አርባምንጭ ከተማን ተከትሎ ከፕሪምየር ሊጉ ለመውረድ በቀሪ ሁለት ሳምንታት ስድስት ቡድኖች ተፋጠዋል።

የ2018 የውድድር ወመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀያ ክለቦች መካከል ከአመታት በኋላ እየተደረገ ቆይቶ ሊጠናቀቅ በእጅጉ ተቃርቧል። ፕሪምየር ሊጉ ከቀናት በፊት ሲዳማ ቡና የሊጉን ዋንጫ በአስረኛ የክለቡ አሰልጣኝ በሆነው ያሬድ ገመቹ አማካኝነት በማንሳት አስረኛው ክለብ መሆኑን ማረጋገጥ የቻለበት ሲሆን በተቃራኒው በዛሬው ዕለት ደግሞ አርባምንጭ ከተማ በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ እየተመራ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ለሦስተኛ ጊዜ ከፕሪምየር ሊጉ በፋሲል ከነማ 2ለ0 መሸነፉን ተከትሎ መውረዱን አረጋግጧል።
ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ብቻ በቀረው የ2018 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አርባምንጭ ከተማን ተከትሎ የሚወርደውን ቡድን ለመለየት በሚደረገው ትንቅንቅ ስድስት ቡድኖች በቀጣይ የሚፋጠጡ ይሆናል። 44 ነጥቦችን በመያዝ 14ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ሸገር ከተማ አንስቶ ወደታች የሚገኙት አዳማ ከተማ ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ፣ ምድረገነት ሽረ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ እጅግ ተጠባቂ መርሀግብሮቻቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን በሊጉ ለመቆየትም ቀጣይ ጨዋታዎቻቸውን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተዋል።
በተለይ በ37ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀግብር ሸገር ከተማ ከ መቻል ፣ አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻ ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ከወረደው አርባምንጭ ከተማ ፣ ምድረገነት ሽረ ከኢትዮጵያ መድን ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም ደግሞ መቐለ 70 እንደርታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚፋለሙባቸው ጨዋታዎች በእጅጉ የሚጠበቁ ሲሆን አሸናፊ መሆን የሚችሉ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ለከርሞ መቆየት የሚችሉባቸውን ዕድሎች በይበልጥ የሚያስላቸው ሲሆን ምንአልባት የ37ኛ እና የ38ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማሻሻያ ተደርጎባቸው ላለመውረድ የሚጫወቱ ቡድኖች ከመሆናቸው አኳያ በተመሳሳይ ሰዓት በተለያየ ሜዳ ላይ ሊደረጉ እንደሚችሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አስተያየት ይስጡ