የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለ14 ጊዜ በማንሳት ብቸኛ ክለብ የሆነው ቅ/ጊዮርጊስ ባሳለፍናቸው ሶስት ዓመታት ደግሞ ከእዚህ ድል በመራቅ ለብዙዎች አግራሞትን ፈጥሯል፤ ቅ/ጊዮርጊስ በዘንድሮው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ጅማሬዎቹም ከያዘው ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ አንፃርም በውጤት ደረጃ በሚፈለገው መልኩ መጓዝም ሳይችል ቀርቷል፤ በቡድኑ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ዙሪያ የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከቡድኑ ወጣት ተጨዋች የአብስራ ተስፋዬ ጋር ቆይታን አድርጎ ነበርና ምልልሳቸው በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን በአዲስ አበባ ላይ እና ቅ/ጊዮርጊስን በጅማ ከተማ ላይ በቡድኑ ዙሪያ እስኪ አንድ ነገር ብትል…
“ቡድናችን በአዲስ አበባ ተሳትፎው ጥሩ ቆይታ ነበረው፤ ውጤታችንም እኛ በምንፈልገው መልኩ ባይሆን እንኳ መጥፎ የሚባል አልነበረም፤ ወደ ጅማ ስናመራ ግን ከመጫወቻ ሜዳው አስቸጋሪነት እንደዚሁም ደግሞ በአብዛኛው የዘንድሮ የሊግ ጨዋታዎቻችን ላይ ተጋጣሚዎቻችን ከእኛ ጋር ሊጫወቱ ሲመጡ በመከላከል ላይ ያተኮረን እንቅስቃሴንም ስለሚከተሉም በእዚህና በራሳችንም አንድአንድ ድክመቶች እንዳሳብነው ውጤት ከማምጣት ጋር ሊሳካልን አልቻለም”፡፡
ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ብዙዎች ባልጠበቁት መልኩ ቅ/ጊዮርጊስን ውጤት እያሳጣው ይገኛል፤ አባባሉ ያስማማሃል…?
“አዎን፤ ብዙ ነገሮችም እንደሚጠበቁብን ያሳየም ነው፤ ክለባችን ካለው ስምና ዝና አንፃር እንደዚሁም ደግሞ ካሰባሰብነውም ምርጥ ተጨዋቾቻችን አኳያ ውጤት ማታጣችን ለእኛ የማይጠበቅም ነው የሆነብንና ለዛም ነው አባባሉ ሊያስማማኝም የቻለው፤ ከዚህ በመነሳት ግን ይህ ውጤት የእኛን ቡድን ፈፅሞ የማይመጥነው እና ሊያጋጥመውም የማይገባም ነው ብለን ስላመንም ባለፉት ጨዋታዎቻችን ላይ በነበሩብን ክፍተቶች ላይ በመስራት ከባህርዳር ከተማ ጀምሮ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤትን ለማስመዝገብ እና ወደ ላይም ልንነሳ እየተዘጋጀን ነው የምንገኘው”፡፡

በባህርዳር ከተማ ላይ ለምታደርጓቸው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ከእረፍት መልስ በመምጣት ስታደርጉት ስለነበረው ዝግጅት
“በአዲስ አበባ እና በጅማ ከተማ ላይ ያደረግናቸውን የሊግ ጨዋታዎቻችንን ካጠናቀቅን በኋላ ክለባችን የሰጠንን የእረፍት ጊዜ በአግባቡ በመጠቀምና ወደ ልምምዳችንም በመመለስ ለባህርዳሩ ቀጣይ ጨዋታዎቻችን ስናደርግ የነበረው ዝግጅት በጣም ጥሩ የነበረ ነው፤ ጠንካራ ልምምዶችንም ነበር ስንሰራ የነበረው፤ ከዛም በመነሳት ነው በቀጣይነት ለምናደርጋቸው እያንዳንዱ ጨዋታዎቻችን የተሻሉ ነገሮችን ልንሰራና ጥሩ ውጤትንም ልናስመዘገብም እየተዘጋጀን የምንገኘው”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን የገጠመው የውጤት ማጣት ጊዜያዊ ነው? ወይንስ ዘለቄታዊ….
