መነሻ ገጽ አፍሪካ “በኮንፌዴሬሽን ካፑ ምድብ ድልድል ውስጥ መግባትናየሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አቅደናል”ወንድሜነህ ደረጄ /ኢትዮጵያ ቡና/
አፍሪካኢትዮጵያ ቡናኮንፌድሬሽን ካፕዜናዎች

“በኮንፌዴሬሽን ካፑ ምድብ ድልድል ውስጥ መግባትናየሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አቅደናል”ወንድሜነህ ደረጄ /ኢትዮጵያ ቡና/

አጋራ
አጋራ

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ውዲቷ ሀገራችንን በመወከል የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ቡና የፕሪ-ሲዝን ዝግጅቱን ከጀመረ የቀናቶች እድሜን ያስቆጠረ ሲሆን ከኡጋንዳው ክለብ ዩጋንዳ አር ኤ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታም መስከረም 2 ቀን ያካሂዳል፤ ኢትዮጵያ ቡና ለእዚህ ውድድርና ለመጪው ዓመት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ዝግጅቱን በምን መልኩ እያከናወነ ነው? ከውድድሮቹ ምን ውጤትንስ ማግኘት ያልማል? የቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብ ምን ይመስላል? በሚለውና ራሱስ በምን መልኩ ለመጪው የውድድር ዘመን ተሳትፎ ሊቀርብ ተዘጋጅቷል? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ  ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለቡድኑ የተከላካይ ሰፍራ ተጨዋች ወንድሜነህ ደረጄ አቅርቦለት ተጨዋቹ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶታል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና እያደረገ ስላለው የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት

“የእስካሁኑ የዝግጅት ጊዜ ልምምዳችን ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡት ተጨዋቾቻችን ካለባቸው ሀገራዊ ተሳትፎ አኳያ ባይቀላቀሉንም ጠንከር ባለ መልኩ ዝግጅታችንን በጥሩ መልኩ እየሰራን ነው፤ ይህ ዝግጅታችን በተለይ ያተኮረው በቅርብ ለሚጠብቀን የኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎአችንም ስለሆነ ደስ በሚል መልኩም ነው እየሰራን የምንገኘው”፡፡

በዝግጅታቸው ወቅት ምን ላይ ያተኮረ ልምምድን እየሰሩ እንደሆነ

“ከእረፍት የመጣን እንደመሆኑ የአሁኑ ዝግጅታችን ያተኮረው ለኢንተርናሽናሉ ግጥሚያ ነው፤ ለዛም ጨዋታ ቡድናችን የኡጋንዳውን ቡድን የሚገጥመው በአርቴፊሻል ሜዳ ላይም እንደሆነ ስላውቅንም ከኳስ ጋር የተያያዘን ጠንከር ያለ ልምምድን ነው እየሰራን የሚገኘው፤ ከእዚህ ልምምድ ውጪም የአቋም መለኪያ ግጥሚያንም ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያደረግንበት ሁኔታም ስለነበርና በዛም ላይ ጥሩ ነገርንም በቡድናችን ላይም ስለተመለከትን ይህ ልምምዳችን ቀጣይነትም የሚኖረው ነው”፡፡

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ከኡጋንዳው ክለብ ጋር ስለሚያደርጉት ጨዋታና ሊያስመዘግቡት ስላሰቡት ውጤት

“ይህን ጨዋታ የምናደርገው የደርሶ መልሱን ግጥሚያ አሸንፈን ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ነው፤ ከዚህ ጨዋታ በኋላ ደግሞ የዕለት የዕለት ጨዋታችንን እያሰብን በመጓዝ ክለቡ ሁሌም የሚያልመውን ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረን እንሰራለን”፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በኮንፌዴሬሽኑ ካፕ ስለሚፋለመው የተጋጣሚው ቡድን አቋም ምን ያውቅ እንደሆነ

“የኡጋንዳውን ክለብ ወቅታዊ አቋም በተመለከተ ልክ የዕጣ ድልድሉ ከእነሱ ጋር ሲደርስን ባየናቸው አንድ አንድ ቪዲዮች ስለ ቡድኑ ያወቅናቸው ነገሮች አሉ፤ ከእነዛም መካከል ክለቡ የቆሙ ኳሶች ላይ መጠቀምን ይችላል፤ ከዛ ውጪም ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወትም ይሞክራሉ ይሄን በሚገባ አይተናል፤ የእኛ ቡድን ግን ሁሌም ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የሚነሳው ከራሱ አቋም በመሆኑ በዛ ላይ ትኩረት አድርጎ ነው ተጋጣሚውን በምን መልኩ መርታት እንዳለበት ወደ ውድድር የሚገባውና ለዛ የጨዋታውን መድረስ እየተጠባበቅን ነው የሚገኘው”፡፡

