የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ቢኒያም ምሩጽ ህጋዊ መስመሩን ባልጠበቀ መልኩ ያለኔ ፍቃድ ወጪ የተደረገበትን የፌዴሬሽኑን አካውንት ማሳገዳቸው ታውቋል።
ፌዴሬሽኑ የሂሳብ አካወንቱ በፕሬዝዳንቱ አቶ ቢኒያም ምሩጽ በአቃቤ ነዋይዋ ወ/ሮ አለምነሽ ፈጠነና በጽ/ቤት ሃላፊዋ ወ/ሮ እታፈራሁ ገብሬ ፊርማ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ከሌሉ በሁለቱ ፊርማ እንዲወጣ ፈቃድ የሰጡበት ማዕተምና ፊርማቸው ያረፈበት የማረጋገጫ ደብዳቤ ለባንኩ ቀርቦ ገንዘቡ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ታውቋል።
ከሰሞኑ ግን በአመራሮቹ መሃል በተነሳው አለመግባባት አቃቤ ነዋይዋና የጽ/ቤት ሃላፊዋ ያለ አቶ ቢኒያም እውቅና ውጪ ፈቃድ የተሰጠበት ደብዳቤ ሳያቀርቡ ወደ 50ሺህ ብር አካባቢ ወጪ በማድረጋቸው አቶ ቢኒያም አካውንቱን ማሳገዳቸው ታውቋል። ባንኩም ያለ መመሪያ ያለ ህጋዊ መንገድ ገንዘቡ የወጣበትን አካሄድ እየመረመረ መሆኑም ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
ባለፈው ቅዳሜ በቫይብስ ሆቴል ሊካሄድ የነበረውን ጠቅላላ ጉባኤና ምርጫ በመደበኛ ፍ/ቤት ያሳገዱት አምስቱ አመራሮች በዋና ጸሃፊውና ምልዓተ ጉባኤ ሳይሟላ ጉባኤው እንዲካሄድ በፈቀዱ አራት የስራ አስፈጻሚዎ ኮሚቴ አባላቶች ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል። ጉባኤውን ከፈቀዱ አራቱ ተከሳሾች ሁለቱ ለፕሬዝዳንትነት ሁለቱ ለስራ አስፈጻሚነት የሚወዳደሩ መሆናቸው የደረሰን መረጃ ያስረዳል።