”በ2014 የዉድድር አመት የተሻለውን ታፈሰ ሰርካ ጠብቁ”
”በቀጣዩ አመት አዳማ ከተማ ከ1 እስከ 5 ባለዉ ደረጃ ያጠናቅቃል”
በዘንድሮው የዉድድር ዓመት ምንም እንኳን ክለቡ አዳማ ከተማ ከሊጉ ቢወርድም በግሉ ጥሩ የሚባል የዉድድር ጊዜን ያሳለፈው ተከላካዩ ታፈሰ ሰርካ ባሳለፍነው ረቡዕ ክለቡ አዳማ ከተማ በቀጣይ ዓመት የትግራይ ክልል ክለቦች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የማይመዘገቡ ከሆነ እነርሱን ተክቶ በሊጉ የሚሳተፈው አንዱ ቡድን ስለመሆኑ፤ በደረሰበት ሀዘን ምክንያት የሚወደዉን ክለብ በሀዋሳዉ ዉድድር ላይ ማገልገል ስላለመቻሉ፤ በቀጣይ አመት ከክለቡ አዳማ ከተማ ጋር ስለሚኖረዉ ቆይታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሀትሪኩ ፀሀፊ ኤርሚያስ ምስጋናዉ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርጓል።
ሀትሪክ:- በቅድሚያ ቡድንህ አዳማ ከተማ በማሟያ ውድድሩ ላይ አስቀድሞ በማለፉ እንኳን ደስ አለህ?
ታፈሰ:- አመሰግናለሁ! እንኳን አብሮ ደስ አለን።
ሀትሪክ:- የ2013 የውድድር አመትን እንዴት አሳለፋችሁት ፣ ምንስ ይመስል ነበር?
ታፈሰ:- ያው… የ2013 የውድድር አመት ለኛ ትንሽ ይከብድ ነበር፤ የተወሰነ ጫና ቢኖርብንም የራሳችንን ጥረት አድርገን ነበር፤ ነገር ግን ቲሙን ለማትረፍ አልቻልንም። ከዛም በኋላ ቡድኑ ወርዷል ሲባል እኛም እንደ ተጫዋች ቅር ብሎን ነበር።
ሀትሪክ:- DSTV ወደ ሀገራችን እግርኳስ በመምጣቱ ምን ተሰማህ?
ታፈሰ:- የDSTV ወደ ሀገራችን መምጣት በተለይ ለተጫዋቾቹ በጣም ደስ የሚል ነገር ነዉ። እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት DSTV ባለመኖሩ ተጫዋቹ ብዙም የእይታ እድልን አያገኝም ነበር፤ ይሄም ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ አሰልጣኞች ስታዲየም እየመጡ ተጫዋቾችን አይመለከቱም ነበር፤ አሁን ግን ሁሉም አሰልጣኝ በየቤቱ ቁጭ ብሎ ጨዋታዎችን የመመልከት እድል አጊኝቷል ደጋፊዎችም እንደዛዉ በዚህም በጣም ነዉ ደስ ያለኝ።

ሀትሪክ:- DSTV መጥቶ ባነቃቃዉ እግርኳሳችን ላይ ለዚያውም በመጀመሪያው አመት አዳማ ከተማ ከሊጉ መዉረዱ ምን አይነት ስሜትን ፈጠረብክ?
ታፈሰ:- እንዳልከዉ በዚህ ጊዜ ከሊጉ በመዉረዳችን በጣም ነበር የከፋኝ የሚገርምህ ነገር ብዙ ጊዜ ከተጫዋቾቹ ጋር ስለ ድክመታችን ለመነጋገር ሞክረናል፤ ነገር ግን ምን እንደሆነ ልናዉቀዉ አልቻልንም ነበር ሜዳ ዉስጥ እንደማንኛውም ቡድን ለማሸነፍ ነዉ የምንገባው ወደ ሜዳ ከገባን በኋላ ግን ምን እንደሚፈጠር አናዉቅም ያዉ በጨዋታ ሂደት ማሸነፍ፤መሸነፍ፤አቻ መዉጣት ያለ ነገር ነዉ። ነገር ግን በቃ ወደ ሜዳ ከገባን በኋላ ማሸነፍ ያቅተናል ምክንያቱ ምን እንደሆነ አላዉቅም።
ሀትሪክ:- በ2013 የዉድድር አመት ፋሲል ከተማ ሻምፒየን መሆኑን እና አቡበከር ናስር ኮከብ ተጫዋች መባሉን እንዴት አገኘኸዉ?
ታፈሰ:- አቡበከር ኮከብ ተጫዋች መባሉ ይገባዋል ባይ ነኝ! ያዉ ወጣትም እንደመሆኑ መጠን ከዚህ ባለፈ ደግሞ ለወደፊቱ በጣም ተስፋ ያለዉ ጥሩ ተጫዋች ነዉ፤ እዚህ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ወጥቶ የመጫዎት ብቃት አለዉ ብየ አምናለሁ። እዚህ ጋር ማሰብ ያለብን ነገር ግን አቡበከር ሰርቶ እና በደንብ ተዘጋጅቶ ስለመጣ ነዉ ጎልቶ መዉጣት የቻለዉ።
ሀትሪክ:- ስለ ፋሲል ከተማ ሻምፒዮንነትስ?
ታፈሰ:- ፋሲል ዋንጫዉን ለማንሳቱ ምክንያት ብየ የማስበው ነገር ስብስቡ ይመስለኛል ጥሩ የሚባል የቡድን ስብስብ አላቸዉ። መጀመሪያ አካባቢ መንገጫገጭ ገጥሟቸው ነበር ከዛ ቡኃላ ግን ዉጤቱን አስተካክለው ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ዋንጫውን ለማንሳት ችለዋል።
ሀትሪክ:- በተጫዋችነት ዘመንህ አብሬዉ ብጫዎት ብለህ የተመኘኸዉ ተጫዋች ይኖር ይሆን?
ታፈሰ:- አዎ በጣም የማደንቃቸው ተጫዋቾች አሉ። ለምሳሌ አዳነ ግርማ እና ሽመልስ በቀለ አብሬያቸዉ ብጫወት ብየ አስቤ አዉቃለዉ አበባዉ ቡጣቆም ሌላኛው የማደንቀዉ ተጫዋች ነዉ። ሶስቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ እያሉ እመለከታቸዉ ነበር ነገር ግን አሁን ላይ ከእነሱ ጋር የመጫወት እድል እንደሌለኝ አዉቃለሁ።

ሀትሪክ:- በ2013 የዉድድር አመት ያሳየኸዉ ብቃት የአቅሜ ጣራ ነዉ ብለህ ታስባለህ ወይስ በ2014 የተሻለዉን ታፈሰ ሰርካ እንጠብቅ?
ታፈሰ:- ኧረ እንደዉም በዚህ አመት ያለኝን አቅም አዉጥቼ አላሳየሁም ብየ ነዉ የማስበዉ፤ በተለይ DSTV እንደመኖሩ መጠን የኔም አቅም በሚገባ ታይቷል የሚል እምነት የለኝም፤ ነገር ግን እንዳልከዉ ከዚህ በኋላ በሚገባ ሰርቼ የተሻለ ነገር እንደማሳይ በጣም እርግጠኛ ነኝ።
ሀትሪክ:- በ2013 የዉድድር አመት እንደ ተጫዋች ማሳካት ፈልገህ ያላሳካኸዉ ወይም የምትቆጭበት ነገር ምን ይሆን ?
ታፈሰ:- እንደ ተጫዋች የምታስበዉ እና የምታቅደዉ ነገር ይኖራል፤ እኔ አላደረግኩትም ብየ የምለዉ ነገር ቢኖር ተከላካይ እንደመሆኔ መጠን አልፎ አልፎ ወደ ማጥቃቱ እየሄድኩ ግብ ማስቆጠር እፈልግ ነበር፤ በምፈልገው መጠን ይሄንን አድርጌያለሁ ብየ አላስብም ነገር ግን እንዳሰብኩት ባይሆንም በዉድድር አመቱ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችያለው ያም ብቻ ሳይሆን ለጎል የሚሆን ኳስ ማቀበልም ችየ ነበር።

ሀትሪክ:- አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ምን ጨምሮልኛል ብለህ ታስባለህ?
ታፈሰ:- በሚገባ አሰልጣኝ ዘርዓይ ትልቅ ነገርን ጨምሮልኛል ብየ አስባለሁ፤ ያዉ እንደሚታወቀው አሰልጣኝ ዘርዓይ ወደ አዳማ ሲመጣ የራሱን ፍልስፍና እና የአጨዋወት መንገድ ነዉ ይዞ የመጣው ከእርሱ በፊት ከነበረዉ አሰልጣኛችን የተለየ ነገርን ጨምሮልኛል የምለዉ በተደጋጋሚ ያለኝን አቅም አዉጥቼ እንድጫወት ይመክረኝ ነበር በተጨማሪም ለኛ ለተጫዋቾች ያለዉ ክብር በጣም ደስ የሚል ነዉ።
ሀትሪክ:- ሀዋሳ ላይ እየተደረገ በሚገኘዉ የሟሟያ ዉድድሩ ላይ ያለፋትን ጨዋታዎች መገኘት አልቻልክም ነበር ምክንያቱ ምን ይሆን?
ታፈሰ:- በዚህ ዉድድር ላይ ጥሩ ነገርን አሳያለሁ ብየ አስቤ ነበር፤ የተለያዩ አሰልጣኞችም ጨዋታዎችን መመልከታቸዉ ስለማይቀር እኔም እራሴን በደንብ ለማሳየት ተዘጋጅቼ ነበር ነገር ግን በአጋጣሚ አባቴን በሞት ተነጠኩ ከባድ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት ከዚህ በፊትም አባቴ ታሞ እያለ ከኤሌትሪክ ጋር ስንጫዎት በጣም ተረብሼ ነበር ጭራሽ የጨዋታዉን ሂደት መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ ሁሉም ነገር ጠፍቶብኝ ነበር ብቻ በጣም ይከብድ ነበር ያዉ ሁሉም ሰዉ ላይ የሚያጋጥም ነገር ቢሆንም፤ በዚህ ምክንያት ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች መገኘት አልቻልኩም ነበር።

ሀትሪክ:- በጨረሻም በቀጣይ የስፖርት ቤተሰቡ በተለይ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች ካንተ ምን ይጠብቁ?
ታፈሰ:- ያዉ እርግጠኛ ሁኜ የምነግርህ ነገር ቀጣይ አመት አዳማ ከተማን በእንደዚህ አይነት ደረጃ እንደማንመለከተዉ ነዉ። ከአመራሮቹም ጋር ስላወራንበት ቢያንስ በቀጣይ አመት ከ1 እስከ 5 ባለዉ ደረጃ ዉስጥ እንደምናጠናቅቅ እምነት አለኝ። እኔም በግሌ በደንብ ሰርቼ እና በሚገባ ተዘጋጅቼ የተሻለ ነገርን ለአዳማ ከተማ ለመስጠት ነዉ የማስበዉ።
አስተያየት ይስጡ