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎአቸው ሊያስመዘግቡት ስላሰቡት ውጤት

“ይሄ ዛሬ የታቀደ አይደለም፤ ከ1990ዎቹ ጅማሬ አንስቶም ነው ኢትዮጵያ ቡና የግብፁን አልአህሊ ከውድድር ካስወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ምድብ ድልድል ውስጥ መግባትን እያለመ የሚገኘውና የእዚህ ዓመት እልማችንም ይኸው ነው”፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ከኢንተርናሽናል ተሳትፎው ውጪ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉስ ምን ውጤትን ማግኘት ያልም እንደሆነ

“ይሄ ሁሌም የታወቀ ነው፤ ቡና የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ ስለሆነ ዋንጫ ማግኘትን አቅዶ ነው የሚነሳው፤ ሌሎች ውጤቶች በቡድናችን ያን ያህል ተቀባይነት ያላቸው አይመስለኝም፤ ክለቡ ምንአልባት ዋንጫ ባያነሳ እንኳን በኢንተርናሽናል ጨዋታ ላይ ሁለተኛም ሆኖ መሳተፍን ይፈልጋል፤ እንደዛም ሆኖ ግን የእኛ እቅድ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ማንሳት ነው፤ ዘንድሮ ጥሩ ጉዞን እያደረግን ነበር፤ የተማርናቸው ነገሮችም አሉ፤ አሁን ስህተቶቻችንን ቀንሰን በመምጣት እልማችንን ማሳካት የግድ ይለናል”፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ለመጪው ዓመት ተሳትፎው አቡበከር ናስርን ከማግኘቱና ከማጣቱ ጋር በተያያዘ

“አቡኪ ከእኛ ጋር ቢኖር በጣም ጥሩ ነው፤ አብሮን ቢጫወትም ብዙ ይጠቅመናልና ደስ ይለናል፤ በሌላ በኩል ስታየው ደግሞ የልጁ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እልሙ ከተሳካም ጥቅሙ ለእሱም ለሀገርም ጭምር ስለሆነ ያ እንዲሳካለት ምኞቴ ነውና የምከፋበት ነገር አይኖረኝም”፡፡

ስለ ቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብና በካምፓቸው ውስጥ ስላለው የቡድን መንፈስ

“በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በአሁን ሰዓት የሚታየው የቡድን መንፈስ በጣም ጥሩ ነው፤ ነባርና አዳዲስ ተጨዋቾቹ በመግባባትና በመከባበር ጥሩ ጊዜንም እያሳለፉ ነው፤ በተለይም ደግሞ እኛ ነባሮቹ አዲሶቹን ስለ ክለቡ ብዙ ነገሮችን እየነገርናቸውና እያሳወቅናቸውም ስለሆነ በፍጥነት እየተግባባንም ነውና ያለን ነገር ጥሩ የሚባል ነው፤ ስለ ቡድናችን የተጨዋቾች ስብስብ በሚመለከት ደግሞ ቡና ብዙ ተጨዋቾቹን አለመልቀቁ በጥሩነት የሚጠቀስለት ነው፤ ሊጠቅሙን የሚችሉ አዳዲስ ተጨዋቾችንም ወደ ክለቡ አስመጥቷልና ያለን ስብስብ በጥሩ መልኩ ሊገለፅ የሚችል ነው”፡፡

በኢትዮጵያ ቡና በሚኖረው የመጪው ዓመት ቆይታ በምን መልኩ ለመቅረብ እንደተዘጋጀ

“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ እኔ ሁሌም ቢሆን ባለፉ ነገሮች ላይ የምቆጭ ተጨዋች ስላልሆንኩኝና ራሴንም ከዓመት ወደ ዓመት ለማሻሻል የምተጋ ተጨዋች ስለሆንኩኝ በመጪው ዓመት ላይ በሚኖረኝ የውድድር ዘመን ተሳትፎዬ በጥሩ ብቃት ላይ ለመቅረብና ክለቤንም ለስኬት ለማብቃት ነው እየተዘጋጀው የምገኘው፤ በኳስ ጨዋታ ትልቁ ነገር ስህተትን መቀነስ ነው፤ ስህተትን የቀነሰ ተጨዋችና ቡድን ደግሞ የልፋቱን ያገኛልና በአዲሱ ዓመት በምርጥ ብቃቴ ላይ እንደምገኝ እርግጠኛ ነኝ”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከዘንድሮ በተሻለ መጪው ዓመት ላይ እንመለከተው እንደሆነ

“ይሄን በሚገባ ነው የምጠብቀው፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ውድድር በመነሳት ነው ስራን የምትሰራውና፤ ጨዋታዎቻችን በዲ.ኤስ. ቲቪ መተላለፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተጨዋቾቻችንና ክለቦቻችን በብዙ ነገሮች እየተጠቀሙ ነው፤ ከዚህ ብዙ ትምህርት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተወስዷልና የተሻለ ነገርን የምንመለከት ይመስለኛል”፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ሸገር ከተማ) : ክለቡ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የ26ኛ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...