የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ በስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ በተደረጉት ጨዋታዎች አራት ተጫዋቾች የቀይ ካርድ የተመለከቱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን በመማታት ከሜዳ የተሰናበቱት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሞሰስ ኦዶ እንዲሁም የወልቂጤ ከተማው ተስፋዬ መላሱ የአራት ጨዋታዎች ዕገዳ እና እያንዳንዳቸው የ3 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል ።
በተጨማሪም የሀምበሪቾ ዱራሜው ቴዎድሮስ በቀለና የመቻሉ ግሩም ሀጎስ የ3 ጨዋታ እና የ3ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በስድስት ክለቦች ላይም የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ተላልፏል። መቻል(አራት ተጫዋቾች)፣ አዳማ ከተማ(አምስት ተጫዋቾች)፣ ባህርዳር ከተማ(ስምንት ተጫዋቾች)፣ ወልቂጤ ከተማ(አራት ተጫዋቾች) በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ ክለቦቹ 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል ፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም አዳማ ከተማ ደጋፊዎቻቸው ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል በሚል የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የእለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸውና የውሀ መጠጫ ፕላስቲክ ጠርሙስ ወደሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት ቀርቧል ያለው ኮሚቴው የክለቡ ደጋፊዎች አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መሠረት 50 ሺህ ብር እንዲሁም ቁሳቁስ ወደ ሜዳ በመወርውራቸው 25 ሺህ ብር በድምሩ 75 ሺህ ቅጣት ክለቡ ተቀጥቷል ብሏል ።
እንዲሁም አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ በመሳደባቸውና ከዚህ በፊት አፀያፊ ስደብ በመሳደብ ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው 75 ሺህ ብር ሲቀጣ የተጋጣሚው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም የራሳቸውን ቡድን ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ለመደባደብና የሀይል ጥቃት ለማድረስ ስለመሞከራቸው ሪፖርት በመቅረቡና ከዚህ ቀደም ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ የ100 ሺህ ብር ተቀጥቷል ሲል የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴው ይፋ አድርጓል ።