በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በባህርዳር አለምአቀፍ ስታድየም ሴኔጋልን የገጠመችው ኢትዮጵያ አንድ ለ ባዶ በሆነ ውጤት ተሸንፋለች ።

ከፍ ባለ ተነካሽነት ጨዋታውን የጀመሩት ሴኔጋሎች ጎል ማስቆጠር የቻሉት 11ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በጥሩ አንድ ሁለት ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሰው ያሬድ ባዬ ለቆ የሄደውን ቦታ በረከት ሳሙኤል አስፍቶለት ነፃ ቦታ ሆኖ ኳስን ከኒኮላ ጂክሰን የተቀበለው በክረምቱ ፒኤስጂን ለቆ አስቶንቪላን የተቀላቀለው ኢብራሂም ምባዬ አቡበከር ኑራ መረብ ላይ በማሳረፍ ሀገሩን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
በኳስ ቁጥጥሩ የቴራንጋ አንበሶቹ የበላይነቱን ይዘው ሲቀጥሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ በረጃጅም ኳስ እና በሽግግር ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የተጋጣሚያቸው ሳጥን ሲደርሱ ግን ፍፁም መረጋጋት አይታይባቸውም ለዚህም ማሳያው አቤል ያለው በረጅሙ ያገኘውን ኳስ ነፃ ሆኖ ከእግሩ ስር ያመለጠችበት ቅፅበት እና በቀላሉ እና በተመሳሳይ ወደ ግራ አቅጣጫ በረጅሙ ለቢኒያም ፍቅሬ የተጣለን ኳስ በጥልቀት ገፋ አድርጎ አክርሮ ሲመታ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችዋ አጋጣሚ ተጠቃሾቹ ናቸው።
ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመራ ሲቃረብ እንደ አጀማመሩ መሆን ያልቻለው እና መጠነኛ መቀዛቀዝን ያሳየን ጨዋታው ከነዓን ማርክነህ እንደምንም ታግሎ ሰጥቶ ቢኒያም ፍቅሬ ወደ ጎል ሞክሮ ለጥቂት የቀኝ ቋሚውን ታካ ለጥቂት ልትወጣ የቻለችዋ አጋጣሚ ምንአልባትም ዋልያዎቹን ወደ አቻነት ልትወስድ ትችል የነበረች ሙከራ ነበረች።
በይበልጥ ከፍ ብሎ መታየት በቻለው ሁለተኛው አጋማሽ በንፅፅር ዋልያዎቹ የአቻነት ውጤት ፍለጋ ላይ ትኩረት በማድረግ በአንፃሩ ሴኔጋሎች በበኩላቸው ጥንቃቄን መርጠው ያስቆጠሯትን ግብ ማስጠበቅ ላይ ረጅሙን ጊዜ ሲያሳልፉ ተስተውሏል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ የሚያስቆጭ ዕድልን አግኝታለች ጥሩ ሲንቀሳቀስ በጨዋታው የተመለከትነው ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ የሳጥን ክፍል በጥልቀት ገብቶ ያሻገረውን ኳስ ከነአን ማርክነህ በግንባር ገጭቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ የኒሱ ግብ ጠባቂ ይሄቫን ዲዮፍ አውጥቶበታል።
ጥንቃቄያቸውን በይበልጥ በማሳደግ በመልሶ ማጥቃት ዕድልን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ሴኔጋሎች ሌላ ሁለተኛ ጎል ሊሆን የሚችል አጋጣሚን ፈጥረው የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ ባስደናቂ መልኩ ካወጣበት በኋላ ጨዋታው ተጨማሪ ነገር ሳያሳየን በሴኔጋል 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አስተያየት ይስጡ