በቤኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ23ተኛ ሳምንት መርሐግብር ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ከመመራት ተነስቶ 3ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክር ባስመለከተዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በተለይ ባህርዳር ከተማ በፈጣን የመስመር እንቅስቃሴ በጨዋታው አንዳች ነገር ለመፍጠር ሲጥር ፤ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የኳስ ቁጥጥሩን የበላይነት በመዉሰድ ለመጫወት ሲጥሩ ተስተውሏል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ21ኛዉ ደቂቃ ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራ ተደርጎበታል ፤ በዚህም አማካዩ አለልኝ አዘነ ያቀበለዉን ኳስ የመስመር አጥቂዉ ፍፁም ጥላሁን የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ኳሷን ወደ ግብ ልኮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ህዝቄል በቀላሉ ተቆጣጥሮታል።
ከዚች ሙከራ በኋላ በ23ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ግብ ተቆጥሮበታል ፤ በዚህም ከቀኝ ኮሪደሩ በኩል የተሻማዉን የቅጣት ምት ኳስ መሀመድ ኑር ናስር በጭንቅላቱ ቀደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም አንተነህ ተፈራ ከሬድዋን የተቀበለዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ ፊሲል ገ/ሚካኤል ኳሷን እንደምንም አዉጥቷታል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም ከፉዓድ ፈረጃ የተነሳዉን ኳስ አማካዩ የአብስራ ተስፉየ በአየር ላይ ወደ ሳጥኑ አሻምቶ አጥቂዉ ሀብታሙ ገዛኸኝ በጭንቅላቱ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። የመጀመሪያዉ አጋማሽ መጠናቀቂያ 42ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ በባህርዳር የግራ ማጥቃት በኩል ፍራኦል ወደ ሳጥን ያሻማዉን ኳስ ሀብታሙ በጭንቅሌቱ ሲጨርፋት አጠገቡ ይገኝ የነበረዉ የክለብ አጋሩ ፍፁም ጥላሁን ኳሷን ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ኳሷ በግቡ አናት ላይ ወጥታለች።
ከዕረፍት መልስ ገና በ46ተኛዉ ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም ፉዓድ ፈረጃ ያሻማውን የመዓዘን ኳስ ቁመተ መለሎዉ አማካኝ አለልኝ አዘነ በግንባሩ በመግጨት ግብ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
መሪ መሆን ከቻሉ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ብልጫ የወሰዱ የሚመስሉት ባህርዳር ከተማዎች በፉዓድ ፈረጃ እና ፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ግን በቀላሉ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ከዕረፍት መልስ በተለይ አጋማሹ እንደተጀመረ ግብ ያስተናገዱት ቡናማዎቹ እጅጉኑ ተቀዛቅዘዉ የቀጠሉ ሲሆን በተለይ ተቀይሮ በገባዉ ጫላ ተሽታ እና ብሩክ በየነ እንዲሁም መሐመድ ኑር አማካኝነት ጥቂት የሚባሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸዉ ቀሮቷል።
መደበኛዉ 90 ደቂቃ ሊጠናቀቅ የ5 ደቂቃ ዕድሜ ሲቀረዉ ግን ባህርዳሮች ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም 85ተኛዉ ደቂቃ ላይ የቡናዉ ግብ ጠባቂ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ያሬድ ባየ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታዉ 3ለ1 በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።