በመጀመሪያው ጨዋታ ከቀኑ በ8 ሰአት ላይ የምድቡን ሁለቱንም ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡትን መከላከያ እና ጅማ አባ ጅፋርን ያገናኘ ሲሆን ጨዋታዉም በጅማ አባ ጅፋር 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ጨዋታው ከጅማሬው ፈጣን እና በግብ ሙከራዎች የታጀበ ነበር ። በተለይም ጅማ አባ ጅፋር በመሀመድኑር እና በዳዊት ፍቃዱ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ። በ12ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ በጭንቅላት በመግጨት ለጅማ አባጅፋር የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ ።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ነበር ። በ42ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር የመጀመሪያውን ግብ አስቆጣሪ ዳዊት ፍቃዱ ይዞት የገባውን ኳስ ለማቀበል ሲሞክር የመከላከያው አምበል ገናናው ረጋሳ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ጅማ አባ ጅፋር 2 ለ 0 እንዲመራ ሆነ ። የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽም በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሩ በፊት በዮሀንስ ሳህሌ የሚመራው የመከላከያ ቡድን በመጀመሪያው ግማሽ በአጥቂ መስመሩ ላይ የነበረውን ክፍተት ለማስተካከል ሁለት ቅያሪዎችን አደረገ ። ቅያሪዎችም በሜዳ ላይ በግልጽ የሚታይ ለውጥ ያመጡ ነበሩ ።
መከላከያ ከእረፍት መልስ ኳሱን በመቆጣጠር ወደ ፊት ለመሄድ ሲምክሩ ተስተውሏል ። በአንፃሩ ጅማ አባጅፋሮች የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ተቃራኒ ገብ ክልል በመውሰድ ጫና መፍጠር ችለዋል ። 56ኛ ደቂቃ ላይ ወጣቱ አጥቂ መሀመድኑር ከዳዊት እስጢፋኖስ የተቀበለውን ኳስ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ በመምታት ለጅማ አባጅፋር ሶስተኛውን ግብ አስቆጠረ ።

መከላከያ ከ 3 ለ 0 መመራት በኋላ ውጤቱን ለመቀልበስ ተጭነው ቢጫወቱም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም በተለይም 68ኛ ደቂቃ ላይ የመከላከያው 14 ቁጥር ሰመረ ሃፍተይ በረኛውን አልፎ ያመከነው ኳስ እንዲሁም 81ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሰመረ ሃፍተይ በጭንቅላት ገጭቶት ለገዛኸኝ ደርሶ ወደ ግብ የሞከረው እና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር ።
መከላከያ ተጭነው ጅማ አባጅፋሮች አፈግፍገው እየተጫወቱ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ 4ኛው ዳኛ ያሳዩት ተጨማሪ 4 ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሲል በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የመከላከያው ቢንያም በላይ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ የጅማ አባጅፋሩን ግብ ጠባቂ አልፎ መረብ ውስጥ አረፈ ።

ጨዋታውም በጅማ አባጅፋር 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ። በጨዋታው ለጅማ አባጅፋር የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ዳዊት ፍቃዱ የጨዋታው ኮከብ በመባል የዋንጫ እና የ12,000 ብር ተሸላሚ ሆኗል ።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከምድቡ መውደቃቸውን ያረጋገጡትን ኢትዮጵያ ቡናን እና አዲስ አበባ ከተማን ያገናኘ ነበር ። ኢትዮጵያ ቡና በሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች እንዳደረገው በብዛት ታዳጊ ተጨዋቾችን ነበር በቋሚ አሰላለፍ የተጠቀመው ። የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ብዙም ሳቢ ያልነበሩ ኳሶች ወደ ግብ የማይደርሱበት እና መሀል ሜዳ ላይ ብቻ በሁለቱም ክለቦች በኩል የሚንሸራሸሩ ነበሩ ።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ጊዜ ምንም አይነት ኢላማውን የጠበቀ የጎል ሙከራ ያልታየበት ነበር ። ኢትዮጵያ ቡና በእንዳለ ደባልቄ እንዲሁም በሮቤል ተክለሚካኤል አማካይነት የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም ። በአዲስ አበባ ከተማ በኩልም ምንም አይነት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ያላስመለከተን ሲሆን በተለይም 29ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ የሰራውን ስህተት ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም የአዲስ አበባ ከተማው ፍፁም ጥላሁን ኳሷን ከግቡ አግዳሚ በላይ ልኳታል ።

በሁለተኛው አጋማሽ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢኖርም ጨዋታው ግን በግብ ሙከራዎች የታገዘ አልነበረም ። በ69ኛ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ላይ ኳሱን ይዞ የገባው የኢትዮጵያ ቡናው የቀኝ መስመር ተከላካይ ቃልአብ ለእንዳለ ደባልቄ አሻግሮለት እንዳለም በግሩም አጨራረስ ለኢትዮጵያ ቡና በውድድሩም ሆነ በጨዋታው የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ ።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ጫና ፈጥረው ለመጫወት ቢጥሩም የቡናማዎቹን ተከላካይ አልፈው ግብ ማስቆጠር ከብዷቸው ነበር ።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የነበረው የጨዋታው ፍጥነት ተመልካችን የሚያዝናና የነበረ ሲሆን በጨዋታው ከተቆጠረው አንድ ግብ ውጪ ሌላ ጎል ሳይቆጠር በኢትዮጵያ ቡና 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ። በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡናን የመሀል ሜዳ በድንቅ ብቃት ሲመራ የነበረው ሮቤል ተክለሚካኤል የጨዋታው ኮከብ በመባል የተዘጋጀለትን የዋንጫ እና የ12,000 ብር ሽልማት ተረክቧል ።

በዚህም መሰረት ጅማ አባጅፋር ምድቡን በ9 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ መከላከያ በ6 ነጥብ ሁለተኛ በመሆን ወደ ቀጣይ ዙር አልፈዋል ። እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በ3 አዲስ አበባ ከተማ በ0 ነጥብ 3 እና 4ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል ።
አስተያየት ይስጡ