33ኛው የቶታል ኢነርጂስ የአፍሪካ ዋንጫ በመጪው ጥር 2 በካሜሩን አስተናጋጅነት ይጀመራል ። የዚህ ውድድር ዋንጫም በውድድሩ የስያሜ ስፖንሰር ቶታል ኢነርጂስ አማካይነት በተመረጡ 18 የአፍሪካ ሀገራት በመጓዝ ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርብ ይፋ ተደርጎ ነበር ።
የአፍሪካ ዋንጫው መስራች ከሆኑት ሀገራት አንዷ ፤ የአንድ ጊዜ ሻምፒዮኗ እንዲሁም የአንድ ጊዜ የፍፃሜ ተፋላሚ በሆነችው ሀገራችንም ከዛሬው ዕለት ጀምሮ በይፋ ለዕይታ ቀርቧል ።

ዋንጫው በቶታል ኢነርጂስ ኢትዮጵያ ዋና መስሪያ ቤት በተደረገው ፕሮግራም የተለያዩ እንግዶች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የቶታል ኢነርጂስ የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ማናጀር አን ሶፊያ ፤ የተቋሙ የብራንድ አምባሳደር ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ም/ዋና ፀሐፊ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ ንግግር ካደረጉ በኋላ በቦታው የተገኙ አካላት ከዋንጫው ጋር የማስታወሻ ፎቶ ስነ ስርዓት አድርገው የዕለቱ ዝግጅት ተጠናቋል ።


የአፍሪካ ዋንጫው እስከ መጪው አርብ በአዲስ አበባ የሚቆይ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ ይፋ በሆነው መሰረት በመጪው ሀሙስ ለመዲናዋ ነዋሪዎች በቦሌ እና በሜክሲኮ በሚገኙ የቶታል ነዳጅ ማደያዎች ለህዝብ ዕይታ የሚቀርብ ሲሆን በዕለቱም ከቀኑ 10:30 ጀምሮ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚዘጋጅ ደማቅ ሥነ-ስርዓት የመንግስት ሀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት እንዲሁም ጥሪ የሚደረግላቸው እንግዶች በተገኙበት በሚዘጋጅ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቆይታውን የሚያጠናቅቅ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