“ጅማ አባጅፋር ላይ ያስቆጠርኩት ግብ መታሰቢያነቱ ለእናቴ ይሁንልኝ” ዊሊያም ሰለሞን (ኢት.ቡና)

ቁመቱ አጠር ያለና ሰውነቱ ደቂቃ የሆነ ተጨዋች… በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እይታ ግን ለቡድኑ ወሳኝ ዊሊያም ሰለሞን… የሀረሩ ዊሊያም ሼክስፒር…. ገና ከታዳጊነቱ በመከላከያ እግር ኳስ ክለብ አመራር እውቅና ተነፍጎት ከብዙ ክርክር በኋላ ቡናማዎቹን ተቀላቅሎ ምርጥ አቋሙን ማሳየቱን ተያይዞታል፡፡ ጅማ አባጅፋርን 3ለ1 ሲረቱ አንድ ግብ አስቆጥሮ አቡበከር ናስር ላስቆጠረው ግብ በጥሩ ሁኔታ የማቀበል ሚናውን ተወጥቷል፡፡ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረገው ዊሊያም ስለ አበጋዝና ዊሊያም የተሰኙ ስሞቹ፣ ስለኢትዮጵያ ቡናና ካሳዬ አራጌ፣ ስለቀጣዩ እቅድ፣ ስለ ብሔራዊ ቡድን መመረጥ፣ ስለ ጋርዲዮላና ካሳዬ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ከውዝግብ በፀዳ ሁኔታ ላይ መገኘትህ ውጤታማ አድርጎኛል ማለት ትችላለህ?

ዊሊያም፡- አንዳንዴ ህይወት እንዲህ ነው… ውስጤ ሰላም መሆኑና የምወደውን ክለብ መቀላቀሌ የፈጠረብኝ ደስታ ውጤታማ አድርጎኛል፤ በዚህ ፍጥነት እሰለፋለሁ ብዬም አላስብኩም ነበር የፈጣሪ ነገር ሆኖ ተሳክቷል፡፡ ተቀያሪ ሆኜ እየገባሁ ነበር ባለፉት 3 ጨዋታዎች ከሰበታ ከተማ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስና ዛሬ ከጅማ አባጅፋር ጋር በነበረው ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ መጨረሴ አስደስቶኛል፤ በሶስቱም ጨዋታዎች ደግሞ አሸንፈናል ይሄ የፈጣሪ ስራ አይመስልህም? /ቃለ ምልልሱን ያደረግነው ሐሙስ ምሽት ነው/

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ለሰጠኝ እምነት ምላሽ ሰጥቻለሁ ብለህ ታስባለህ?

ዊሊያም፡-የሚጠበቅብኝን እየተወጣሁ ነው ብዬ አላስብም ገና ብዙ ይጠብቅብኛል ካሳዬን ስናይ ከአባትም በላይ ነው ለሰው ሁሉ እኩል ያስባል የሚያበላልጠው ነገር የለም ነገሮችን ቀድሞ ይረዳና ይመክረናል ከአሰልጣኞች ብዙ ጊዜ የማልጠብቀውን ነገር ጠርቶ ይመክራል ማንም ተጨዋች ካሳዬ እንዲነካ አይፈልግም በርሱ ደስተኛ ነን፡፡

ሀትሪክ፡-ዊሊያምና አበጋዝ የሚል ስም መሃል ያለው አንድነት ምንድነው?

ዊሊያም፡- /ሳቅ በሳቅ/ ሁለቱም የኔ ስሞች ናቸው ዊሊያም ቤተሰቦቼ ያወጡልኝ ስሜ ነው አበጋዝ አሁን ሰፈር ውስጥ ከሐረር የመጣ ቅፅል ስም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ጅማ አባጅፋር ቤካም የሚባል ተጨዋች አለ አባቱ ዴቪድ ቤካምን ስለሚወዱት የተሰጠ ስም ነው ያንተስ ዊሊያም ከምን ተነሣ?

ዊሊያም፡-ስሙን ያወጣችልኝ እናቴ ናት አንዴ እንደነገረችኝ ከሆነ 120 ፕሮግራም ላይ ባለው ትረካ ምጥ ላይ ሆና ስለዊሊያም ሼክስፒር ሲነገር ሰማችና ወደደችው በዚህ ምክንያት ዊሊያም ብላ ጠራችኝ ይህን አውቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ያለው ስሜት ምን ይመስላል? ዋንጫ እየታሰበ ነው 2003 ዋንጫ የተገኘበትን 10ኛ አመት ሊከበር?

ዊሊያም፡- የሁላችንም የቋሚዎቹም የተጠባባቂዎቹም ይሁን የሁሉም የቡድኑ አባላት ገና ከመነሻው ዋንጫ የማግኘት እቅድ ይዘን ነው የተነሣነው… ፈጣሪ ተጨምሮበት የ2013 የዋንጫ ባለቤት እንሆናለን ብለን እናስባለን፡፡

ሀትሪክ፡- በመከላከያ አትፈለግም መባልህ ከቡና ጋር ላይሳካልኝ ይችል ይሆን የሚል ስጋት አልፈጠርብህም?

ዊሊያም፡-እንደርሱ እንኳን አላስብኩም፡፡ አልፈለግህም ያለኝ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ሳይሆን የቢሮ ሠራተኞችና ምንም እውቀቱ የሌላቸው ሰዎች ናቸው በዚህም ብዙ አልሰጋሁም ከአሰልጣኙ አፍም አልፈልግህም የሚል ነገር አልወጣም፡፡

ሀትሪክ፡- መከላከያዎች ለዝግጅት አዳማ እያሉ ሄደህ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌን አነጋግረህ አልፈልግህም የኔ እቅድ አይደለህም እንዳለህ አውርተኸኝ ነበር ይሄስ እውነት አይደለም?

ዊሊያም፡-አዎ እውነት ነው ገና ከመነሻው አሰልጣኙን ሄጄ ሳናግር እኔም ተጎዳሁ እናቴን መርዳት እፈልጋለሁ ካደኩኝ ለምንድነው ደመወዜ የማያድገው ብዬ ስጠይቅ ነበር አሰልጣኙን…እርሱም እሺ አለኝና ቢሮ ሄዶ ቡድን መሪዎቹንና አመራሮቹን ጠየቀ ለሌሎቹ ደመወዝ ተጨምሮ ለኔ ብቻ ነው ያልተጨመረው… ሄዶ ሲያናግራቸው እዚህ የመቀጠል ፍላጎት የለውም ካንተ ጋር መስራት አይፈልግም ብለው መለሱለት ያኔ ነው ካልፈለክ መልቀቅ ትችላለህ እቅዴም አይደለህም ያለኝ ለዚህ ሁሉ መነሻው የቢሮ ሠራተኞቹ እንጂ እርሱ አይደለም፡፡ የመጀመሪያ ቀን ልምምድ ስንሰራ ጠርቶ ያበረታታኝ አሰልጣኝ ዮሐንስ ነው ምክትሉ ዮርዳኖስ አባይም ደመወዝ እንደሚጨመርልኝ ነግሮኝ ነበር ከላይ ያለው እውነት እንደሚያስረዳው በአሠልጣኞቹ እፈልግ እንደነበር ያስታውቃል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና አብረኸው በመጫወትህ የተደሰትከው በማን ነው?

ዊሊያም፡- ከአቡበከር ናስርና እያሱ ታምሩ ጋር መጫወቴ አስደስቶኛል፤ ሁለቱም በደንብ ተቀብለውኛል ድጋፋቸውም አልተለየኝምና ማመስገን እፈለጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ትላንትና ዛሬህን ስታይ ምን ይሰማሃል?

ዊሊያም፡- ኳስ ከጀመርኩ ጥቂት አመታት ቢያልፍ ነው በዚህ ደረጃ ፈጣን ለውጥ ማሳየቴና አሁን ያለሁበትን ደረጃ ስመለከት እድለኛ መሆኔ ተሰምቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ባንተ እድሜ ጥሩ አቅም ኖሯቸው መጫወት ላልቻሉ ታዳጊዎች የምትለው ነገር አለ?

ዊሊያም፡-ይሄ ለመከላከያ ብቻ አይደለም ሐረር ላይ በጣም ጎበዝ ጎበዝ የሆኑ እኩዮች አሉኝ እድሉን ሊያገኙ ስለሚችሉ በርትተው እንዲሰሩ የተለያዩ ሙከራ እንዲያደርጉ እዚያ ኳስና በጀትም በደንብ ስለሌለ እዚህ መጥተው እድላቸውን ቢሞክሩ ደስ ይለኛል ይህን ለነርሱ አስተላልፍልኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የሐረር ህብረተሰብ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወይስ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ነው?

ዊሊያም፡-የሐረር ህዝብ ብቸኛ የሐረር ተወላጅ በሆነውና ለቅዱስ ጊዮርጊስ በሚጫወተው አቤል እንዳለ ምክንያት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነበር የኔ ወደ ኢትዮጵያ ቡና መግባት ሲሰማ አብዛኛው ደጋፊ የኢትዮጵያ ቡና ሆኗል… በሁለታችን ምክንያት የሸገር ደርቢ ሐረር ላይ አለ ማለት ነው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ከውጪ የማን ደጋፊ ነህ?

ዊሊያም፡-የማንቸስተር ሲቲና ፔፕ ጋርዲዮላ ደጋፊ ነኝ ጋርዲዮላ ምርጥ አሰልጣኝ ነው፤ ሲቲን ቀይሮታል ጥሩ ቡድንም ገንብቷል፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌና አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ መሀል ምን አይነት ተመሳሳይ ባህሪ አየህ?

ዊሊያም፡-ሁለቱም ላመኑት ሟች ናቸው… ለወጣቶች እድል ይሰጣሉ ባመኗቸው ወጣቶችም አላፈሩም ሁለቱም ደፋርነታቸው ያመሳስላቸዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ፕሪሚየር ሊጉ በዝግ መሆኑ የስሜት መቀዛቀዝ አይፈጥርም?

ዊሊያም፡- ይፈጥራል እንጂ…. ደጋፊ አለመኖሩ ይደብራል ደጋፊው ለተጨዋቾቹ ወሳኝ ነው ከዚህ በተቃራኒ ግን በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉም ደስ የሚል ነገር ነው እድል ይፈጥራል፡፡

ሀትሪክ፡- አብሬው መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ማንን ነው?

ዊሊያም፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚጫወተው አቤል እንዳለ ጋር መጫወት እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት የቅርብ ጊዜ እቅዱ አለህ?
ዊሊያም፡-/ሳቅ/ አዎ ከፈጣሪ ጋር ዘንድሮ ለብሔራዊ ቡድን እጫወታለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተመለከተኝና ምረጠኝ እያልከው ነው?

ዊሊያም፡- ከፈጣሪ ጋር ጥሩ መሆኔ ይሰማኛል ለአገሬም ለመጫወት ዝግጁ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ጅማ አባጅፋርን 3ለ1 ስትረቱ አንድ ግብ አስቀጠርክ አንድ ግብ የሆነ ኳስ ደግሞ አቀበልክ.. የግቧ መታሰቢያ ለማን ይሰጥ?

ዊሊያም፡- አዎ ጅማ አባጅፋር ላይ ያገባኋት ግብ መታሰቢያነቱ ለእናቴ ይሁልኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ .. የምትፈልገውን ማመስገን ትችላለህ..?

ዊሊያም፡-ለመላው ቤተሰቤ፣ ለእናቴ፣ ለአቤል እንዳለ፣ ለሐረር ህዝብ፣ ከጎኔ ለነበሩት የሰፈሬ ልጆች ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌና የአሠልጣኝ ቡድን፣ ለክለባችን ደጋፊዎች በሙሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport