– በዋና ደኛ ኢያሱ ፈንቴ ፊሽካ ቀን 10 ሰዓት ሲል በጀመረዉ እና ተመጣጣኝ የሚባል ፋክክር በተመለከትንበት የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ገና በመባቻዉ በ6ተኛዉ ደቂቃ ላይ ዲቻዎች ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም ዘላለም አባተ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻገረዉን ኳስ አበባየሁ ቢስተዉም ከጀርባ የነበረዉ ብስራት በቀለ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
በሂደት ወደ ጨዋታዉ እየገቡ ጥሩ የሚባሉ ዕድሎችን በቢኒያም አይተን አማካኝነት መፍጠር የቻሉት አዳማዎች በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ዕድል አጊኝተዉ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ፤ በዚህም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ ቢኒያም ኳሷን እየገፋ ሳጥን ዉስጥ ከገባ በኋላ በመሳይ ነኮይ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ ቢመታም ኳሷን አምክኗታል ።
በድጋሚ በ34ተኛዉ ደቂቃ ዘላለም ከቀኝ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ኳስ አሻምቶ የነበረ ቢሆንም በነፃነት አግኝቷት ኳሷን አጊኝቷት የነበረዉ ብስራት ኳሷን ሳይጠቀሞባት ቀርቷል። በዚህ ሂድት በቀጠለዉ ጨዋታም አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲል ቢኒያም ፍቅሬ እና አድናን ረሻድ በፈጠሩት ሰጣ ገባ ሁለቱም በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተዋል።
ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ ግብ አስቆጣሪዉ ብስራት በቀለ በወላይታ ዲቻ በኩል በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታለች ፤ ከዚች ሙከራ በኋላም በድጋሚ የዲቻ ተከላካዮች ቢኒያም አይተን ላይ የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ዬሴፍ ታረቀኝ ዳግም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
በጥሩ ፉክክር እየተሟሟቀ በቀጠለዉ የዕለቱ ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ ዲቻዎች በኢዮብ ተስፋየ የግንባር ኳስ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ሲያደርጉ ፤ በድጋሚ አበባየሁ ሀጂሶ በ89ነኛዉ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ እና ሊጠናቀቅ የዳኛዉ ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት ግን በ97ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል የተሻማዉን ኳስ ቢኒያም አይተን እንደምንም ታግሎ ለሙሴ አቀብሎት ነፃ የነበረዉ ሙሴ ኪሮስ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አዳማ ከተማ በመጨረሻም አቻ ማድረግ ችሏል።
– በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሲዳማ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ጨዋታቸዉን በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል ።
ምሽት 1:00 ሰዓት ሲል በተጀመረዉ እና ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ወደ ሜዳ በገቡት ሁለት ክለቦች መካከል በተደረገዉ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከጨዋታዉ መባቻ አንስቶ ሲዳማዎች በንፅፅር የተሻሉ ሁነዉ የተመለከትናቸዉ ሲሆን ነገር ግን በሙከራ ረገድ ሲቸገሩ ተስተውሏል ።
በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማዎች በጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ የተወሰደባቸው ሲሆን በአጋማሹም አንድ ቀዳሚ ተጠቃሽ ሙከራ አድርገዋል በዚህም ከማዕዘን የተሻማዉን ኳስ በተደጋጋሚ የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ወደ ግብ ሞክረዉ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ መክብብ እና ተጫዋችቾ ብሎክ አድርገዉት በመጨረሻም በዛብህ በረዥሙ አዉጥቶታል።
ያን ያህል ሙከራ ባልተመለከትንበት የምሽቱ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽም ሲዳማዎች በ22ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል ቡልቻ ሹራ ድሪብል እያደረገ ሳጥን ውስጥ ገብቶ በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ፋሪስ ከግቡ ወጥቶ ኳሷን አምክኗታል።
እምብዛም ሙከራ ያላስመለከተዉ የመጀመሪያው አጋማሽ በዚህ ሁኔታ ፍፃሜዉን ሲያገኝ ፤ በሁለተኛዉ አጋማሽም ሲዳማዎች በተሻለ ማጥቃት ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲጥሩ በተቃራኒው ወልቂጤዎች ደግሞ ወደ ኋላ አፈግፍገዉ በይበልጥ በመከላከል ሲጫወቱ ተስተዉሏል።
የጨዋታዉ ሰዓት እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተቀዛቀዘ በቀጠለዉ የምሽቱ ጨዋታ በመጨረሻዉ ደቂቃ ላይ በወልቂጤ ከተማ በኩል ተመስገን በጅሮንድ ከቀኝ መስመር በኩል በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም መክብብ ደገፉ በአስደናቂ ብቃት ኳሱን አዉጥቷት በመርሐግብሩም ሁለቱም ክለቦች ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታዉ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።