“የበፊቱን ሐዋሳ ከተማን ለመገንባት ጠንክረን እየሰራን ነው”ብሩክ በየነ /ሐዋሳ ከተማ/

የሐዋሳ ከተማን የአጥቂ ስፍራ በጥሩ ብቃቱ እየመራ ያለው ወጣቱ ተጨዋች ብሩክ በየነ ሲዳማ ቡናን ድል ካደረጉ በኋላ ስለ ቡድናቸው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ዙሪያ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች የሀትሪክ ስፖርቱ ድረ-ገፅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አንስቶለት ምላሽን ሰጥቶበታል።

ከሲዳማ ቡና ጋር የነበራቸውን ጨዋታ ስለ ማሸነፋቸው
“ጨዋታው ለእኛ በጣም አስፈላጊያችን እና ካሸነፍን ደግሞ ወደ መሪዎቹ ልንጠጋበት የምንችልበት ነበር። በፈጣሪ እርዳታም ግጥሚያውን ድል አድርገን አሸናፊነታችንን ወደ ማጠናከሩ መጥተናል”።

ስለ ሲዳማ ቡና
“ሲዳማ ቡና ጠንካራ ቡድን ነው። የባለፈው ጨዋታ ላይ ብናሸንፋቸውም ግጥሚያው የወንድማማቾች ደርቢ ከመሆኑ አንፃር ፈትነውን ነበር። በእዛን ዕለቱ ጨዋታ እነሱን በማሸነፋችን ግን በጣም ደስ ብሎኛል”።

ስለ ጠንካራ እና ክፍተት ጎናቸው

“እንደ ጥንካሬ የማነሳው ቡድናችን የሚያደርጋቸውን እያንዳንዱን ጨዋታዎቹን በህብረት ለማሸነፍ መጫወቱንና እንደ በፊቱ ጎሎችን እምብዛም የማናስተናግድ መሆናችን ነው። ሌላው በክፍተት ደረጃ የማነሳው ደግሞ ብዙ ኳሶችን እናገኝና እነዛን አንጠቀምም”።

የሊጉ አጀማመራቸው ላይ ስኬታማ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወራጅ ሊሆኑ ይችላሉ ስለመባላቸው

“በትክክል ውድድሩን ስንጀምር እንደ አሁኑ በተሳካ ሁኔታ አልነበረም። ያ ሊሆን የቻለውም የአዲስ አበባ አየር ከብዶን ስለነበር ነው። ያኔም ሐዋሳ ዘንድሮ ይወርዳል የሚል ነገርን እንሰማም ነበር። አሁን ግን ጅማ ላይ ያ ስጋት እኛ ቡድን ጋር እንደሌለ በምናስመዘግባቸው ውጤቶች እያሳየን ይገኛልና ከዚህ በኋላም በሚኖሩን ጨዋታዎች አሸናፊነታችንን በማስቀጠል የበፊቱን ጠንካራውን ሐዋሳ ከተማን የምንገነባ ይሆናል”።

ስለ ስብስባቸው

“በአብዛኛው በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነው ያለን። ጥቂት ሲኒየር ተጨዋቾችም አሉን። እነሱም ለስኬታማነታችን ጉዞ እኛን እያበረታቱን ይገኛልና ይሄ መሆን መቻሉ ጠቅሞናል”።

ስለ ዘንድሮ እቅዳቸው

“በውድድሩ ከመሪዎቹ ቡድኖች ብዙ አልራቅንም። ሊጉ ደግሞ በርካታ ጨዋታዎች አሉት እና ለዋንጫው ተፎካካሪነት እንጫወታለን”።

ከመስፍን ታፈሰ ጋር ስላላቸው ጥምረት እና ያለፈው ጨዋታ ላይ አንድ ኳስን ስለመከልከሉ

“መስፍን ታታሪ እና ምርጡ የቡድናችን ተጨዋች ነው። ከእሱ ጋርም ጥሩ ጥምረትም ስላለን ዘንድሮ መልካም የውድድር ዘመንን በጋራ እናሳልፋለን። ከሲዳማ ጋር በነበረው ጨዋታ አንድ ኳስን ለእሱ መስጠት ሲኖርብኝ ሳልሰጠው የቀረሁት የሲዳማ ተጨዋቾች እሱ ላይ ያተኮሩ መስሎኝ ነው። ይሄን ችግር በቀጣይ ጨዋታዎች አሻሽለዋለው”።

በመጨረሻ

“ለሐዋሳ ከተማ በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ከጓደኞቼ ጋር ቡድኑን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ እፈልጋለሁ። ቡድናችንም ከነበረበት ብቃት ተሻሽሎም አሁን ላይ ወደ ውጤታማነት መምጣቱም ደስታን እንደፈጠረብኝ መናገርንም እሻለሁ። ለእዚህ እንድንበቃም በተለይ ደግሞ ለወጣት ተጨዋቾች ብዙ እድሎችን እየሰጠ ላለው ጥሩ አሰልጣኛችንም ሙሉጌታ ምህረትም አድናቆቴን መስጠት እፈልጋለሁ”።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor