👉…ከ11 ተጨዋቾቹ ጋር በስምምነት ውሉን ቀዷል..
👉….በፍትህ አደባባይም ተሸንፏል…
በገንዘብ ዕጥረት ውስጥ የገባው ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ሁለት አመት ውል ካስፈረማቸው 11 ተጨዋቾቹ ጋር በስምምነት መለያየቱ ተገለጸ።
የሀትሪክ ምንጮች ባገኙት መረጃ መሠረት በ2014 ከፈረሙት 15 ተጨዋቾች በውላቸው መሠረት የቀጠሉት አራት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው። ሙሉ የፊርማ ክፍያ በመውሰዳቸው በ2015 ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ፣ ስብስብ ጋር እንደሚቀጥሉ የተረጋገጠው አራቱ ተጨዋቾች ፍሬዘር ካሳ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደ፣ ጸጋዬ ባህሩና ብርሃኑ ጸጋዬ መሆናቸው ታውቋል።
ከዚያ ውጪ ከትላንት በስቲያ ሰኔ 30 / 2014 ጀምሮ ውላቸው የተቋረጠው አምበሉን ሄኖክ አርፍጮን ጨምሮ ሚካኤል ጆርጅ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ሳምሶን ጥላሁን፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ፣ ኤሊያስ አታሮ፣ መላኩ ወልዴ፣ ኢያሱ ታምሩ፣ ባዬ ገዛኸኝ፤ ሀብታሙ ታደለና አበባየሁ ዮሀንስ መሆናቸው ታውቋል። ክለቡ ከ11 ተጨዋቾች ጋር በመስማማቱ እስከ ሰኔ ወር ድረስ ያለውን ደመወዝ በመክፈል መልቀቂያቸውን መስጠቱ ታውቋል።አብዛኞቹ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ እንደመሆናቸው ቀጣዩ የ2015 የውድድር አመት ጉዞው አስጊ ሆኗል።
በሌላ በኩል ክለቡ በተጠናቀቀው የዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ በ10ኛ ደረጃ በማጠናቀቁ ከሊግ ኩባንያው ሊሰጠው የነበረው 9 ሚሊየን 15ሺ 751. ከ82 ሳንቲም ታግዷል። በቀድሞ ተጨዋቹ አብዱልሰመድ አሊ በመደበኛ ፍርድቤት የተከሰሰው ክለቡ በፍትህ አደባባይም ተሸንፏል። ተጨዋቹ የተሰጠውን ቼክ በማቅረብ በከፈተው ክስ በማሸነፉ የተጨዋቹ ክፍያና የጠበቃ ወጪ ተካቶበት ወደ 700 ሺህ ብር ከክለቡ እንዲከፈለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 5ኛ ፍ/ብሄር ችሎት ወስኗል።
“በፍ/ቤቱ ውሳኔ መሰረት የፕሪሚየር ሊግ ኩባንያ ክለቡ ከሚደርሰው ገንዘብ ቆርጦ ለተጨዋቹ እንዲከፍልና መክፈሉን በጽሁፍ እንዲያረጋግጥለት አዟል ይህም በእግርኳስ የመጀመሪያ ክስተት ነው” ሲል የተጨዋቾች ወኪልና የህግ ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ተናግረዋል።
ሀድያ ሆሳዕና በሌሎችም ተጨዋቾች በመደበኛ ፍ/ቤት የቀረበበት ክስ ለሽንፈት እንዳይደርገው የበርካቶች ስጋት ሆኗል።
በፍ/ቤቱ ውሳኔ ዙሪያ የተጠየቁት የሊግ ኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ እንደተናገሩት ” በፍ/ቤቱ ውሳኔ መሠረት ለክለቡ የሚሰጠው ብር ታግዷል። መክፈል አንችልም የዘንድሮ ውድድር ሲጀመር ለእያንዳንዱ ክለብ የሰጠነው 1.2 ሚሊየን ብር አካባቢም አልተከፈለውም ከክፍያ ጋር ተያይዞ ያለበትን ችግር ካልዘጋ ገንዘቡ በእግድ ይቆያል” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
አስተያየት ይስጡ