በግብፅ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያውን እያካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በሰፊ የጎል ልዩነት ተጋጣሚውን አሸንፏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ የዛንዚባሩን ኒዉ ጄኔሬሽን 10 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ረምርሟል። በጨዋታዉም አምበሏ ሎዛ አበራ አምስት እንዲሁም መዲና አዎል ሶስት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ቀሪዎቹን ሁለት ጎሎች ደግሞ አረጋሽ ካልሳ እና ሀሳቤ ሙሶ በማስቆጠር ክለባቸዉ 10ለ1 እንዲያሸንፍ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በዕለቱም ሎዛ አበራ ካስቆጠረቻቸዉ ስድስት ጎሎች በተጨማሪም አምስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችታ ማቀበል ስትችል ከዚህ በተጨማሪም በውድድሩ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ በአስራ አንድ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ችላለች።
በዉድድሩም ሎዛ አበራ እና መዲና አወል በእኩል ስድስት ጎሎች የኮከብ ግብ አግቢነቱን መምራት የጀመሩ ሲሆን ፤ ክለባቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ቀሪ አንድ ጨዋታ እየቀረው ለግማሽ ፍፃሜው ማለፋን አረጋግጧል።
- ማሰታውቂያ -
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምድቡን የመጨረሻ ጨዋታም ከዩይ ጆይንት ስታር ጋር የፊታችን አርብ ከቀኑ በ10:00 በካሳራኒ ስታዲየም የሚያደርግ ይሆናል።