የስድስተኛው ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ መካከል ተደርጎ በባህርዳር ከተማ የ2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ባህሩ ነጋሽ ፣ ሔኖክ አዱኛ ፣ አማኑኤል ተርፋ ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ በረከት ወልዴ ፣ ዳዊት ተፈራ ፣ አቤል ያለው ፣ ተገኑ ተሾመ እንዲሁም ሞሰስ ኦዶ በምርጥ 11 ተካተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በባህርዳር ከተማ በኩል ፔፔ ሰይዶ ፣ መሳይ አገኘሁ ፣ ያሬድ ባየህ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ፍራኦል መንግስቱ ፣ አለልኝ አዘነ ፣ ያብስራ ተስፋዬ ፣ አባይንህ ፌኖ ፣ ፍፁም ጥላሁን ፣ ቸርነት ጉግሳ እንዲሁም ሐብታሙ ታደሰ ተሰልፈዋል ።
በብዙ የተጠበቀው ጨዋታ ገና ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረ እና በመጀመሪያው አጋማሽ ተደጋጋሚ ሽኩቻዎች የታዩበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በሁለቱም በኩል በፈጣን የተጋጣሚ ክልል ለመግባት በሚደረጉት ጥረቶች በአንፃራዊነት ፈረሰኞቹ በተሻለ የባህርዳር ከተማን የኋላ ክፍል ለመፈተን ችለው ነበር ።
ጨዋታው በጀመረ በሰከንዶች ውስጥ ሞሰስ አዶ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ተመልሷል ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም አጥቂው በፍሬዘር ካሳ በሳጥን ውስጥ ጥፋት የተሰራበት ቢመስልም የመሀል ዳኛው ፌዴራል አርቢትር ቢንያም ወልደአገኘሁን የፍፁም ቅጣት ምት ለመስጠት አላሳመናቸውም ።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ሞሰስ ኦዶ ከመሳይ አገኘሁ ጋር በተፈጠረ ግጭት ተጫዋቹን በግንባር በመመታቱ በ7ኛው ደቂቃ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
በ13ኛው ደቂቃ ላይ በባህርዳር ከተማ በኩል ቀዳሚ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ተደርጓል ። ሙከራውን ያደረገው የባህርዳር ከተማው የፊት አጥቂ ሀብታሙ ታደሰ ሲሆን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በባህሩ ነጋሽ ተይዟል ።
የቁጥር ብልጫ የወሰዱት የጣና ሞገዶቹ ተጭነው ለመጫወት ጥረቶችን አድርገዋል ። በነዚህ አጋጣሚዎች ፈረሰኞቹ በፈጣን ሽግግር ወደ ባህርዳር ከተማ ሜዳ ለመግባት የሚያደርጓቸው ሙከራዎች በተደጋጋሚ በሚሰሩባቸው ጥፋቶች ይቋረጡ ነበር ።
መሳይ አገኘሁ በ21ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛውን ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት የሞከረው ኳስ ዳግም በባህሩ ነጋሽ ተመልሷል ።
ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ማድረጋቸውን የቀጠሉት የጣና ሞገዶቹ በ28ኛው ደቂቃ ላይ አከታትለው በቸርነት ጉግሳ እንዲሁም አለልኝ አዘነ ወደ ግብ ያደረጓቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ተመልሷል ።
አቤል ያለውን በፊት አጥቂነት በመጠቀም የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ለተጫዋቹ በሚላኩ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል ።
በ36ኛው ደቂቃ ላይ የአምናው የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ቢንያን በላይ የተገኑ ተሾመን መጎዳት ተከትሎ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል ።
ከቢንያም መግባት በኋላ ፈርሰኞቹ ቀደም ባሉት ደቂቃዎች ከነበራቸው በተሻለ በባህርዳር ከተማ የሜዳ ክፍል ላይ እንቅሰቃሴዎችን አድርገዋል ።
የመጀመሪያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ አምስት ደቂቃዎች ሲጨመሩ የጣና ሞገዶቹ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል ።
አባይነህ ፌኖ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ፍፋኦል መንግስቱ ከመረብ አሳርፎታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜም በባህር ከተማ የ1 ለ 0 መሪነት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ አቻነት ለመመለስ ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ ተጨማሪ ግቦችን ለማከል ዕድሎችን በመፈለግ የጀመሩት ነበር ።
በአጋማሹ ቀዳሚ ደቂቃዎች ላይ ከማዕዘን በተሻገረ ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በ53ኛው ደቂቃ ላይም ባህርዳር ከተማ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል ። የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር አመቻችቶ ያቀበለው አባይነህ ፌኖ ከሐብታሙ ታደሰ የተቀበለውን ኳስ ለቸርነት ጉግሳ ያቀበለው ሲሆን የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ነፃ ሆኖ ያገኘውን ኳስ ከመረብ አሳርፏል ።
በ55ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ያለው በሳጥን ውስጥ ገብቶ ያገኘውን ኳስ በግራ እግሩ ወደ ግብ ቢሞክረውም ኳሱ ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ።
አማኑኤል ኤርቦን በዳዊት ተፈራ ተክተው ያስገቡት ፈረሰኞቹ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለአማኑኤልና አቤል በሚላኩ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረዋል ።
በ58ኛው ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማ በኩል አለልኝ አዘነ ከሳጥን ውጪ ያደረገው የግብ ሙከራ በባህሩ ነጋሽ ተመልሷል ።
በሁለት ግብ ልዩነት ጨዋታውን በመምራት ላይ የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ሲጥሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ግብ ለማግኘት የሚደረጉ ሙከራዎቻቸው ውጤታማ መሆን የቻሉ አልነበሩም ።
በ72ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ በግራ መስመር የባህርዳር ከተማ ተጫዋቾች መዘናጋትን በአግባቡ ተጠቅሞ ወደ ፊት ይዞ የገባውን ኳስ ሳይጠቀምበት ሲቀር ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በተቃራኒው አቅጣጫ አባይነህ ፌኖ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ አማኑኤል ተርፋ ደርሶ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 10 ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ከሜዳው መሀል ከተገኘ የቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ አማኑኤል ተርፋ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮታል ።
በቀጣዮቹ የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ የባህርዳር ከተማን የኋላ ክፍል በመፈተን የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ጠንካራ የግብ ዕድልን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ።
በመጨረሻም በባህርዳር ከተማ የ2 – 1 ድል ጨዋታው ተጠናቋል ።
በሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው አርብ ህዳር 28 ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ ባህርዳር ከተማ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በተከታዩ ቀን 9:00 ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