“ባለፉት አመታት አምጠን አምጠን ዛሬ ተወልዷል በዚህም በጣም ተደስተናል”
መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ
/ የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ ፕሬዝዳንት/
ኢትዮጵያ ቡና ከክለቡ ዋነኛ አጋር ከሆነው ሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ዘመናዊ የተጨዋቾች ማመላለሻ መኪና ዛሬ ተበረከተለት ።
ዛሬ ከቀትር በኋላ በካሌብ ሆቴል በነበረው የርክክብ ስነስርዓት ላይ ” የሰርቪሱ ስጦታ ቃል ከተገባ 5 አመት ያለፈው ሲሆን ባለፉት አመታት አምጠን አምጠን ዛሬ ተወልዷል በዚህም በጣም ተደስተናል። ደጋፊው ቃል ተገብቶ ሳይሰጠን እያለ ለሚያነሳው ጥያቄም ምላሽ በመሆኑ ትልቅ ደስታ የሚፈጥር ነው ዘመናዊ አውቶቢሱ ብዙ ካገለገለ ለአምስት አመታት ነው ከዚያ በኋላስ የሚለው ከአሁኑ መታሰብ አለበት ማናጅመንቱ ቢኖርም ባይኖርም ኢትዮጵያ ቡና ዘላለማዊ በመሆኑ ከፍ ወዳለ ስራ መግባት አለብን… ሰርቪሱ ላይ የኢትዮጵያ ቡናና የሀበሻ ቢራ ሎጎዎች መደረጉ ከደጋፊው ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው” ሲሉ የክለቡ የቦርድ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
“ሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር በራሱ አነሳሽነት ከውል ውጪ መኪናውን መግዛቱ ከእኛ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የመሄድ ፍላጎቱን ያሳያል ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ ደጋፊያችን ከተቋሙ ጎን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ…. ለዘመናዊው አውቶቢስ ግዢ የተመበው 23 ሚሊዮን ብር ቢሆንም መኪናው የተገዛው በ17 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ነው ለዚህም በክለባችን ቦርድ ማኔጅመንትና ደጋፊው ስም አመሰግናለሁ” ሲሉ መቶ አለቃ ፈቃደ ተናግረዋል።
የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኧኝ ወልዴ በበኩላቸው “ላለፉት አምስት አመታት እየተንከባለለ የዋጋ ንረት ሲከሰት በጀቱን እየጨመርን እዚህ ደርሰናል። የዘመናዊው መኪና ግዢው በመፈጽሙ ደስ ብሎናል ክለባችን በፋይናንስ ግልጽ ሆኖ ሙሉ መረጃውን ገቢና ወጪውን የተጨዋቾች ደመወዝ ሳይቀር የሚገልጽ መሆኑ ይታውቃል በዚህ ግዢ የመጀመሪያ ተመስጋኝ ሹፌራችን ነው መኪናው ያለበትን ቦታ ሄዶ አይቶ ፕሮፎርማ አምጥቶ ነው ግዢው የተፈጸመው …መኪናውን የገዛነው ከበላይነህ ክንዴ አስመጪ ድርጅት ሲሆን እኛ መሆናችንን ካወቀ በኋላ ሂሳቡን ቀንሶ ሽያጩን ስላደረገልን እናመሰግናለን” ሲሉ አስረድተዋል። አቶ ገዛኧኝ ጨምረው ሲናገሩ ” የመኪናው ግዢ ከታክስ ጋር 17 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ሲሆን ለተለያዩ የግዢ ሂደቶች ወደ 850 ሺህ ብር ተጨማሪ ወጪ ሆኖ አጠቃላይ ግዢው 18 ሚሊዮን 83 ሺህ 647 ብር አካባቢ ሆኗል ” ሲሉ አብራርተዋል።
ከጫሹ ከበላይነህ ክንዴ አስመጪ ድርጅት ተወክለው የመጡት አቶ ሃይሉ ዘርጋው በበኩላቸው “ኢትዮጵያ ቡና በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ በመጀመሪያ ረድፍ ከሚጠሩት አንዱና አንጋፋ ክለብ ነው … ከዚህ ታሪካዊ ክለብ ጋር ግንኙነት በመፍጠራችን ደስ ብሎናል መኪናው ጎልደን ድራገን ባስ ሲሆን በዘመናዊነቱና ዋጋው ከአውሮፕላን ዝቅ ከመደበኛ አውቶቢሶች ከፍ ያለ ነው ይህን መኪና አዲሱ ደንበኛችን የሆነው ኢትዮ ቡና መረከቡ ትልቅ እመርታ ነው የድርጅቱም ባለቤት አቶ በላይነህ የሚገዛው ኢትዮጵያ ቡና ከሆነ 500 ሺህ ብር ቀንሱ ብለው አዘውን ነው ሽያጩ የተከናወነው” ሲሉ ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ቡና የስራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ይስማሸዋ ስዩምም በዕለቱ እንደተናገሩት ” ከሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ጋር የነበረን የግንኙነት ጅማሮ 10 አመታት ያልፈዋል ያኔ የተተከለውን ግንኙነት ያሳደጉት አሁን ያሉት ናቸው … ሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ገና ጠርሙስ ማምረት ሳይጀምር ነው ከኛ ጋር ግንኙነት የጀመረው…. የክለባችንን ሩጫ ጨምሮ በርካታ ኢቨንቶች ላይ ድጋፍም ሲያደርግ ኖሯል.. ኢትዮጵያ ቡናም ለሀበሻ ታማኝ ደንበኛ በመሆኑ ሀበሻ ከጭንቅላታችን አይወጣም” ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ ይስማሸዋና መቶ አለቃ ፈቃደ የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት ሲጀመር የሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩትና አሁን በህይወት የሌሉትን አቶ ዘውዱ ንጋቱን ከግንኙነቱ ጅማሮ አንስቶ ለነበራቸው ተነሳሽነትና ድጋፍ በክለባቸው ስም አመስግነዋል።
ደጋፊውን በመወከል ንግግር ያደረጉት የደጋፊ ማህበሩ ፕሬዝደንት አቶ መንግስቱ ታደሰ በበኩላቸው ” የኢትዮጵያ ቡናና የሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ግንኙነት ቤተሰባዊ ነው በርካታ ጊዜ የፈጀብን ጉዞ በመጠናቀቁ እንዲሁም የደጋፊው ህልም በመሳካቱ ደስ ብሎኛል ደጋፊያችን የሀበሻ ማርኬቲንግ በመሆን ከተቋሙ ጎን እንደሚሆን እተማመናለሁ” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
17 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ወጪ የተደረገበት ጎልደን ድራገን ባስ ከሹፌሩና ረዳቱ ጋር 53 ሰዎችን የሚይዝ መሆኑ ታውቋል።