መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ “በወላይታ ድቻ የቀድሞ ስምና ዝናዬን እንደምመልስ እርግጠኛ ነኝ” ምንይህሉ ወንድሙ /ወላይታ ድቻ/
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግወላይታ ድቻዜናዎች

“በወላይታ ድቻ የቀድሞ ስምና ዝናዬን እንደምመልስ እርግጠኛ ነኝ” ምንይህሉ ወንድሙ /ወላይታ ድቻ/

አጋራ
አጋራ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ላሳደገው ክለብ መከላከያ ጨምሮ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለባህርዳር ከተማ ክለብ ተጫውቶ አሳልፏል፤ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቹ ምንይህሉ ወንድሙ በመከላከያ ክለብ ውስጥ በነበረባቸው የውድድር ጊዜያቶች ውስጥም ካለው ችሎታ አንፃር ጉዳት ከሜዳ አርቆት በሚፈልገው የላቀ ደረጃ ላይ እንዳይገኝ ቢያደርገውም ለክለቡ ግን በርካታ ግቦችን በማስቆጠር በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ተደናቂነትን አትርፏል፤ ባሳለፍነው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ላይ ለባህርዳር ከተማ በበርካታ ግጥሚያዎች ላይ የመሰለፍ እድልን ባያገኝም ለቡድኑ 5 ያህል ግቦችን በማስቆጠር ተሸሎ የታየው ይኸው ተጨዋች በክረምቱ ወራት የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት አዲሱን ክለቡን ወላይታ ድቻን ሊቀላቀል የቻለ ሲሆን ይህን ተጨዋች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ በዝውውር ሂደቱ ዙሪያና ስለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እንደዚሁም ደግሞ ከራሱ ጉዳዮች ጋርም በማያያዝ አጠር ያሉ ጥያቄዎችን አቅርበንለት የሚከተለውን ምላሽ ሊሰጠን ችሏል፡፡

ሀትሪክ፡- ከሳምንታቶች በፊት ምንይህሉ ወደ ወላይታ ድቻ ማምራቱ ተነግሯል፤ በዝውውሩ ክለቡ ቀዳሚ ምርጫህ ነበር?

ምንይህሉ፡- አዎን፤ እነሱ አቅሜን ስለሚያውቁ በጣም ይፈልጉኝ ነበር፤ ከመጀመሪያው አንስቶም ያወሩኝም ነበር፤ ከአሰልጣኙ ጋርም ጥሩ ቅርርብ ስለነበረንና የእሱም ተመራጭ ተጨዋች ስለሆንኩኝ የውል ጊዜዬን ከባህርዳር ከተማ ክለብ ጋር እንዳጠናቀቅኩኝና ከእነሱ ጋር እንደተለያየሁኝ የወላይታ ድቻ ተጨዋች መሆኔን በፊርማዬ አረጋገጥኩኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለአንተና ለክለባችሁ ዘንድሮ እንዴት አለፈ?

ምንይህሉ፡- የውድድር ዘመኑ ተሳትፎአችን በእኔ አመለካከት የሚመጥነንን ውጤት ለክለባችን ያስመዘገብንበት አልነበረም፤ ቡድናችን ስኬታማ ለመሆን ጥሩ አቅም ነበረው፤ ጉዞውንም እያሳመረ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን የውጤት መንገጫገጭ እያጋጠመው በመምጣቱ በሚፈልገው ደረጃ ስኬትን ሊያስመዘግብ አልቻለም፤ እንደ ግል የእኔን የውድድር ጉዞ በተመለከተ ደግሞ በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ላይ ዘንደሮ በቋሚ ተሰላፊነት ለመጫወት አልቻልኩም፤ የክለቡ አሰልጣኝ የመጀመሪያ ተመራጭ ስላልነበርኩም ነው በተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ያም ሆኖ ግን ተቀይሬ በገባሁባቸው ጨዋታዎች ጭምር 5 ያህል ጎሎችን ለቡድኑ በማስቆጠር ከሚሰለፉት ተጨዋቾች በተሻለ መልኩ ውጤታማ ተጨዋች የሆንኩበት ጊዜ ነበርና ይህንን በጥሩ መልኩ ነው የምገልፀው፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ወላይታ ዲቻ ከማምራትህ አኳያ በአዲሱ የውድድር ዘመን አንተንና ክለባችሁን በምን መልኩ እንጠብቃችሁ?

ምንይህሉ፡- ወላይታ ዲቻን በመጪው የውድድር ዘመን እንዲህ ባለ መልኩ ይቀርባል ብሎ መገመት ከወዲሁ አስቸጋሪ ቢሆንም ይህ ክለብ ዘንድሮ ወጣት ተጨዋቾችንና በኋላም ላይ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች በማካተት ተስፋ ሰጪ ነገርን አስመልክቷል፤ ከዚህ በመነሳት የሚታይ ጥሩ ነገር አለና ይህን ቡድን በጋራ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፤ በወላይታ ዲቻ በሚኖረኝ ቆይታ እኔን በተመለከተ በአዲሱ የውድድር ዘመን ላይ ቀድሞ በመከላከያ ክለብ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት የነበረኝን ምርጥና ወጥ የሆነን ብቃት ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ዳግም ለእዚህ ቡድን የማስመለክት ይመስለኛል፤ ይህን ስል ደግሞ ያለ ምክንያት አይደለም፤ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ባህርዳርን ስቀላቀል አስቀድሞ የመቐለ 70 እንደርታ ተጨዋች ስለነበርኩና ቡድኑ ካጋጠመው ፈተና ጋር በተያያዘም በቂ የሆነን የዝግጅት ጊዜ ልምምድን ከባህርዳር ከተማ ጋር ስላልሰራውኝ የተወሰነ ክፍተት ነበረብኝ፤ አሁን ግን ከወዲሁ በግል ወደ ልምምድ ስለገባውና ወደ ክለቤም በመቀላቀል የፕሪ-ሲዝን ልምምድንም የምሰራበት ጊዜ ሩቅ ስላልሆነ የተሳካ የውድድር ዘመንን ከወላይታ ዲቻ ጋር እንደማሳልፍ በጣሙን እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ያሳለፍካቸውን ያለፉት ጊዜያቶች ዛሬ ላይ ሆነህ እንዴት ትመለከታቸዋለህ?

ምንይህሉ፡- በእግር ኳስ ህይወቴ ደስ የሚሉም፤ በፈተና የታጀቡም ጊዜያቶችን ነው ባለፉት ዓመታቶች ያሳለፍኩት፤ በብዙ ነገሮች ተፈትኜም መምጣቴ ለእኔ ብርታት ሆኖኝ ኳሱን አሁን ላይ ደስተኛ ሆኜ እንድጫወትበት እያደረገኝም ነውና በዚሁ ውስጥ ስላለፍኩ ደግሞ በቀጣዩ ጊዜ የኳስ ቆይታዬ ከአሁን በተሻለ መልኩ ለክለቤ ጥሩ ነገርን ለመስራት በበቂ ሁኔታ እየተዘጋጀው ነው የምገኘው፡፡

 

ሀትሪክ፡- በፈተና የታጀቡትና በጥሩ መልኩ ያሳለፍካቸው የኳስ ጊዜያቶችህ የትኞቹ ናቸው?

ምንይህሉ፡- የኳስ ዘመኔ ላይ ለእኔ ምርጡና ጥሩ ጊዜያቶችን ያሳለፍኩት በሰባት ዓመታት የመከላከያ ክለብ ቆይታዬ ለአንድም ቀን ቤንች ተጨዋችነትን ሳላውቅ በወጥ አቋም ላይ ሆኜ በቋሚ ተሰላፊነት ለቡድኑ በመጫወት ስኬታማ ጊዜን ያሳለፍኩበትን ሲሆን በፈተና የታጀቡ አስከፊ ጊዜያቶችን ያሳለፍኩት ደግሞ የመጀመሪያው ለመከላከያ በምጫወትበት ሰዓት በአንድ ወቅት የገጠመኝ የእግር ጉዳት ከሜዳ ያራቀኝ ስለነበርና በተለይም ደግሞ አንዴ የፕሪምየር ሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነት እየመራው በነበርኩበት ሰዓት ላይም ይህ ጉዳት ከሜዳ እንድቀር ስላደረገኝ ከዛ ውጪ ደግሞ ዘንድሮ በነበረኝ የባህርዳር ከተማ ክለብ ቆይታዬም የተጠባባቂ ተጨዋች ሆኜ ብዙ ልጫወት ስላልቻልኩ እነዚህን በፈታኝነት የምጠቅሳቸውና የሚያስቆጩኝ ጊዜያቶች ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የፋሲል ከነማን ሻምፒዮናነትና የዚትዮጵያ ቡናውን አቡበከር ናስርን የጣምራ ኮከብነት ሽልማት በምን መልኩ ነው የምትገልፀው?

ምንይህሉ፡- የፋሲል ከነማ የዘንድሮ የተጨዋቾች ስብስብ በጣም ሰፊ ከመሆኑ ባሻገር በቡድኑ ውስጥ የነበረው የአሸናፊነት ስሜት ከፍ ያለ ስለነበር የእዚህ ዘመን ውጤቱ ከልፋታቸው አንፃር የሚገባቸው ናቸው፤ አቡበከርን በተመለከተ በሁሉም ነገር በየጨዋታዎቹ ታታሪ ሆኖ ነው ኳሱን የሚጫወተው፤ አሁን ካለው ብቃት በተሻለ ደረጃ መጫወትም ይችላል፤ በቀጣይነት ሀገራችን ጭምር ከእሱ ብዙ ነገርንም ትጠብቃለችና በኮከብነቱ ስለሚገባው በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በርታም ነው የምለው፡፡

ሀትሪክ፡- በመከላከያ በነበርክበት ሰዓት በእግር ኳስ ችሎታህ ከነበረህ ስምና ዝና አንፃር ያንን ብዙ ማስቀጠል አልቻልክም ነበር….?

