በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተፈፀሙ የዲሲፕሊን ጥፋቶች ላይ የቅጣት ውሳኔዎች ተላልፈዋል ።
በዘጠነኛው ሳምንት በተካሄዱ 8 ጨዋታዎች 38 ተጫዋቾች/የቡድን አመራሮች የማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርድ እንዲሁም 3 ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል ። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ቅዳሜ ታህሳስ 16 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች) ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ በዲስፕሊን መመሪያው መሰረት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
መሀመድ አብዱለጢፍ ( ድሬዳዋ ከተማ ) ክለቡ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ በመሆኑ የአንድ ጨዋታ እገዳ ፤ ዋኬኔ አዱኛ ( አዲሴ አበባ ከተማ ) ክለቡ ከድሬዳዋ ከተማ በነበረው ጨዋታ ከሳጥን ውጪ ኳስ በእጅ በመመለሱ ከሜዳ በቀይ ካርድ የተሰናበተ ሲሆን የአንድ ጨዋታ እገዳ እና የ3,000 ብር ቅጣት ፤ ግርማ ዲሳሳ ( ባህርዳር ከተማ ) ክለቡ ከአዳማ ከተማ በነበረው ጨዋታ ላይ ዳኛውን አፀያፊ ስድብ በመሳደብ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱን ተከትሎ የሶስት ጨዋታ እገዳ እና የ3,000 ብር ቅጣት እንዲሁም ብሩክ በየነ ( ሀዋሳ ከተማ ) ክለቡ ከአርባምንጭ ከተማ በነበረው ጨዋታ ላይ በ66ኛ ደቂቃ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን በሚገልፅበት ጊዜ በውስጥ ልብስ ላይ ሀይማኖታዊ መልዕክት የሚያስተላልፍ ምስል በማሳየቱ የ3,000 ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል ።
በክለብ ደረጃ ባህርዳር ከተማ ክለቡ ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የክለቡ አራት ተጫዋች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ እንዲሁም በተመሳሳይ ሃዋሳ ከተማ ክለቡ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ስድስት ተጫዋች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በክለብ ደረጃ 5,000 ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡
በተጨማሪ ሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ክለቡ ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎችና የደጋፊ አስተባባሪዎች በጨዋታው መጠናቀቂያ ወቅትና ጨዋታቸው ካለቀ በኋላ ከፖሊስ ጋር ግጭት ስለመፍጠራቸውና ድንጋይ ስለመወርወራቸው ፣ የተለያዩ የስታዲየሙ ንብረቶች ላይ ጉዳት ስለማደረሳቸው ሪፖርት ቀርቦበታል ። የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ የ75,000 ብር እንዲከፍል ወስኗል። ከዚህም በተጨማሪ በሪፖርት ላይ የቀረቡትን የተነቃቀሉና የተሰበሩ ንብረቶችን እንዲያሰራ ወይም ባለንብረቱ አስልቶ በሚያቀርበው ዋጋ መሰረት ክፍያ እንዲፈፀም ወስኗል ።
አስተያየት ይስጡ