አርባምንጭ ከተማ ቶጓዋዊ ግብ ጠባቂና ጋናዊ የመሃል ተከላካይ በዛሬው ዕለት አስፈርሟል
የተጫዋቾች ውል በማራዘም እና አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው በመቀላቀል ስብስባቸው በማጠናከር ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ እግርኳስ ክለብ አዞዎቹ የቶጎ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ኢድሪሳ ኦጎጆንና ጋናዊ እስቲፈን ባዱ አስፈርመዋል።
ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ኢንተንቴ ከተባለ የሀገሩ ክለብ ጋር ቆይታ የነበረውና ከዚህ ቀደም ለቶጎ የእድሜ ዕርከን ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የዋናው ብሄራዊ ቡድን የግብ ጠባቂው ለክለቡ ፊርማውን አኑሯል ።
በዋና አስልጣኝ በረከት ደሙ የሚመራው ክለብ ሌላኛውን 6ኛውን ፈራሚ አድርጎ ጋናዊውን ከዚህ ቀደም በጋና አሻንቲ ኮቶኮ በተባለ ክለብ በውድድር ዓመቱ ምርጥ ተከላካይ በመባል የተመረጠውንና በ2016 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በመቻል ቤት 29 ጨዋታዎችን ማከናወን የቻለውን እስቲፈን ባዱን አስፈርሟል።
አርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በፕሪሚየር ሊጉም ብርቱ ተፎካካሪ ለመሆንና ጥንካሬውን ለማስቀጠል የክለቡ ነባር ተጨዋቾችን ውል በማደስና አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደክለቡ የማቀላቀል ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል ።