ቀን 10 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ፊሽካ በጀመረዉ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃ ላይ ብልጫ መዉሰድ የቻሉት አፄዎቹ በ8ተኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራ አድርገዋል ፤ በዚህም ዩናታን ፍስሀ ከግራ መስመር ያሻማዉን ኳስ አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ እንደምንም ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢሞክርም አዲሱ ፈራሚ ሚሊዮን ሰለሞን ኳሱን ብሎክ አድርጎበታል።
በድጋሚ በከደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ በመድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ስህተት የተገኘዉን ኳስ አማኑኤል ለአቤል እንዳለ ቢያቀብለዉም ተጫዋቹ ኳሷን ሳይጠቀምባት ቀርቷል። ምንም እንኳን ያን ያህል ሙከራ ባያደርጉም በጨዋታ እንቅስቃሴ ግን መልካም የነበሩት መድኞች በ20ኛዉ ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የመጀመሪያ ሙከራ ሲያደርጉ ፤ በድጋሚ ከደቂቃዎች በኋላ መድኖች በወገኔ ገዛኸኝ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ነክታ ወጥታለች።
በዚህ ሂደት የቀጠለዉ እና ያን ያህል ሙከራ ያላስመለከተዉ መርሐግብርም ተጨማሪ እድሎች በሁለቱም ክለቦች በኩል ሳያስመለክት አጋማሹ ፍፃሜዉን አጊኝቷል ፤ ከዕረፍት መልስ በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ መድኖች አቡበከር ወንድሙ ለመሐመድ አበራ አቀብሎት ወደ ግብ በሞከረዉ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ሳይሳካላቸዉ ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
በተቃራኒዉ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደ ሜዳ በመግባት የማጥቃት ሀይላቸዉን ለማጠንከር የሞከሩት አፄዎቹ ዉጥናቸዉ ሰምሮ በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አግኝተዋል። በዚህም ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን ጌታነህ ከበደ ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በተደጋጋሚ ጫና ፈጥረዉ መጫወት የቀጠሉት አፄዎቹ በጨዋታዉ መገባደጃ 85ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አክለዋል ። በዚህም አፍቅሮት ሰለሞን ተቀይሮ ለገባዉ ናትናኤል ማስረሻ የሰጠዉን ኳስ ተጫዋቹ ወደ ግብነት ቀይሮ አፄዎቹ መርሐግብሩን ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል።
– ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀምበሪቾ ዱራሜን ሶስት ለአንድ በሆነ ዉጤት አሸንፏል ።
በዝናባማ መርሐግብር በተከናወነው እና ያን ያህል ሙከራዎችን ባልተመለከትንበት የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻማዉን ኳስ ዳግማዊ አርአያ ለማግኘት በሚሞክርበት ወቅት ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት በ29ነኛዉ ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት ሀምበሪቾዎች አጥቂዉ ቶሎሳ እየገፋ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ነገር ኳሷን ከቀኝ በኩል ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢህንም ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታለች። ያን ያህል ሙከራ ባላስመለከተዉ የመጀመሪያዉ አጋማሽ መገባደጃ ወቅት 42ተኛዉ ደቂቃ ላይም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ ዳዊት ተፈራ ከቢኒያም በላይ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ያገኛትን ኳስ በቀኝ በኩል በቀኝ እግሩ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ሁለቱም ክለቦች የተጠራ የግብ ዕድልን ለመፍጠር ተቸግረዉ የተስተዋለ ሲሆን በተለይ ፈረሰኞቹ ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ፊት ቢልኩም ዉጥናቸዉ ሰምሮ አደጋ ሳይፈጥሩ ቆይተዉ ነገር ግን በ75ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ከታምራት እያሱ የተቀበለዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብነት ቀይሮ የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ሲያደርግ ፤ የጨዋታዉ መደበኛ ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓትም ሀምበሪቾዎች በቶሎሳ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዉ ጨዋታዉ በፈረሰኞቹ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።