ምንይህሉ፡- እውነት ነው፤ በፊት ምንይህሉ፣ ምንይህሉ የሚለው ስም በተደጋጋሚ ጊዜ ይጠራ ነበር፤ በኋላ ላይ ያጋጠመኝ ጉዳት ግን ከሜዳ አርቆኝ ስለነበር በበፊቱ ደረጃ ስሜ ሊጠራ አልቻለምና መጀመሪያ ላይ በጣም ይቆጨኝ ነበር፤ በኋላ ላይ ሳስበው ግን ፈጣሪ ያልፈቀደው ነገር ስለሆነና ያንንም በፀጋ ልትቀበለው ይገባልና እኔም ሁኔታዎቹን በዛ ደረጃ ላይ በመመልከት እንዲሁም ከቁጭት ስሜት በመውጣት ቀድሞ ወደነበረኝ ስምና ዝና ለመምጣት ጥረትን አደርጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ ያሉትን ጊዜያቶች በምን መልኩ አሳለፍካቸው?

ምንይህሉ፡- አብዛኛውን ጊዜያቶች በጅማ ከተማ ከሚገኙት ቤተሰቦቼ ጋር ነው እያሳለፍኩ ያለሁት፤ ከዛ ውጪም ለአንድ ሳምንት በቂ እረፍትን ካደርግኩኝ በኋላም የጂምና የትንፋሽ ልምምዶችን በመስራት ራሴን ለአዲሱ የውድድር ዘመን እያዘጋጀውኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ትዳር ዓለሙ አመራህ?

ምንይህሉ፡- ያው በለው፤ ፍቅረኛ አለኝ፤ ሰላማዊት ተካልኝም ትባላለች፤ በባህርማዶ በመገኘት ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰች ስለሆነች የመጪው ዘመን ላይ ከእሷ ጋር ወደትዳሩ ዓለም ማምራታችን አይቀሬ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ዲ.ኤስ.ቲቪ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጋችንን ማስተላለፉን ተከትሎ ምን የተለየ ያጋጠመህ ነገር አለ?

ምንይህሉ፡- በመጀመሪያ ሊጋችን በዚህ መልኩ በዲ.ኤስ.ቲቪ ለመተላለፍ በመቻሉ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ከዛ ባሻገር ደግሞ የጨዋታዎቹ መተላለፍ እኔን በስም የሚያውቁኝ በርካታ ሰዎች በአካልም ተመልክተው እንዲያውቁኝ የተረዳሁበት ሁኔታም ስላለ ያ ለየት ያለ አጋጣሚ ሆኖልኛል፤ ይህን ስትመለከት ደግሞ በጨዋታው መተላለፍ በራሱ አንተም ጠንክረህ በመስራት ታታሪ ተጨዋች እንድትሆንም ሁኔታዎች ይጋብዙሃልና አስደሳች ሁኔታዎች ናቸው ያጋጠሙኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የቀድሞ ክለብህ መከላከያ ከወረደበት ከፍተኛው ሊግ ወደ ነበረበት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም ሊመለስ ችሏል፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?

ምንይህሉ፡- መከላከያ የምወደውና ከልጅነቴ አንስቶም ያሳደገኝ ክለብ ነው፤ እንደ እናትና አባቴም የምቆጥረው ክለብ ነው፤ ከዛ ውጪም ቡድኑ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት ላይም ከእነ ጉዳቴ በማስፈረም ክለቡ ውስጥ ቆይታ እንዳደረግ ያስቻለኝ ስለሆነም ይህ ቡድን ዘንድሮ ባስመዘገበው ውጤት ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ በማለፉ በጣም ነው የተደሰትኩት፤ በዚህ አጋጣሚም ለክለቡ አጠቃላይ አባላቶችና አመራሮች እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለትም እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- እናጠቃል?

ምንይህሉ፡- በእግር ኳስ እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ በቅድሚያ ፈጣሪዬን በመቀጠል ከጎኔ የሆኑትን ቤተሰቦቼን ለእኔ ጥሩ ሀሳቢ የሆነችውንና ብዙ ነገሮችን ያደረገችልኝን መልካሟን ፍቅረኛዬን ሰላማዊትንና እንደዚሁም የእኔ እድገትን የሚመኙት ሁሉ ምስጋናዬን እያቀረብኩላቸው ሌላ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ደግሞ ሊጋችን በዲ.ኤስ.ቲቪ ለመተላለፍ መቻሉ ደስ የሚል ውድድርን እየተመለከትንበት ይገኛል፤ የተወሰነ ችግር ብዬ የምጠቅሰው የአንድአንድ ሜዳዎች ምቹ አለመሆን ነውና ለመጪው ዘመን ውድድር እነዚህ ተስተካክለው ቢቀርቡ በጣም ደስ ይለኛል፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...

ዋልያዎቹዜናዎችየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

አንጋፋው አሰልጣኝ በስማቸው የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ሊገነባላቸው ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ለማመስገን እና ዕውቅና ለመስጠት...