በሊጉ የ23ኛ ሳምንት ሁለተኛ መርሀግብር ፋሲል ከነማን ከአርባምንጭ ከተማ አገናኝቶ 1 – 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
ፋሲል ከነማዎች በ22ኛው ሳምንት ሀድያ ሆሳዕናን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራ አንድ አራት ቅያሪዎችን በማድረግ አስቻለው ታመነ ፣ አምሳሉ ጥላሁን ፣ ዱላ ሙላቱ እና በዛብህ መለዮን በሽመክት ጉግሳ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ዓለብርሀን ይግዛው ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ይስሀቅ ተገኝ፣ አቡበከር ሻሚል እና ሱራፌል ዳንኤልን በመኮንን መርዶኪዮስ ፣ መሪሁን መስቀለ እና አህመድ ሁሴን ተክተው ገብተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ክለቦች በጥሩ ፉክክር የጀመሩት ነበር ። በተለይም የመጀመሪያ አስር ደቂቃዎች ላይ በአፄዎቹም ሆነ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ዘደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችና አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራም በ9ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከመስመር ይዞ የሄደውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ይስሀቅ ተገኝ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ከሙከራዎች የራቀው ጨዋታው ተመስገን ደረሰ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ባደረገው ሙከራ ሌላ የግብ ዕድል አስመልክቶናል ። ጨዋታው በመጀመሪያ ደቂቃዎች በነበረው ልክ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መመላለሶች ባይታዩበትም በሁለቱም በኩል የግብ አጋጣሚዎችን ለማግኘት ከመጣር አላረፉም ።
ውጤታማ ያልሆኑ የማጥቃቱ የሶስተኛው ዞን የኳስ ፍሰቶች በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመሩት ቡድኖች ኳስ እና መረብና ከማገናኘት አግዷቸዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ላይ የተሻለ የማጥቃት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች በ41ኛው ደቂቃ ላይ ልፋታቸው ፍሬ አፍርቷል ።
በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተነሳው ኳስ በኤሪክ ካፓይቶ በኩል ለተመስገን ደረሰ ደርሶ ተመስገን አዞዎቹን መሪ ያደረገ ግብ በፋሲል ከነማ መረብ ላይ አሳርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአርባምንጭ ከተማ የ1 – 0 መሪነት ተጠናቋል ።
ከዕረፍት መልስ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸዉን ግብ ለማስቆጠር በመጠኑም ቢሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ የቸሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት አፄዎቹ በ56ተኛዉ ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ገዛኸኝ አማካኝነት ጥሩ የሚባል የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸዉ ቀርቷል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም ጫናቸውን የቀጠሉት ፋሲል ከነማዎች በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይ በአማካዩ ሱራፌል ዳኛቸዉ አማካኝነት ከሳጥን ውጭ ጥሩ የሚባል ሙከራን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም በዕለቱ ድንቅ ሲንቀሳቀስ ያመሸዉ ግብ ጠባቂዉ ይስሀቅ ኳሷን እንደምን ወደ ዉጭ አውጥቷታል።
በተቃራኒው አዞዎቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ ካስቆጠሩ በኋላ በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገው በመከላከል አልፎ አልፎ በሚገኙ አጋጣሚዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ቢሆንም በ78ተኛዉ ደቂቃ ግብ አስተናግደዋል።
በዚህም አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸዉ ከአፄዎቹ የቀኝ ማጥቃት በኩል ያሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂዉ ይስሀቅ መቆጣጠር ባለመቻሉ ምክንያት በዛብህ መለዮ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። አፄዎቹ የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በይበልጥ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠንክረው የቀጠሉ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተገባዷል።
ዉጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በ34 ነጥቦች በነበረበት 4ተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በተቃራኒው አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በ24 ነጥቦች 13ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
በ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 7(ሰኞ) ከቀኑ 9:00 ጀምሮ አርባምንጭ ከተማ ከወላይታ ድቻ ሲጫወት በተከታዩ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት ፋሲል ከነማ ለገጣፎ ለገዳዲን ይገጥማል ።