩ ኳስ መጫወትን ይፈራሉ። ድህነትን ሳንፈራ እንዴት ነው ኳስን የምንፈራው ብዬም ነው በድጋሚ ልነግራቸው የምፈልገው”።

በመጨረሻ

“እግር ኳስ ለእኔ ህይወቴ እና መዝናኛዬ ጭምር ነው። ኳስን በጣምም ነው የምወደው። የተጨዋችነት ዘመኔ ላይ እዚህ ስፍራ እንድደርስ ብዙዎች ያበረታቱኝ ነበር። አንዳንዶቹም የአካባቢያችን ኳስ ወዳዶች ለእኔ ችሎታ ክብር ሰጥተው ነፍሳቸውን እስከመስጠት የደረሱም ነበሩ። ለምሳሌ ታሪኩ ሀብታሙን ብወስድ ለደደቢት ተተኪ ቡድን ስጫወት በአንድ ጎል 400 ብር ይሰጠኝ ነበር። እሱ መልካም የሆነ ሰው ነው እነ ሙሌ ደረጄና ዳዊት እንደዚሁም ሌሎቹም ለእኔ ልዩ ፍቅር ነበራቸውና እነሱንና ቤተሰቦቼን ለማመስገን እፈልጋለሁ”።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

በ5 ሳምንታት 39 ጨዋታዎች፣ 72 ጎሎችና ከ22.6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተመዘገበ!

በአቤኔዘር አበበ በ2019 ዓ.ም የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ አምስት የውድድር ሳምንታት...