“ጊዜያዊ ነው፤ ምክንያቱም ጠንካራ እንደዚሁም ደግሞ ጥሩ እና በቀጣይ በምናደርጋቸው ጨዋታዎቻችን ላይም ወደ አሸናፊነት መንፈስ በፍጥነት ሊመለስ የሚችል ውጤታማ ቡድን እንዳለን እናምናለንና ለዛም ስንል ቡድናችን ውስጥ የነበሩትን አንድአንድ ችግሮቻችንን እንደ ቡድን በመነጋገር የፈታናቸው ስለሆኑና ክፍተቶቻችንን ስላወቅን እንደዚሁም ደግሞ እስካሁን አውጥተን የተጫወትነው አቅምም በቂ ነውም ብዬ ስለማላስብም ሰሞኑን እየሰራን ካለነው ጥሩ ልምምድ አንፃር ራሳችንን እንደተመለከትኩት ቀጣዩ ጊዜ ለቡድናችን ብሩዕም ነው የሚሆንልን”፡፡
በባህርዳር ከአዳማ ከተማ ጋር ስለምታደርጉት ቀጣይ የሊግ ጨዋታ
“ከእዚህ ጨዋታ የድል ውጤት ያስፈልገናል፤ እሱ ብቻ ግን በቂ አይደለም፤ በእዚህ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ከአሁን በኋላ በምናደርጋቸው እያንዳንዱ ጨዋታዎች ውጤቱ ያስፈልገናልና ለሁሉም ቡድኖች እኩል ትኩረት ሰጥተን በመግባት በደረጃ ሰንጠረዡ ወደላይ ለመነሳት እና ወደመሪነቱ ለመምጣት ተዘጋጅተናል”፡፡
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ፋሲል ከነማ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኙትን እናንተን በ7 ነጥብ ርቆ መሄዱ አያስፈራችሁም….
“በፍፁም፤ እንደውም እነሱ ናቸው ቅ/ጊዮርጊስ ብዙ ጊዜ ከኋላ ተነስቶ መምጣትን የለመደ መሆኑን ስለሚያውቁ የሚፈሩን፤ እኛ እነሱንም ሆነ ሌላውንም ቡድን መቼም ፈርተንም አናውቅም”፡፡
ለቅ/ጊዮርጊስ በቋሚ ተሰላፊነት በማትገባበት ሰዓት ምን አይነት ስሜትን ነው የምታስተናግደው
“ቅ/ጊዮርጊስ በሚያደርጋቸው ማንኛውም ጨዋታዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሳልገባ ስቀር ሁሌም ቢሆን የማኮርፍ ወይንም ደግሞ ጥሩ ያልሆነ ስሜት የሚሰማኝ ተጨዋች ስላልሆንኩ የሚመጣውን ሀገር ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፤ በእዚህ ቡድን ውስጥ እስካለው ድረስም በማልሰለፍበት ሰዓት ነገ ይሄን እድል ላገኝ እንደምችል ስለማውቅ ተስፋ የማደርገው ብዙ ነገርም አለኝም፤ ምክንያቱም ቅ/ጊዮርጊስ አሁን የያዘው ስኳድ በጣም ሰፊ ነው፤ ተመጣጣኝ ችሎታ ያላቸውን ልጆች የያዘ እና እንደ ቡድንም የሚንቀሳቀስም ነው፤ ይሄን ስላወቅኩም የመጫወት ዕድሉን በተደጋጋሚ ጊዜ አገኛለው ብዬ ስለማምን ያን ወቅት በጉጉት እየጠበቅኩኝ ነው”፡፡

ከቅ/ጊዮርጊስ የውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ በቡድኑ ዙሪያ ያወራችሁት ነገር ምንድን ነበር? እከሌ መሰለፍ አለበት፤ እንትና ቢገባ የሚል ነገርን አንስታችኋል?
“አሰላለፍን በተመለከተ ይሄ የአሰልጣኙ እንጂ የእኛ ስራ ስላልሆነ በእዚህ ዙሪያ እንትና ወደ ሜዳ ተሰልፎ ይግባ እከሌ ይቀመጥ በሚል አልተነጋገርንም፤ ምክንያቱም አሰልጣኙ ለፈለገው እና ይጠቅመኛል ለሚለው አጨዋወት የሚጠቀምባቸውን ልጆች እያሰለፈ ይገኛል፤ ወደ እኛ ቡድን ስታመራም ሁሉም ተጨዋች ተመሳሳይ ችሎታ እና ኳሊቲም ስላለው በዛ መልኩም ነው ተጨዋቾችን በማሰለፍ እየተጠቀመባቸው የሚገኘው፤ ከውጤት ማጣታችን ጋር በተያያዘ ባለፈው ጊዜ ወደ ልምምድ ከመግባታችን በፊት በቡድኑ ዙሪያ ተነጋግረናል፤ ቅ/ጊዮርጊስ የማይገባውን ውጤት ሊያስመዘገብ እንደቻለም ተረድተናል፤ ይሄ ያስቆጫል፤ ጥሩ ያልሆነ ስሜት እንዲሰማንም አድርጎናልና ከዛ ተነስተን ነው ደጋፊዎቻችንን በውጤት ለመካስና የቅ/ጊዮርጊስንም ሀያልነትን በድጋሚ ለመመለስ እየተጋን የሚገኘው”፡፡
አስተያየት ይስጡ