ፋሲል ከነማ መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ውጤት ሲያስመዘግቡ ድሬዳዋ ከተማም ከብዙ ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ (30-07-2013) ሲደረጉ የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

ምሽት 1:00 ሲል የጀመረው ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከወላይታ ድቻ ያገናኘ ሲሆን በጨዋታውም አፄዎቹ በሙጂብ ቃሲም 2ግቦች ታጅበው ወደ ዋንጫ የሚያደርጉትን ግስጋሴ አጠናቅረው ቀጥለዋል።

ጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ ለማስተናገድ የፈጀበት 3ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች በበረከት ደስታ አስደናቂ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ከ3ደቂቃዎች በኋላ 6ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት በመጠቀም የተገኘችውን ኳስ የወላይታ ድቻው ቢንያም ፍቅሬ ወደግብ ቢሞክረውም የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሜኬል ሳማኪ በግሩም ሁኔታ አምክኖበታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄን መሰረት ያደረገ ጨዋታ ለመጫወት ሲሞክሩ ታይተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 13ደቂቃዎች ሲቀሩት 32ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከነማው እንየው ካሳሁን ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ሙጂብ ቃሲም በግንባሩ በመግጨት ወደግብነት ቀይሮት አፄዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከዚህች ግብ መቆጠር 5 ደቂቃዎች በኋላ 37ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ዲዲዬ ለብሪ ከርቀት የተላከለትን ኳስ በግብ ጠባቂው ሳማኪ አናት በመላክ ግብ ለማስቆጠር የሞከረ ቢሆንም ተከላካዩ ከድር ኩሊባሊ በግሩም ሁኔታ አውጥቶት የጦና ንቦቹን አቻ እንዳይሆኑ ማድረግ ችሏል። ከዚህም በኋላ የውጤት ለውጥ ሳይኖር የመጀመሪያው አጋማሽ በአፄዎቹ መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ፋሲል ከነማዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥንቃቄ የተሞላ ጨዋታ ሲያደርጉ ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ ውጤቱን ለመቀልበስ ተጭነው ተጫውተዋል። ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል አስደንጋጭ ሙከራ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም። በጨዋታው 76ኛ ደቂቃ ላይ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም ከሽመክት ጉግሳ የተላከለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደግብነት ቀይሮ የአፄዎቹን ድል ማረጋገጥ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላም ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይስተናገድበት ጨዋታው በአፄዎቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች 41ነጥቦችን በመሰብሰብ ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 11 በማሳደግ ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ ሲያጠናክሩ ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በ21 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የእለቱ የመጀመሪያው እና 10:00 ሲል የተጀመረው የድሬዳዋ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ በባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉ ሲሆን በተቃራኒው ጅማ አባጅፋሮች ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ ባለሜዳዎቹ የጨዋታውን የመጀመሪያ ለማድረግ የፈጀባቸው 6ደቂቃዎች ነበር። 6ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ጁንያስ ናንጄቦ አስደናቂ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ወደ ግብነት ግን ሳይቀየር ቀርቷል። በአንፃሩ ጅማ አባጅፋሮች ከጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃ አንስቶ ወደኋላ በማፈግፈግ ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂቂበማድረስ ለመጠቅ ሲሞክሩ ተስተውሏል። ሆኖም ውጤታማ አልነበሩም።

በመጀመሪያው አጋማሽ የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ጁንያስ ናንጄቦ በተደጋጋሚ ግብ የማግባት ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል። ጅማ አባጅፋሮች በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ጥሩ ግብ የማግባት እድል ቢያገኙም የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች ተረባርበው ግቡ እንዳይቆጠርባቸው ማድረግ ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚዎቻቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን በዚህኛውም አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው በተጀመረ 78ኛው ደቂቃ ላይ ሁለቱን ቡድኖች የለየችው ብቸኛ ግብ መገኘት ችላለች። የጅማ አባጅፋሩ ተከላካይ ውብሸት አለማየሁ ሙኅዲን ሙሳ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍ.ቅ.ምት ዳንኤል ሀይሉ ወደ ግብነት ቀይሮት ድሬዳዋ ከተማ ጣፋጭ 3ነጥቦች እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ውጤቱንም ተከትሎ በ16 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ሽንፈት ያስተናገዱት ጅማዎች ደግሞ በ10 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

 

ሊጉን ፋሲል ከነማ በ41 ነጥቦች ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና በ30ነጠቦች እንዲሁም ቅ/ጊዮርጊስ በ27 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ጅማ አባጅፋር በ10ነጥቦች እንዲሁም አዳማ ከተማ በ7ነጥቦች የመጨረሻዎቹን ሁለት ደረጃዎች ይዘዋል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *